እስራኤል በሶሪያ ኢራናዊያን ጄነራሎችን በመግደል ተከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኘው የኢራን የቆንስላ ሕንጻ ላይ እስራኤል በፈፀመችው ጥቃት ሰባት ጄነራሎች መገደላቸውን የኢራን የአብዮት ጠባቂዎች ተናገሩ።
ከሟቾቹ መካከል የአብዮታዊ ጠባቂው ክንፍ የሆነው የኩድስ ኃይል ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ብርጋዲዬር ጀነራል መሐመድ ሬዛ ዛሄዲ እና ምክትላቸው ብርጋዲየር ጀነራል ኦሐመድ ሐዲ ሐጂ ራሒም እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
የኢራን እና የሶሪያ መንግሥታት ከኢራን ኤምባሲ ቀጥሎ የሚገኘውን ሕንጻ ያወደመውን ይህን ጥቃት አውግዘዋል።
የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ላይ ለውጭ ሚዲያዎች አስተያየት አልሰጠም።
ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሶሪያ በአብዮታዊ ጥበቃው በገንዘብ ይደገፋሉ እና ይሰለጥናሉ ካላቸውና ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸው የተለዩ ኢላማዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶች መፈፀሙን አምኗል።
እስራኤል፣ በሰሜን የአገሪቷ ክፍል ሔዝቦላህ እና ሌሎች በሊባኖስ እና በሶሪያ የሚገኙ እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች ድንበር ተሻግረው ለፈፀሙባት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ባለፈው ጥቅምት ወር በጋዛ ላይ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በሶሪያ ላይ የምትፈፅመው ጥቃት ጨምሯል።
ሰኞ ዕለት የተፈፀመው ጥቃትም ግጭቱን እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የእስራኤል የጦር አውሮፕላን ሰኞ ዕለት በደማስቆ ምዕራባዊ አካባቢ ሜዜህ የሚገኘው የኢራንን የቆንስላ ሕንጻ ኢላማ አድርጓል ብሏል።
የሶሪያ የአየር መከላከያ የተወሰኑ ሚሳኤሎችን መትቶ የጣለ ቢሆንም ሌሎች ግን አልፈው ሕንጻውን አፍርሰዋል፤ በሕንጻው ውስጥ ነበሩ ሰዎችን ገድሏል፤ አቁስሏል ብሏል ሚኒስቴሩ።
አስክሬኖችን ለማውጣት እና የተጎዱትን በሕይወት ለማትረፍ ከፍርስራሽ ውስጥ የማውጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ የደረሰውን የጉዳት መጠን እና የተጎጂዎችን ማንነት በስም አልጠቀሰም።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ከሕንጻው ጭስና አቧራ ሲወጣ አሳይተዋል።
ከወደመው ሕንጻ ቀጥሎ የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ግን የደረሰበት ጉዳት የለም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራን አምባሳደር ሁሴን አክባሪ “ የእስራኤል ኤፍ 35 ተዋጊ ጄቶች በጭካኔ የመኖሪያ አካባቢዎችንና የቆንስላውን ሕንጻ ኢላማ አድርገዋል” ብለዋል።
አምባሳደሩ ለኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት በጥቃቱ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል።
አብዮት ጠባቂው በኋላ ላይ በሰጠው መግለጫም ብርጋዲየር ጀነራል መሐመድ ሬዛ ዛሄዲ እና ብርጋዲየር ጀነራል ኦሐመድ ሐዲ ሐጂ ራሂምን ጨምሮ “አዛዦች እና ከፍተኛ የጦር አማካሪ” ሲል የገለጻቸው ሰባት የሚሆኑት የጦር መኮንኖች መገደላቸውን ገልጿል።
የኢራን ሚዲያ እንደዘገበው የ63 ዓመቱ ዛሄድ የአብዮት ጠባቂው ክንፍ የሆነው በቁዳስ ኃይል ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩ ሲሆን በሌባኖስ እና ሶሪያ ከአውሮፓውያኑ 2008 እስከ 2016 ድረስ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል። ሐጂ ራሂም ደግሞ የእርሳቸው ምክትል እንደሆኑ ገልጿል።
በዚህም ዛሄዲ እስራኤል እያካሄደችው ባለው ዘመቻ ከተገደሉ ከፍተኛ የኢራን አዛዦች መካከል አንዱ ሆኗል።
ተቀማጭነቱን በዩኬ ያደረገው የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ታዛቢም የቁዳስ ኃይል ከፍተኛ መሪ፣ ሁለት የኢራን አማካሪዎች እና አምስት የአብዮታዊ ጠባቂዎች በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሳል ሜክዳድም “ ጭካኔ የተሞላበት ያሉትን ጥቃት” ያወገዙ ሲሆን በጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎችም ሰለባ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ስለጥቃቱ እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በደቡብ እስራኤል ከተማ ኤላት የባሕር ኃይል ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ገልጸዋል። ድሮኑ ኢራን ሰራሽ ሲሆን የተላከውም በኢራን ነው ብለዋል።
ይህ ጥቃት የተፈፀመው እስራኤል በደማስቆ እና ባለፈው አርብ በሰሜናዊቷ ከተማ አሌፖ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት ተከትሎ ነው። የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ተቋም እንዳለው በዚህ ጥቃት 38 የሶሪያ ወታደሮችንና ሰባት በኢራን የሚደገፉ የሌባኖስ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ አባላትን ጨምሮ 53 ሰዎች ተገድለዋል።
ባለፈው ጥር ወር ላይም እስራኤል በሜዜህ ላይ ሌላ ጥቃት ፈፅማ ነበር።በዚህም አምስት ከፍተኛ የአብዮት ጠባቂዎችና በርካታ የሶሪያ የጸጥታ ሰዎች ሰለባ ሆነውበታል ተብሏል።












