የተመድ ፍርድ ቤት እስራኤል ምግብ እና መድሃኒት ጋዛ እንዲገባ እንድትፈቅድ አዘዘ

የጋዛ ሕጻናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ሕጻናት የምግብ እርዳታ ሲጠባበቁ

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል ሊከሰት የሚችለውን ረሃብ ለማስወገድ ምግብ እና መድሃኒት ጋዛ እንዲገባ እንድትፈቅድ አዘዘ።

የተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እስራኤል “በአስቸኳይ የሚፈለጉ አገልግሎቶች እና ሰብዓዊ እርዳታዎች” እንዲገቡ “ያለመዘግየት” መፍቀድ አለባት ሲል ወስኗል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሰማው በሳምንታት ውስጥ ጋዛ በረሃብ ልትመታ ትችላለች የሚል ማስጠንቀቂያ ከወጣ በኋላ ነው።

የተመድ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች በሕግ አሳሪ ቢሆኑም ፍርድ ቤቱ ግን የሚያስተላልፈውን ትዕዛዝ ተፈጻሚ የማድረግ አቅም የለውም።

እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እስራኤል ሆነ ብላ የሰብዓዊ እርዳታዎች ጋዛ እንዳይደርሱ እንደምትከለክል ይጠቁማሉ። እስራኤል ግን መሰል ትችቶች መረጃ ላይ የተመሰረቱ አይደለም በማለት ታስተባብላለች።

ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው በሚል በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ክስ ሲመለከት ነበር።

ባለፈው ሳምንት በዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚመራ ኤጀንሲ 2.2 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች “ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት” እንዳጋጠማቸው ጠቅሶ በሰሜናዊ የጋዛ ክፍል በግንቦት ወር ረሃብ ያጋጥማል ያለ ሲሆን በጋዛ ያለውን ሁኔታም “እጅግ አስከፊ” ሲል ገልጾታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካሁን በጋዛ 27 ሕጻናትን ጨምሮ 31 ሰዎች በምግብ እጥረት እና በውሃ ጥማት ለሕልፈት ተዳርገዋል ይላል።

ፍርድ ቤቱ እስራኤል አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ አገልግሎት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ጋዛ በፍጥነት እንዲደርስ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ሙሉ ትብብር እና አስፈላጊ የሆኑ እርምጃ መውሰድ አለባት ብሏል።

ተመድ መድሃኒት፣ ምግብ፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ነዳጅ፣ መጠለያ፣ አልባሳት እና የንጽህና መጠበቂያ በጋዛ በፍጥነት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ቁሶች ናቸው ሲል ዘርዝሯል።

ፍርድ ቤቱ ጨምሮም የእስራኤል ሠራዊት አባላት በፍልስጤማውያን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጽሙ እስራኤል የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባት ብሏል።

በቅርብ ወራት የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሸከርካሪዎች ግብጽ ድንበር ላይ ረዥም ሰልፍ ሰርተው የታዩ ሲሆን እርዳታው ጋዛ እንዳይደርስ እስራኤል እክል እየሆነች ነው የሚል ክስ እየተሰማ ይገኛል።

እስራኤል በበኩሏ ለሰላማዊ ሰዎች ተብሎ የሚገባው አብዛኛው እርዳታ ለሐማስ የሚደርስ ነው ትላለች።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ በአየር እና በመድር ጦር የታገዘ ድብደባ ስትፈጽም ቆይታለች።

በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚኒስቴር በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ32ሺህ 500 መሻገሩን ይገልጻል።