የእስራኤል ቀኝ አክራሪ ሚኒስትር በአል አቅሳ መስጊድ ግቢ ውስጥ መጸለያቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

የእስራኤል ቀኝ አክራሪ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር

የፎቶው ባለመብት, Itamar Ben-Gvir X account

የእስራኤል ቀኝ አክራሪ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር በእየሩሳሌም አል አቅሳ መስጊድ ግቢ ውስጥ የአይሁዳውያንን ጸሎት ሲመሩ መታየታቸው ቁጣን ቀሰቀሰ።

በዚህ መስጊድ ግቢ መጸለይ የሚችሉት የእስልምና እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ከአስርት ዓመታት በፊት መግባቢያ የተደረሰ ሲሆን ሚኒስትሩ በዚህ ተግባራቸው ይህንን መጣሳቸው ተገልጿል።

እስራኤል በወረራ በያዘቻት ምስራቅ ኢየሩሳሌም በሚገኘው እና አይሁዳውያን ቴምፕል ተራራ ብለው በሚጠሩት ስፍራ ቤን ግቪር የአይሁዳውያንን ጸሎት ሲመሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ወጥተዋል።

ከአስርት ዓመታት በፊት በተደረሰው መግባቢያ መሰረት አይሁዳውያን ስፍራውን መጎብኘት ቢችሉም መጸለይን ይከለክላል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በስፍራው የእስልምና አምልኮትን ብቻ የሚፈቅደው ነባራዊ ስምምነት ላይ እስራኤል ምንም አይነት የፖሊሲ ለውጥ አላደረገችም ብሏል።

ስፍራውን በበላይነት የምትጠብቀው ዮርዳኖስ ቤን ግቪር በስፍራው ያደረጉት ጉብኝት "ተቀባይነት የሌለው ትንኮሳ ነው" ስትል አውግዛለች።

ሐማስ በበኩሉ "በፍልስጤማውያን ህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትን ጥልቀት" የሚያሳይ ያለ ሲሆን የፍልስጤም አስተዳደር ቃለ አቀባይ ማህሙድ አባባስ የቀኝ አክራሪው ሚኒስትር ጉብኝት "ቀይ መስመሮችን ያለፈ ነው" ብለዋል።

ስፍራው በመጽሀፍ ቅዱስ የተጠቀሱ የሁለት ቤተመቅደሶች መገኛ ነው በሚል አይሁዳውያን የተቀደሰ ስፍራ ይሉታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለሙስሊሞች ደግሞ ነቢዩ መሐመድ ወደ ሰማይ ያረገበት ቦታ ነው ብለው ሰለሚያምኑ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ ስፍራ ይታያል።

በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እስራኤል ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ከዮርዳኖስ በመውሰድ በወረራ ተቆጣጥራለች።

ዮርዳኖስ የስፍራው ጠባቂ በመሆን ታሪካዊ ሚናዋን እንድትቀጥል እንዲሁም እስራኤል የጸጥታ እና ተደራሽነትን እንድትቆጣጠር መግባባት አለ።

እስራኤል ይህንን መግባባት ሆን ብላ ለመጣስ እየሞከረች ነው ሲሉ ፍልስጤማውያን የሚወቅሱ ሲሆን በቅርብ ዓመታት ፖሊስ ሳይከለክላቸው አይሁዳውያን ጎብኝዎች ሲጸልዩ መታየት ቀጥሏል።

ቦታውን የሚያስተዳደረው የእስላሚክ ኢንዶወመንት ድርጅት ዋቅፍ እሁድ ዕለት ወደ መስጊዱ ግቢ የመጡት ሚኒስትሩን ጨምሮ 1 ሺህ 250 አይሁዳውያን መሆናቸውን አስታውቋል።

ፖሊስን በበላይነት የሚመሩት የአገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት ሚኒስትር ጽንፈኛው ቤን ጊቭር ከዚሀ ቀደም ስፍራውን ቢጎበኙም በይፋ ጸሎት ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።

ሚኒስትሩ ወደ መስጊዱ ሲገቡ እና ሲዞሩ በፖሊስ ታጅበው ነበር።

ቀኝ አክራሪው በስፍራው ላይ ሆነው ባደረጉት ንግግር ታጋቾችን በተመለከተ እንዲሁም እስራኤል መላውን ጋዛ ተቆጣጥራ ፍልስጤማውያን ከስፍራው "በፈቃዳቸው እንዲፈናቀሉ" የሚደረግበት መንገድ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሩ የሚሉት ሰላማውያን ዜጎችን በግዳጅ ማፈናቀል እንደሚቆጠር የጦር ወንጀልም ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

እስራኤል በወረራ በተቆጣጠረቻት ዌስት ባንክ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ "ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በማስነሳት" ሚኒስትሩ በዩናይትድ ኪንግደም ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የአል አቅሳ መስጊድ

የፎቶው ባለመብት, Gazi Samad/Anadolu via Getty Images

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።