ኪሊያን ምባፔ ከፒኤስጅ የእስያ የቅድመ ውድድር ጨዋታ ጉዞ ውጭ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳዩ የእግር ኳስ ቡድን ፓሪስ ሴይንት ጄርሜን የቅድመ ውድድር ጨዋታውን በእስያ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያደርጋል። ነገር ግን የቡድኑን ጉምቱ ተጫዋች ኬሊያን ምባፔን የጉዞው አካል አላደረገውም።
በመሆኑም ፒኤስጅ ምባፔን በሚቀጥለው ዓመት በነጻ ከማሰናበት ይልቅ በአሁኑ ወቅት ዳጎስ ባለ ገንዘብ በመሸጥ ካዝናውን መሙላት ይፈልጋል።
በእርግጥ ምባፔ አሁን ያለው ኮንትራት እስከሚጠናቀቅበት የሚቀጥለው ዓመት የውድድር መጨረሻ ድረስ ከፒኤስጅ ጋር መቆየት እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ተናግሯል። በውድድር ዘመኑ መጨረሻም በነጻ ሪያል ማድሪድን ለመቀላቀል እንዳቀደ በስፋት ይወራል።
ፈረንሳያዊው የፊት መስመር ተጫዋች በፈረንጆቹ 2017 በ165.7 ሚሊዮን ፓውንድ ፒኤስጅን በመቀላቀል የክለቡ የምንጊዜም ሁለተኛው ውድ ፈራሚ ነው።
የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ኪሊያን ምባፔ ሞናኮን ከተቀላቀለ ጊዜ ጀምሮ በ260 ጨዋታዎች 212 ግቦችን አስቆጥሯል።
ፒኤስጅ አሁን ያለው ሁኔታ ምባፔን የቡድኑ አካል አድረጎ ወደ እስያ መጓዙ አሳማኝ ባለመሆኑ ፓሪስ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግን ወስኗል።
የቡድኑ ሊቀመንበር ናስር አል-ከላፊ “የማይሆን ነው” በማለት በምባፔ ጉዳይ ያላቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል። ምባፔን በ2024 በነጻ ማሰናበት የማይታሰብ ነው ብለዋል።
ምባፔን ፒኤስጅ በዚህ ክረምት ሊሸጠው እንደሚችል ብዙ የእእር ኳስ ቡድኖች ሲያጠያይቁ ቆይተዋል። ነገር ግን ምባፔ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት መጨረሻ ሪያል ማድሪድን የመቀላቀል ፍላጎት ስላለው በዚህ ዓመት ከሌላ ቡድን የሚቀርብለትን ጥያቄ ላይቀበል ይችላል።
ፒኤስጅ ባለፈው ዓመት የፈረንሳይ ሊግ 1ን ቢያሸንፍም ከሻምፒዮንስ ሊግ ግን ሩብ ፍጻሜ ሳይደርስ በባየርን ሙኒክ ተሸንፎ ተሰናብቷል።
የፒኤስጅ አሰልጣኝ ክሪስቶፍ ጋልቴር ተሰናብተው የቀድሞው የባርሴሎና እና የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬ ተተክተዋል።
ሌላኛው የፒኤስጅ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በዚህ የውድድር ዓመት መጨረሻ ከቡድኑ ተሰናብቷል። በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የምባፔን አገር ፈረንሳይን በማሸነፍ የዓለም ዋንጫን ከፍ ያደረገው አርጄነቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ፣ ወደ አሜሪካ ተጉዞ ኢንተር ሚያሚን ተቀላቅሏል።












