በቦረና ዞን 5 ልጆች ያሏት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆችን ወለደች

የፎቶው ባለመብት, Kominikeeshinii Aanaa Taltallee
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ ወ/ሮ ቡካዩ ዱለቻ የተባለች እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆችን ማክሰኞ ሰኔ 11/2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ መውለዷ ተነገረ።
የተልተሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ኃላፊ አቶ ሶራ ሸሬ እና ቀዶ ህክምናውን ያከናወኑት የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ብርሃኑ በቀለ ወ/ሮ ቡካዩ 50 ደቂቃ በፈጀ “አፕራሲዮን” ሁለት ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆችን በአንድ ጊዜ መውለዷን ተናግረዋል።
የእናትየው ሆድ እጅግ እየገፋ በመሄዱ ለደኅንነቷ ሲባል በ35ኛ ሳምንታቸው ህጻናቱ እንዲወለዱ መደረጋቸውም ተጠቁሟል።
የቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ አዳ ቀበሌ ነዋሪዋ እናት ወ/ሮ ቡካዩ ቀደም ሲል የ15፣ የ13፣ የ10፣ የ5 እና የ3 ዓመት የሆኑ ሦስቱ ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ልጆች አላት።
ቀደም ያሉት አምስቱም ልጆቻቸው ቤት ውስጥ እንደተወለዱ ለቢቢሲ የገለጸችው ወ/ሮ ቡካዩ፣ የመጨረሻው እርግዝናዋ ግን ከሌሎቹ የተለየ እንደነበር ተናግራለች።
“ሌሎች እርግዝናዎች ላይ ምንም ችግር አልነበረብኝም። ይኼኛው እርግዝና ግን ከበዶኝ ነበር። ሁለተኛ ወሬ ላይ ስደርስ ነበር ከመሬት መነሳት ያቅተኝ፣ ይደክመኝ ነበር” ብላለች።
ይህንን በቀዶ ህክምና የተደረገ ወሊድ የመሩት ዶክተር ብርሃኑ በቀለ እናት እና የተወለዱት አራት ህጸናት “በሙሉ ጤንነት” ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Kominikeeshinii Aanaa Taltallee
በመጀመሪያ ከማህጸን የወጡት 2 ሴቶች ሲሆኑ፣ ቀጥሎ ሁለቱ ወንዶች እንደተወለዱም ዶክተር በቀለ አስረድተዋል።
ጨምረውም ሁለቱ ወንዶች በአንድ የእንግዴ ልጅ የተቀሩት ደግሞ በሌላ የእንግዴ ልጅ በጋራ እንደነበሩ አንስተዋል። ሁለቱ ሴቶች እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ግራም ሲመዝኑ፣ ወንዶቹ 2.1 እና 2.2 ኪሎ ግራም እንዳላቸውም ሐኪሙ ተናግረዋል።
ዶክተር ብርሃኑ እናትየው የመጀመሪያውን የቅድመ ወሊድ ምርመራ ያደረገችው በአምስተኛ ወሯ እንደነበር እና አራት ልጆችን እንዳረዘች ያወቀችውም በዚያ ወቅት መሆኑን አመልክተዋል።
የተልተሌ ሆስፒታል ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ብርሃኑ በቀለም ባለፈው ዓመት ነበር በዚህ ‘ስፔሻሊቲ’ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁት።
“ሦስት እንጂ፣ አራት ልጆች [ያረገዘች ሴት] አጋጥሞኝ አያወቅም። አራት ልጆች ተወለዱ ሲባል የሰማሁት ራሱ አንዴ ነው” ብለዋል።
“በእርግዝና ወቅት ምንም ችግር አልነበረም ሆዷ በጣም አድጎ ነበር። ድካምም ነበራት። አሁን ህጻናቱም እናትም ሰላም ናቸው። ጡት ይጠባሉ ግን ሰለማይበቃቸው ተጨማሪ ፎርሙላ [የጨቅላ ህጻናት የዱቄት] ወተት እየተጠቀሙ ነው” ሲሉም አክለዋል።
“አራት ልጆች እንዳረገዝኩ ሳውቅ በጣም ነው ደስ ያለኝ” የምትለው እናት፣ ቢሆንም “አሁን ሁለት ልጆች እንኳን ማሳደግ አስቸጋሪ ነው። ብዙም ብር የለኝም። ሀብታም አይደለሁም እንዴት ነው የሚያደጉት ብዬ አስባለሁ” ሲሉ የወደፊቱ እንደሚያሳስባት እናት ገልጻለች።
ከአንድ በላይ ልጆች የመጸነስ ዕድል
ቢቢሲ ከአንድ በላይ ጽንስ የሚፈጠርበትን ሁኔታ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ያናገራቸው ዶ/ር ፀጋዬ ተስፋዬ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶችን በማጣቀስ ጉዳዩ ተፈጥሯዊ መሆኑን ገልፀው፣ ብዙ የመውለድ ዕድሉ ግን በሁኔታዎች የተወሰነ መሆኑን ያስረዳሉ።
“ሁለት መንታ ልጆችን የመጸነስ ዕድል በአማካኝ ከ250 እርግዝና በአንዱ ይከሰታል። ሦስት ጽንስ በአንድ ጊዜ የመፈጠር ዕድል ደግሞ ከ10 ሺህ እርግዝናዎች በአንዱ የመከሰት ዕድል አለው” ይላሉ።
ከሦስት በላይ ጽንስ የመፈጠር ዕድል እያነሰ እንደሚሄድ የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ አራት ልጆች የመጸነስ ዕድል የሚፈጠረው ከ700 ሺህ እርግዝናዎች በአንዱ ነው ብለዋል።
በአንድ ጊዜ ብዙ ልጆችን የመፀነስ (Multiple Pregnancy) በዋነኛነት ሁለት ዘርፎች አሉት።
ተመሳሳይ መንትያዎች (Identical twins) እና ወይንም የማይመሳሰሉ (Fraternal twins) የሚባሉት ማለት ነው።
የተመሳሳይ መንትያዎች እርግዝና ከ2 ሚሊየን እርግዝናዎች አንድ ብቻ ነው የሚገጥመው።
በዓለም ላይ የሰው ልጅ በአንድ ጊዜ ምን ያህል ልጆችን ይወልዳል በሚለው ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ ሃሳብ የለም።
የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት የሆኑት ዶ/ር ደምሰው አመኑ፣ አንዲት ሴት በአንድ ጊዜ ሊኖራት የሚችለው የልጆች ቁጥር ይህ ሊሆን ይችላል ተብሎ በጥናት የተቀመጠ ነገር የለም ሲሉ ከዚህ በፊት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።












