በደቡብ አፍሪካ በተፈጸመ የጅምላ ተኩስ ቢያንስ 11 ሰዎች ተገደሉ

ደቡብ አፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በደቡብ አፍሪካ በተፈጸመ የጅምላ ተኩስ የሦስት ዓመት ሕጻንን ጨምሮ ቢያንስ 11 ሰዎች ተገደሉ።

ትናንት ጠዋት በሱልስቪል አካባቢ በሚገኝ የእንግዶች ማረፊያ በተከፈተው ተኩስ 14 ሰዎች ተጎድተዋል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ብርጋድየር አታሌንዳ ማቴ እንዳሉት ሰዎች ተሰባስበው እየጠጡ ሳለ ማንነታቸው ያልታወቀ ሦስት ታጣቂዎች "በድንገት" ተኩስ ከፍተዋል።

ተኩሱን የጀመሩበት ምክንያት አልታወቀም። እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰውም የለም።

የወንጀል መበራከት በሚፈትናት ደቡብ አፍሪካ በቅርብ ጊዜ ከተፈጸሙ የጅምላ ተኩሶች መካከል ይጠቀሳል።

በእንግዳ ማረፊያ ወንዶች እየጠጡ ሳለ ታጣቂዎቹ በድንገት ደርሰው መተኮስ እንደጀመሩ ተገልጿል።

ከተገደሉት ሰዎች መካከል የ12 ዓመት ወንድ እና የ16 ዓመት ሴት ይገኙበታል።

የፖሊስ ቃል አቀባይዋ "25 ሰዎች እንደተተኮሰባቸው አረጋግጫለሁ" ብለዋል።

"መጠጥ ቤቱ ሕገ ወጥ ነበር። ሕገ ወጥ እና ፈቃድ አልባ መጠጥ ቤቶች አስቸጋሪ ሆነዋል" ሲሉም አክለዋል።

የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ኤስኤቢሲ እንደዘገበው በተኩሱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎችም ሰለባ ሆነዋል።

ከሚያዝያ እስከ መስከረም ባሉት ወራት 12,000 መጠጥ ቤቶች መዘጋታቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ከ18,000 በላይ ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ደቡብ አፍሪካ ግድያ ከሚፈጸምባቸው አገራት በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።

የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕፅ እና ወንጀል ክፍል አሐዝ እንደሚያሳየው፤ እአአ ከ2023 እስከ 2024 ድረስ ከ100,000 ሰዎች መካከል 45ቱ ይገደላሉ።

ከሚያዝያ እስከ መስከረም ድረስ በየቀኑ 63 ሰዎች መገደላቸውን የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል።