የትራምፕ በቡድን 20 አገራት ስብሰባ አለመገኘት ለደቡብ አፍሪካ ጎልቶ የመታያ ዕድል ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images
ደቡብ አፍሪካ በባለፈው ዓመት የቡድን 20ን ፕሬዝዳንትነትን የተቀበለችው፤ ታዳጊ አገራትን የሚፈትኑ ጉዳዮች የመሪዎቹ የስብሰባ አጀንዳ እንዲሆኑ የማድረግ ተስፋን ሰንቃ ነው።
በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን ስብሰባ የምታዘጋጀው ደቡብ አፍሪካ፤ የዓለማችን ከፍተኛ ኢኮኖሚ ባለቤት ለሆኑት የቡድን 20 አገራት መሪዎች ልታቀርብ ከምትችላቸው ጉዳዮች አንዱ ብድር ነው።
በኢኮኖሚ ከላቁ አገራት ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እስከ አራት እጥፍ ከፍተኛ ወለድ ለሚከፍሉት ታዳጊ አገራት የሚቀርበው ብድር በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ መቅረብ አለበት የሚለውን መከራከሪያ ለመሪዎቹ የማቅረብ ፍላጎት አላት።
የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት፣ በባለ ብዙ ወገን መድረኮች ላይ በአፍሪካ አገራትን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም ውድ ለሆኑ ማዕድኖቻቸው የተሻለ የሚባለውን ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ ዛሬ ኅዳር 13 እና ነገ ሕዳር 14/2018 ዓ.ም. የሚካሄደው ስብሰባ አጀንዳዎች ናቸው።
እስካሁን ድረስ ግን ከስብሰባው ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ የሆነው ነጥብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስብሰባ ላይ ላለመገኘት መወሰናቸው ነው።
ፕሬዝዳንቱ ስብሰባው ላይ ለመገኘት በምክንያትነት የጠቀሱት በሰፊው ውድቅ የተደረገውን የደቡብ አፍሪካ ነጮች ጉዳይ ነው። ትራምፕ በቁጥር ትንሽ የሆኑት ነጮች በከፍተኛ መጠን እየተገደሉ እና መሬታቸው እየተቀማ ነው ይላሉ።
ይህ ጉዳይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻክር አደርጓል። አሜሪካ በዋሽንግተን የነበሩትን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር አባርራለች።
ለአገሪቱ ከምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ የተወሰነውን ቀንሳለች። ከዚህም ባሻገር ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ላይ ከተጣሉ ታሪፎች መካከል ከፍተኛ የሆነው የ30 በመቶ ቀረጥ ደቡብ አፍሪካ ላይ ጭናለች።
ትራምፕ መጀመሪያ የተናገሩት በእሳቸው ምትክ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ እንደሚገኙ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት ግን አንድም የአሜሪካ ተወካይ በቡድን 20 ስብሰባ ላይ እንደማይሳተፍ አስታውቀዋል።
የአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአሜሪካ የሚቀርብበትን ውንጀላ በተመለከተ የመለሰው የዲፕሎማሲያዊ አነጋገርን በጠበቀ የተጋፋጭነት አቋም ነበር። በነጮች ላይ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው የሚለውን ክስ በጽኑ ውድቅ ያደረገው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፤ አሜሪካ ተሳተፈችም አልተሳተፈች ስብሰባው እንደሚካሄድ ገልጿል።
የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ሊካሄድ 48 ሰዓታት ሲቀሩት አሜሪካ በድንገት አቋሟን መቀየሯን አስታወቀች። የአሜሪካ መንግሥት፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ዲፕሎማቶች የተውጣጣ እና አነስተኛ ቁጥር ያለው ቡድን በጂ20 ቀጣይ ፕሬዝዳንት ርክክብ ላይ እንደሚሳተፉ ገልጿል። ይህም ቡድን ቢሆን ግን በአባል አገራቱ ስብሰባ ላይ እንደማይሳተፍ ተናግሯል።
ሁለቱም አገራት መካረራቸውን ለማርገብ ማቀዳቸውን የሚያሳይ ምንም ምልክት አለመኖሩን ተከትሎ፤ አሜሪካ በቀጣይ ዓመት በምታዘጋጀው የቡድን 20 ስብሰባ ላይ የደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማቶች እንዳይሳተፉ ሊከለከሉ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
የደቡብ አፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትር ኤኖክ ጎዶንግዋና በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አገራቸው በቀጣዩ የቡድን 20 ስብሰባ ላይ ልትሳተፍ የማትችለው በአንድ ምክንያት እንደሚሆን ተናግረዋል።
"የቡድን 20 አባል ነን፣ ተጋባዥ አገር አይደለንም። ስለዚህ ከማንም ግብዣ እንዲቀርብልን አንፈልግም" ብለዋል።
"አሜሪካ እንድንሳተፍ የማትፈልግ ከሆነ ይህንን ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ ቪዛ መከልከል ነው" ሲሉ አገራቸው የቀጣዩን ዓመት ስብሰባ የማትካፈልበት ሌላ ምክንያት እንደማይኖር አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እና ደቡብ አፍሪካ የዓለማችን ሀብታም አገር ባልተገኘችበት ሁኔታ ግቧን ማሳካት ትችላለች?
የ'ኬምብሪጅ ኢንስቲትዩት ፎር ሰስቴነብሊቲ ሊደርሺፕ' ፕሮፌሰሩ ሪቻርድ ካላንድ ትችላለች ባይ ናቸው።
"በትክክል አዕምሯቸውን እየተጠቀሙ ያሉ ሰዎች ለ[አሜሪካ አለመኖር] ብዙ ክብደት የሚሰጡ አይመስለኝም" ይላሉ።
"የሚያስገርመው፤ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አለመኖር እውነተኛ መግባባት እንዲኖር የበለጠ ክፍት ቦታ ይፈጥራል። ምክንያቱም ሰዎች በየጊዜው ወደ ትከሻቸው ዘወር እያሉ እርሱን አይመለከቱም፤ ባህሪ እና አቋሙንም ለመገመት እና ለመመርመር አይሞክሩም" በማለት ያስረዳሉ።
በፕሮፌሰሩ ሪቻርድ ካላንድ ትንተና መሠረት፤ የአሜሪካ አለመኖር መካከለኛ ኃይል ያላቸው አገራት ከፍ እንዲሉ ያደርጋል። እንዲሁም የጋራ መግለጫ በማውጣት የሚፈልጉትን የለውጥ አጀንዳ ወደፊት መግፋት ይችላሉ።
ሰኞ ዕለት በጆሃንስበርግ በሚገኘው የስብሰባው አዳራሽ ለጋዜጠኞች ምላሽ የሰጡት የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላም ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። ሚኒስትሩ፤ "[አሜሪካ] ቀርታለች፤ ስለዚህ እነሱ በሌሉበት፣ የተገኙት አገራት ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው" ብለዋል።
"ተቋሙ በሌለ አካል የተነሳ ወደ ኋላ መጎተት ስለማይችል፤ የመሪዎች የስምምነት መግለጫ እንድናጸድቅ የሚሳተፉ አገራትን ለማሳመን ወደፊት እየገፋን ነው" ሲሉም አቋማቸውን በይፋ አብራርተዋል።
የመሪዎች ስምምነት መግለጫ የሚባለው፤ አገራት የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ በሚያደርጉ ጉዳዮችን በተመለከተ ስምምነት ለመድረስ የሚያከናውኑት የዓመታት ስራ የመጨረሻ ምዕራፍ ነው።
ንግድን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን የሚኖሩ እንቅፋቶች፣ የቴክኖሎጂ እድገቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቃሽ የድርድር ነጥቦች ናቸው። ስምምነት መግለጫው እነዚህ ጉዳዮች በተመለከተ አገራት እርምጃ ለመውሰድ የተስማሙባቸውን ነጥቦች ይዘረዝራል።
በዘንድሮው ስብሰባ ላይ ግን የማይገኙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብቻ አይደሉም። የቻይናው ዢ ሺፒንግም በምትካቸው የሚልኩት በዚህ ዓመት በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ አገሪቱን እየወከሉ ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ቺያንግን ነው።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በወጣባቸው የእስር ማዘዣ ምክንያት አይሳተፉም። የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባውምም በስብሰባው ላይ የማይገኙ ሌላኛዋ መሪ ናቸው።
የትራምፕ አጋር የሆኑት የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ዣቪየር ሚሌም በበኩላቸው ለአሜሪካ አጋርነታቸውን ለማሳየት በሚል በስብሰበው ከመሳተፍ ተቆጥበዋል።
ይሁን እንጂ እነዚሁ መሪዎች በሙሉ ከአሜሪካ ተቃራኒ በሆነ መልኩ አገራቸውን አቋም የሚወክሉ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን ይልካሉ።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላሞላ የመሪዎቹ አለመሳተፍ የሚሰጠውን ቦታ አጣጥለው አቅረበውታል። አንዳንድ ጊዜ የአገራቲ መሪዎች ዋና ኹነቶችን መሳተፍ እንደማይችሉ እና ይህም "ያልተለመደ አለመሆኑን" ገልጸዋል። ተተኪዎችን እንደሚልኩም አክለዋል።
ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ሌሎች የዓለም ኃያላን ደቡብ አፍሪካ ስብሰባውን ለማዘጋጀት የተረከበችውን የመሪነት ሚና ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ወሳኝ ማዕድናትን ለማውጣት እና በአገር ውስጥ እሴት ለመጨመር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
የአፍሪካ አገራት የሚያወጧቸውን ማዕድናት በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምረው ለገበያ ማቅረብ ቢችሉ ለኢኮኖሚ እድገታቸው ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚኖረው ሲከራከሩ ቆይተዋል። ይህ ሂደት የሚፈጥረው የኢኮኖሚ እድገት አገራቱ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸውን እድገት፣ የስራ እድል እና ገቢ እንደሚያመጣ ያስረዳሉ።
ደቡብ አፍሪካ፤ በተለያዩ የሚኒስትሮች ስብሰባዎች እና ኮሚቴዎች ላይ እንደዚህ ዓይነት ሀሳቦችን ለዓመታት ስታነሳ ቆይታለች።
በዚህኛው ዙር፤ የቡድን 20 ስብሰባን በማስተናገድ የመጨረሻዋ አገር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ፤ ይህንን ኃላፊነት በሰሜኑ እና በደቡቡ የዓለም ክፍል መካከል ያለውን የዕድገት ልዩነት ለማጥበብ እንደምትጠቀምበት አስታውቃለች።
የአገሪቱ መንግሥት የፍትሐዊነት፣ የዘላቂነት እና የጋራ ብልጽና አጀንዳዎችን ወደፊት መግፋት ይፈልጋል።
በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ፤ ምንም እንኳ እንደ ቡድን 20 ባሉ ባለ ብዙ ወገን ተቋማት አማካኝነት ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ይህ ዓይነቱ ጥምረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ ፕሮፌሰር ካላንድ ይናገራሉ።
"በምድር ላይ ያለው የሰው ልጅ ሕይወት የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሥነ ሕዝብ ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ አብዮት እና በመሳሰሉት ጉዳዮች የኅልውና ተግዳሮት እያጋጠመው ነው። እነዚህ ሁሉ ለሰው ልጅ በጣም ከባድ የሆኑ ጫናዎች ናቸው። ዓለም አቀፍ ቅንጅት እና ትብብር ከሌለ እነዚህን ተግዳሮቶች መቋቋም አይቻልም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ደጋፊዎቻቸው፤ ባለ ብዙ ወገን ተቋማት በትክክል የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ ያላቸው አስተዋጾ አነስተኛ እንደሆነ ይከራከራሉ። ከእነዚህ ተቋማት ይልቅ በሁለት አገራት መካከል የሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ይመርጣሉ።
ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ታዳጊ አገራት እንደ ለድሃ አገራት የብድር ዋጋን መቀነስ ያሉ ጉዳዮች እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ስምምነት እንደሚጠይቅ በመግለጽ ይከራከራሉ። አንድ ለአንድ በሚደረሱ ስምምነቶች ይህንን ማሳከት እንደማይቻልም ያስረዳሉ።
በብዙ መልኩ ሲታይ የደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 ፕሬዝዳንትነት፤ ስለ ባለ ብዙ ተቋማት እና ውጤታማነታቸው የሚደረገው ሰፊ ክርክር አንድ አካል ነው።
ደቡብ አፍሪካ ነገ እሁድ የቡድን 20 አገራት የጋራ የስምምነት መግለጫ እንዲያወጡ ማሳመን ከቻለች፤ የዓለም ኃያሏ አገር ሳትገኝ እንኳ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል።















