ቡድን 20 ታሪካዊ በተባለ ውሳኔ የአፍሪካ ኅብረትን አባል አድርጎ ተቀበለ

የአፍሪካ ኅብረት ቡድን 20ን መቀላቀሉ ይፋ ሲደረግ

የፎቶው ባለመብት, MEA/X

ቡድን 20 ታሪካዊ በተባለ ውሳኔ የአፍሪካ ኅብረትን አባል አድርጎ ተቀበለ።

በኢንዱስትሪ የበለጸጉ እና ከአዳጊ አገራት የላቀ የምጣኔ ኃብት ዕመርታ ያስመዘገቡት አገራት ስብስብ የሆነው ቡድን ሃያ አባላትም ውሳኔ ታሪካዊ ተሰኝቷል።

55 አባላት ያሉት የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 (G20) አባል አገራትን ተቀላቅሏል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ የአፍሪካ ኅብረትን አዲስ የቡድን 20 ቋሚ አባል አድርገው ሲያስተዋውቁ አንደኛው ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው አፍሪካን በአንድ ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ ማካተት ነው።

ሕንድ የቡድን 20 መሪነቷ የዓለምን ደቡባዊ አገራት ተሳትፎ ከማሳደግ ጋር የተያያዘ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የዚህ ዕቅድ ትልቁ አካል ደግሞ የአፍሪካ ኅብረትን የቡድኑ አባል ማድረግ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕንድ የቡድን 20 መሪ በሆነችበት በዚህ ወቅት ከአፍሪካ አገራት በርካታ ተሳታፊዎች መገኘታቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

ሞዲ የአፍሪካ ኅብረትን በቡድኑ መቀላቀል ሲገልጹ አጠገባቸው የነበሩ የአፍሪካ ተወካዮች ደስታቸውን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ፕሬዝዳንት አዚል አሶሚኒ በቡድን 20 የፓርላማ አባላት መቀመጫ እንዲወስዱም በሞዲ ተጋብዘዋል።

ሁለቱ መሪዎች ዜናው ይፋ ከተደረገ በኋላ ተቃቅፈውም ታይተዋል።

ተወካዮቹ “ታሪክ ተሠርቷል” ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት በቡድን 20 መቀላቀል ቡድኑን የተሻለ አካታች እንደሚያደርገው ተገልጿል።

ሕንድ በጉባኤው እንዲነሳ ከምትፈልገው ርዕሰ ጉዳይ አንዱ የታዳጊ አገራት ምጣኔ ሀብት ነው።

በርካታ ታዳጊ አገራት ከቻይና፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈት ስለሚከብዳቸው ሕንድ ሃብታም አገራት እንዲያግዙ ትሻለች።

በቡድን 20 አገራት ጉባኤ ላይ ከሚነሱ ነጥቦች አንዱ የዩክሬን ጉዳይ የነበረ ሲሆን፣ ቢቢሲ ይፀድቃሉ ከተባሉ ሰነዶች መካከል የተመለከተው ሰነድ እንደሚጠቁመው ስለ ዩክሬን እስካሁን የተጠቀሰ ነገር የለም።

ሰነቡ የባንክ ዘርፍን ማሻሻልና ክሪፕቶከረንሲን መቆጣጠር ጨምሮ ሌሎችም ነጥቦችን ያካተተ ነው።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎ የብሪክስ ስብሰባ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።

የእስር ማዘዣው ከመውጣቱ በፊት አምና በቡድን 20 አገራት ጉባኤ ላይ በባሊ አልተገኙም።

በሌላ በኩል የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕንድን ‘ባሐራት’ በሚል ስም መጥራታቸው ውዝግብ ፈጥሯል። አገሪቷ ስሟን በይፋ ስለመቀየሯ እስካሁን የተባለ ነገር ግን የለም።

ሌላው በጉባኤው የሚነሳው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ነው። ታዳጊ አገራት የበለጠ ተጎጂ ስለሚሆኑ ካደጉ አገራት አንዳች መተማመኛ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሲገለጽ ቆይቷል።

የመጀመሪያው የቡድኑ ውይይት አንድ ምድር ወይም 'One Earth' የሚባል ሲሆን የአካባቢ ጉዳይን የተመለከተ ይሆናል።

ታዳጊ አጋራት በሕንድ ተወክለው በሚካሄደው ውይይት ሃብታም አገራት የካርበን ልቀትን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በገንዘብ፣ ቴክኖሎጂና መሠረተ ልማት እንዲደግፉ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

ቡድን 20 ጉባኤ በሕንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images