ሰር ጂም ራትክሊፍ ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት ከፍተኛውን ዋጋ አቀረቡ

ሰር ጂም ራትክሊፍ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ሰር ጂም ራትክሊፍ

የማንችስተር ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብን ለመግዛት የሰር ጂም ራትክሊፍ ኢኒየስ ግሩፕ ከኳታሩ ሺክ ጃስሚን የበለጠ የጨረታ ዋጋ ማቅረቡ ተነገረ።

ቡድኑን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጨረታ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ስፖርት እንዳረጋገጡት ኢኒየስ ግሩፕ ከፍተኛውን ገንዘብ አቅርቧል።

የኳታሩ የባንክ ባለሀብት ሼክ ጃስሚን ማንችስተር ዩናይትድን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቅለል አምስት ቢሊየን ፓወንድ ያቀረቡ ሲሆን፣ ብሪታኒያዊው የንግድ ሰው ራትክሊፍ ግን ቡድኑን ለመቆታጠር የሚያስችላቸውን ድርሻ ብቻ ነው ለመግዛት የፈለጉት።

ራትክሊፍ በግሌዘር ቤተሰቦች የተያዘውን 69 በመቶ የክለቡን ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት አላቸው ተብሎ የታሰበ ቢሆንም፣ አሁን ግን የግሌዘር ቤተሰቦች የተወሰነ የባሌቤትነት ድርሻ ይዘው እንዲቆዩ ፍላጎት አላቸው ተብሏል።

ቢሆንም ግን ጂም ራትክሊፍ በማንችስተር ዩናይትድ ባለቤትነት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ የሚያስገኝላቸውን ከ51 በመቶ በላዩን እንደሚይዙ ተነግሯል።

ራትክሊፍ ካቀረቡት ክፍያ አንጻር የግሌዘር ቤተሰቦች ቀጣዩን እርምጃቸውን ይወስናሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ማኅበር ግን ቡድኑ በተለያዩ ባለድርሻዎች ከመያዙ ይልቅ ሙሉ ለሙሉ ለሚገዛ አካል እንዲሸጥ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

ጂም ራትክሊፍ እና ሼክ ጃስሚን ማንችስተር ዩናይትድን በባለቤትነት ለመቆጣጠር የቀረቡ ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የክለቡ ባለቤት የግሌዘር ቤተሰብ ውሳኔያቸውን ለማሳወቅ የቀረቡላቸውን አማራጮች እየመረመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በሼክ ጃስሚን የቀረበውን ክፍያ እና ለአንድ ገዢ ቡድኑን የማስተላላፍ ሃሳብንም ከግምት ያስገባሉ ተብሏል።

በ2005 (እአአ) ማንችስተር ዩናይትድን የገዙት የግሌዘር ቤተሰቦች “ስትራቴጅክ አማራጮችን መፈለግ” በሚል ክለቡን ለመሸጥ ያቀረቡትን ሃሳብ ተከትሎ ነው ዋነኞቹ ገዢዎች ፍላጎታቸውን ገለጹት።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጉልህ ታሪክ ያለው እና በዘንድሮው የውድድር ዘመን አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት ባለሃብቶች ጥያቄያ አቅርበዋል።

ከእነዚህም መካከል ከኳታር ትልልቅ ባንኮች የአንደኛው ሊቀ መንበር የሆኑት ሼክ ጃስሚ ቢን ሃማድ አል ታኒ ፋውንዴሽናቸው ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቡን በተጨማሪ ከፍተና ገንዘብ አቅርቧል።

ብሪታኒያዊው ቢሊዮነር ሰር ራትክሊፍ ማንችስተር ዩናይትድን የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ቀደም ብለው ያሳወቁ ሲሆን፣ በተቋማቸው ኢኒዮስ በኩል ቡድኑን ለመግዛት አማራጮችን አቅርበዋል።

የኳታሩ ሼክ ጃሲም ክለቡን ወደ ቀድሞ ክብሩ የመመለስ ዕቅድ አለን በማለት ቡድኑን ቢገዙ ሊያደርጉ ያሰቡትን ገልጸዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑን ማጠናከር፣ የልምምድ ማዕከሉን ማስፋት፣ ስታዲየሙን ማዘመን እና ሰፊ መሠረተ ልማትን ማሟላት የሼክ ጃሲም ‘ናይን ቱ ፋውንዴሽን’ ትኩረት ከመሆኑ በተጨማሪ ካለዕዳ በቀጥታ ክፍያ ቡድኑን ለመግዛት መታሰቡ ተነግሯል።

ማንችስተር ተወልደው ያደጉት ራትክሊፍ ለክለቡ ባለቤትነት የአገሪቱ ዜጋ በመሆናቸው ተመራጭ ከመሆናቸውም በላይ “ማንችስተርን ወደ ማንችስተር ዩናይትድ የመመለስ ፍላጎት ይኖራቸዋል” የሚል ግንዛቤ አለ።

በ70 ዓመቱ ብሪታኒያዊ የሚመራው ኢኒዮስ ግሩፕ በስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የማፍሰስ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ የፈረንሳዩን ኒቼ እና የስዊድኑን ሉዛን ክለቦች በባለቤትነት ያስተዳድራል።

በሌሎች የስፖርት ዘርፎች በመሳተፍም ውጤታማ እንደሆነም ይነገራል።

በሌላ በኩል የዕድሜ ዘመን የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼክ ጃሲም፣ ኳታር ውስጥ የሚገኘው ኪውአይቢ ባንክ ሊቀ መንበር ሲሆኑ፣ የቀድሞው የኳታር ጠቅላይ ሚንስትር ልጅም ናቸው።