ዩክሬን ከአሜሪካ የረዥም ርቀት ሚሳኤል ሳታገኝ ቀረች

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ቶማሀውክ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤልን በተመለከተ ምንም ፍንጭ አልሰጡም።

ትራምፕ ለዩክሬን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሊሰጡ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።

ከዘለንስኪ ጋር ከተወያዩባቸው ነጥቦች አንዱ የዚህ መሣሪያ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን መሣሪያው ለዩክሬን እንዲሰጥ ስለመስማማታቸው ለማወቅ አልተቻለም።

ዘለንስኪ መሣሪያውን ያገኙ አይመስልም። ትራምፕ አሁን ላይ መሣሪያውን ለዩክሬን ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል።

በውይይታቸው ስለ ረዥም ርቀት ሚሳኤሎች መወያየታቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ሆኖም ግን "አሜሪካ ነገሮችን ማባባስ ስለማትፈልግ" መግለጫ ለመስጠት አልፈቀዱም።

ከውይይቱ በኋላ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው "ዩክሬን እና ሩሲያ ባሉበት ይቁሙ" ሲሉ ጦርነቱ እንዲገታ አሳስበዋል።

ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ከመወያየታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

በቅርቡ ሁለቱ መሪዎች ሀንጋሪ ወስጥ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዘለንስኪ፤ ቶማሀውክ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል እንዲሰጣቸው የሚፈልጉት የሩሲያን የኃይል አቅርቦት ለማዳከም ነው።

ትራምፕ መሣሪያው ለዩክሬን ሊሰጥ እንደሚችል ቢጠቁሙም፤ በዋይት ሀውሱ ውይይት በግልጽ ቃል አልገቡም።

ትራምፕ ሚሳኤል መላክ "ጦርነቱን ማባባስ ቢሆንም ጉዳዩ ለውይይት ክፍት ነው" ብለዋል።

"ቶማሀውክ ሳያስፈልግ ጦርነቱን በቅርቡ እናቆማለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር የተነጋገሩት ፑቲን ቶማሀውክ ለዩክሬን ሊላክ ይችላል የሚል ስጋት ስለተፈጠረባቸው እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ "ሚሳኤል ሊካክ ይችላል ብሎ መፍራት ጥሩ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

ዩክሬን ቶማሀውክ ከተሰጣት በምላሹ ለአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እንደምትሰጥ ዘለንስኪ ሲናገሩ ትራምፕ በፈገግታ ታጅበው አድምጠዋል።

ትራምፕ የጋዛን የሰላም ዕቅድ በማርቀቃቸው ዘለንስኪ አመስግነው፤ የዩክሬን እና ሩሲያን ጦርነትንም እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

ዘለንስኪ ከውይይቱ በኋላ "ስለ ቶማሀውክ መወራቱ ሩሲያን ያስፈራ ነው" ብለዋል።

ፑቲን ከትራምፕ ጋር ለመወያየት የጠየቁት ከረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሉ ጋር በተያያዘ መሆኑን እንደማያውቁም ገልጸዋል።

ዩክሬን መሣሪያውን ታገኝ እንደሆነ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ "የእውነት ይሆናል" ብለው መልሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለአውሮፓ መሪዎች ደውለው ከትራምፕ ጋር የተነጋገሩትን ገልጸዋል። "ቅድሚያ የሚሰጠው የሰዎችን ሕይወት ማዳን ነው። ዩክሬን ደኅንነቷ ተጠብቆ በመላው አውሮፓ የምንኖር ሰዎች ሰላም ማግኘት አለብን" ብለዋል።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እንዳሉት ከአውሮፓውያን መሪዎች ጋር የተደረገው የስልክ ውይይት "ውጤታማ" ነበር።

ዩኬ ለዩክሬን ሰብአዊ እርዳታ መላክ እንደምትቀጥልም አክለዋል።

ትራምፕ ለዩክሬን ቶማሀውክ የመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ቢጠቁሙም ፑቲን መሣሪያውን መለገስ የአሜሪካ እና ሩሲያን ወዳጅነት የበለጠ ያሻክራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን የስልክ ውይይት "ጥሩ ነበር" በማለት ገልጸውታል።

ፑቲን ከትራምፕ ጋር ሲገናኙ ዘለንስኪም ውይይቱን ይታደሙ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ "በመካከላቸው መቃቃር አለ፤ ሁሉም ሰው ምቾት እንዲሰማው እንፈልጋለን" ብለዋል።

የሦስትዮሽ ውይይት ሊደረግ ቢችልም ፊት ለፊት እንደማይገናኙ ጠቁመዋል።

ትራምፕ ያለፈው ነሐሴ በአላስካ ከፑቲን ጋር ሲገናኙ ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ተስፋ ቢያደርጉም፤ ውይይታቸው ያለ ውጤት ተቋጭቷል።

ከዚህ ውይይት ከሳምንታት በኋላ ትራምፕ ከአውሮፓ መሪዎች እና ከዘለንስኪ ጋር እያደረጉ የነበረውን ውይይት አቋርጠው ለፑቲን መደወላቸው ይታወሳል።