አሜሪካዊው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ እና ትራምፕን ያቃቃራቸው ምንድን ነው?

ወግ አጥባቂው ሄሴ ሮሜሮ በካቶሊክ ፖድካስት ፕሮግራሙ ቃላትን እየመረጠ ለአቡነ ሊዮ 14ኛ መልዕክት ያስተላልፋል።
"አቡኑ እንዴት ወደ ገነት መግባት እንዳለብን ይንገሩና" ይላል። "በመንግሥት ሥራ ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን የላቸውም። መስመራቸውን ቢጠብቁ ይሻላል።"
የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ የሆነው ሮሜሮ አሜራካዊው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን አቡን በቅርቡ ስደተኞችን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ተንገብግቧል።
ከአምስት አሜሪካዊያን አንዱ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደሆኑ ይገልፃሉ። ቤተ-ክርስትያኗ በአሜሪካዊያን የአኗኗር ዘይቤ እና ፖለቲካ ላይ ትልቅ ሚና አላት።
ካቶሊኮቹ ምክትል ፕሬዝደንቱ ጄዲ ቫንስ እና አክቲቪስቱ ሊዮናርዶ ሊዮ፤ ትራምፕ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እና የትምህርት ሚኒስትሯ ሊንዳ ማክማሆንን ጨምሮ ሌሎች በካቢኔው ቁልፍ ቦታ ያላቸው ሰዎች የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ናቸው።
ነገር ግን የስደተኞች ጉዳይ በቤተ-ክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች እና በትራምፕ አስተዳደር መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ምዕመናንም ተከፋፍለዋል።
ባለፈው ግንቦት የቤተ ክርስቲያኗ ካርዲናሎች በሊቃነ-ጳጰሳት አዳራሽ ተሰባስበው መሪያቸውን ሲመርጡ ሮሜሮ "እንደ ትራምፕ ያለ አቡን" ይመረጣል የሚል ተስፋ ነበረው።
አቡነ ሊዮ 14ኛ በተደጋጋሚ ስደተኞችን አሜሪካ ውስጥ የሚደርስባቸውን እንግልት አውግዘዋል። ባለፈው ኅዳር መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ "ራሱን እንዲመለከትም" ጥሪ አቅርበዋል።
ጳጳሱ ወንጌልን አጣቅሰው "ኢየሱስ በግልፅ እንደሚናገረው በስተመጨረሻው ወቅት ሁላችንም 'እንግዳ ያስተናገዳችሁት እንዴት ነው?' ተብለን እንጠየቃለን" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ አስተያየታቸው ከአንድ ሳምንት በኋላ የአሜሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ኮንፈረንስ ባወጣው ያልተለመደ እና "ልዩ መግለጫ" በአሜሪካ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ሁኔታ "እንዳሳሰበው" ገልጸዋል።
ጳጳሳቱ እየተፈጠረ ባለው "ፍርሀት እና መረበሽ" ደስተኛ እንዳልሆኑ አስታውቀው "ሰዎች በጅምላ ታፍሰው ከሀገር እንዲወጡ መደረጋቸውን" እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።
አክለው "የሰው ልጅን ዝቅ የሚያደርግ ንግግር እና ግጭት እንዲያበቃ" ፀሎት እናደርጋለን ብለዋል።
ኮንፈረንሱ መሰል መግለጫ ሲያወጡ በ12 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። መግለጫውን የደገፉት አቡኑ "በጣም አስፈላጊ" እና ሁሉም ካቶሊኮች እና "ቅን ልቡና ያላቸው ሰዎች በጥሞና እንዲያደምጡት" አሳስበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ እና የጳጳሱ መቃቃር
የፎርድሀም ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት እና ባሕል ማዕከል ኃላፊ ዴቪድ ጊብሰን "ግንኙነቱ ውጥረት የነገሰበት ነው" ይላሉ።
ወግ አጥባቂዎች አቡነ ሊዮ ስለ ማኅበረሰባዊ ለውጥ እና ስደተኞች ከሚያቀነቅኑት አቡነ ፍራንሲስ የተለየ ሐሳብ ይዘው ይመጣሉ ብለው ጠብቀው ነበር ይላሉ ጊብሰን።
"አብዛኞቹ ንዴታቸውን እየገለጹ ነው። ቤተ-ክርስቲያኗ አፏን ትዝጋ ማለት ነው የቀራቸው" የሚሉት ምሑሩ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ፅንስ ማቋረጥ ላይ እንድታተኩር እንደሚሹ ይገልጻሉ።
የአሜሪካ የድንበር ጉዳዮች አስፈፃሚ የሆኑት የሮማ ካቶሊክ እምነቱ ተከታዩ ቶም ሆማን ቤተ-ክርስቲያኗ "ተሳስታለች"፤ መሪዎቿ ደግሞ "ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያንን በማቅናት ጊዜ ቢያጠፉ ይሻላል" ይላሉ።
ባለፈው ጥቅምት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት አቡኑ አሜሪካ ስደተኞችን የምትይዝበት መንገድ "ኢ-ሰብዓዊ" ነው ማለታቸውን እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።
ቺካጎ የተወለዱት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ አሜሪካ ስደተኞችን የምታንገላታበት ሁኔታ "ፅንስ ማቋቋረጥን ከሚቃወም" ጎራ የሚጠበቅ አይደለም ብለዋል።
ጊብሰን የአሜሪካ መንግሥት "ዶናልድ ትራምፕ እና ሪፐብሊካን ፓርቲን የሚደግፉ በቂ ካቶሊኮች በተለይ ነጮች አሉ ብሎ በማሰብ ከአቡኑ ጋር ፀብ ማንሳቱ የተሳሳተ ስሌት ነው" ይላሉ።
60 በመቶ የሚሆኑ ነጭ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች ላይ የሚወስዱት እርምጃ ትክክል ነው ብለው እንደሚያስቡ በቅርቡ የወጣ ጥናት ይጠቁማል።
30 በመቶ ሂስፓኒኮች እና ከጠቅላላው የካቶሊክ ተከታይ 37 በመቶ የሚሆኑት የትራምፕ እርምጃ ደጋፊዎች መሆናቸውን ቁጥሮች ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀኝ ዘመም ካቶሊኮች በአዲሱ አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ ቦታ እየያዙ መጥተዋል። የዚህ መገለጫ የሆኑት ጄዲ ቫንስ የፖለቲካ ዕይታቸው ከእምነታቸው የተቀዳ እንደሆነ ይናገራሉ።
ምክትል ፕሬዝደንቱ ምንም እንኳ አሁን አሜሪካ እየወሰድችው ያለው እርምጃ ከቤተ-ክርስቲያኗ ጋር የሚጋጭ አይደለም ቢሉም በሕገ-ወጥ መንገድ የመጡ ሰዎች ሰብዓዊነትን መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረው ያውቃሉ።
አንዳንድ ካቶሊኮች ግን ይህ እየሆነ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ። ጂን ራተንበሪ ቺካጎ ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ገርትሩድ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመን ናት። ከተማዋ የትራምፕ ስደተኞችን የማባረር ፖሊሲ ሰለባ ናት።
"ካቶሊክ በመሆኔ እኮራለሁ። ቤተ-ክርስቲያኗ ከአቡኑ ጀምሮ እስከ ሌሎች ጳጳሳት ድረስ ስደተኞች ክብር ሊነፈጉ አይገባም እያለች ነው። ሰው በመሆናቸው የተሰጣቸው ክብር ሊነፈግ አይገባም" ትላለች።
ቦስተን አቅራቢያ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ደግሞ ለገና በዓል ባዘጋጀው ፕሮግራም እየሱስ ራሱ ስደተኛ ነበር የሚል መልዕክት አስተላልፏል።
በተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት አይስ የተባለው የአሜሪካ መሥሪያ ቤት ስደተኞች ላይ እያደረሰ ነው ያሉትን እንግልት በግልፅ ተቃውመዋል።
በርካታ የአሜሪካ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በፅንስ ማቋረጥ ረገድ ወግ አጥባቂ አቋም ቢኖራቸውም ልክ እንደ ኢቫንጀሊካል ክርስቲያኖች ራሳቸውን ተራማጅ አድርገው ያስባሉ።
ኢቫንጀሊካኖች ባለፉት ሦስት ምርጫዎች በአብዛኛው ድምፃቸውን ለሪፐብሊካኖች ሲሰጡ ካቶሊኮች ደግሞ በተቃራኒው ዲሞክራቶችን ደግፈዋል።
አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ በአሜሪካ የሚገኙ ካቶሊኮች የተወለዱት በሌሎች ሀገራት ውስጥ ነው። ጊብሰን "ይህች ቤተ-ክርስቲያን የተመሠረተችው በስደተኞች ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከወንጌል በተቃራኒ
የዋሺንግተን ግዛቱ ሊቀ ጳጳስ ዮሴፍ ታይሰን በኮንፈረንሱ መግለጫ ድጋፋቸውን ከገለፁ 216 ጳጳሳት አንዱ ናቸው። አምስት ጳጳሳት ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ሦስቱ ደግሞ ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
"ቤተ-ክርስቲያኗ ስደተኞችን የምታይበት መንገድ እና የወቅቱ አስተዳደር የሚመለከትበት መነፅር መሠረታዊ ልዩነት አላቸው። እኛ ለስደተኞች አዎንታዊ ዕይታ አለን" ይላሉ።
ሊቀ ጳጳስ ዮሴፍ ልክ እንደ አቡነ ሊዮ ድንበሩ ክፍት ይሁን ሳይሆን "ሁሉም ስደተኞች በጅምላ ሊባረሩ አይገባም" እንደሚሉ ይገልጻሉ።
"ከሀገር እንዲወጡ እየተደረጉ ያሉት ሰዎች የቤተ-ክርስቲያናችን ምዕመናን ናቸው።"
የሃይማኖት አባቱ እንደሚሉት በርካታ ሂስፓኒኮች በሚያዘወትሩት ቤተ-ክርስቲያናቸው ግማሽ ያክል ምዕመናን ከወቅቱ ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ችግር ላይ ወድቀዋል። ቅስና የያዙ ስደተኞች በመኖራቸው ቤተ-ክርስቲያኗ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወድቃለች።
"ማንኛውም ሰው በየትኛውም ሰዓት የሥራ ፈቃዱ ሊሰረዝ ይችላል። ለዚህ ነው አብዛኞቹ የኛ ሰዎች ሰነዳቸውን ይዘው የሚንቀሳቀሱት።"
ጳጳስ ዮሴፍ የወቅቱ የአሜሪካ ፖሊሲ ከካቶሊክ አስተምህሮ ጋር የሚቃረን ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
ለሄሴ ሮሜሮ ግን የአሜሪካ ሊቀ-ጳጳሳት እና አቡኑ ናቸው ከካቶሊክ ትምህርት በተቃራኒ የቆሙት። አስተምህሮቱ ስደተኞች ሕግ እንዲያከብሩ፣ ሀገር ቤት መቆየት እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው ይደነግጋል።
"በአሜሪካ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ያሉ ሊቀ ጳጳሳት አስተምህሮቱን እና ነገረ መለኮቱን የሚመለከቱበት መንገድ ዘመናይ እና ተራማጅ ነው።"
ምንም እንኳ ሮሜሮ አቡኑ እና ሊቀ ጳጳሳቱ የቤተ-ክርስቲያኗ መሪዎች መሆናቸውን ቢቀበሉም እንዲለወጡ እንደሚፀልይ ይናገራል።
"ብቸኛው ኃጢያት የሌለበት እየሱስ ነው። እሱ ፍፁም ነው። ሌሎቻችን አንዳችን ለአንዳችን ልንፀልይ ይገባል።"















