የኤርትራ ጦር በሽራሮ በፈጸመው ጥቃት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት የኤርትራ ጦር በሽራሮ ከተማ ላይ በከፈተው ጥቃት አንዲት የ14 ዓመት ታዳጊ መገደሏን እና 18 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።
ሮይተርስ ከሰብዓዊ ድርጅት ተቋማት የተገኘ መረጃ የሰፈረበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰነድን ተመልክቻለሁ ብሎ ባወጣው ዘገባ፣ የኤርትራ ጦር ቢያንስ 23 ጊዜ ወደ ሽራሮ ከባድ መሳሪያ ተኩሷል ብሏል።
ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ ከተማ ላይ ከፍቶት ነበረ በተባለው ጥቃት፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ተጠልለውበት የነበረ ትምህር ቤት ጉዳት ደርሶበታል ብሏል የሮይተርስ ዘገባ።
የከባድ መሳሪያ ጥቃት ተፈጽሞባታል የተባለችው ሽራሮ ከኤርትራ ድንበር 11 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።

በተመሳሳይ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የኤርትራ ጦር በሽራሮ ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ድበደባ መፈጸሙንና ከዚያ በፊት ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ሠራዊት ጋር ውጊያ አካሂደው እንደነበረ ገልጸው ነበር።
አቶ ጌታቸው ትናንት ሰኞ ግንቦት 22/2014 በትዊተር ገጻቸው ላይ ቅዳሜና እሁድ የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከአንድ ሳምንት በፊት ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ. ም. የኤርትራ 57ኛ እና 21ኛ ክፍለ ጦሮች ወደ ትግራይ ክልል ጥቃት ስንዝረው እንደነበርና አዲአዋላ በተባለው አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ጥቃቱን እንደመከቱ ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ትናንት ግንቦት 22/2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተካሄደ ስለተባለው ውጊያ መረጃው እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጸው፣ የተከሰተ ነገር ካለ አጣርተው መረጃ እንደሚሰጡ ተናግረው ነበር።
'የህወሓት ትንኮሳ'
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኤርትራ ሠራዊት ጥቃት ሊፈጽም እንደማይችል በመግለጽ “ህወሓቶች ራሳቸው ትንኮሳ ፈጽመው” የሚያሰሙት ክስ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ዛሬ ለአል ዐይን አማርኛ ይህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ግጭት የተከሰተው በህወሓት ትንኮሳ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አል ዐይን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ትንኮሳ የፈጸመው ህወሓት ጉዳት የደረሰውም በህወሓት አማጺያን ላይ ነው ስለማለታቸው ዘግቧል።
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ህወሃት ይህን “ትንኮሳ” የሚፈጽመው ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደ ግጭት ለማስገባት ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊታቸው ላይ የኤርትራ ጦር ይህን ጥቃት የሚሰነዝረው “ቀጠናውን ወደማያባራ ግጭት” ለመውሰድ መሆኑን እና “ይህም ወደ ሰላም ሊደረግ የሚችል ጉዞን የሚያሰናክል” ነው ብለዋል።
ይህ ባለፉት ቀናት በኤርትራ እና የትግራይ ኃይሎች መካከል ተደርጓል ስለተባለ ጦርነት ከኤርትራ በኩል የተባለ ነገር የለም።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኤርትራ ህወሓት ለዳግም ጦርነት በዝግጅት ላይ እንደሆነ በመግለጽ እራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ገልጻ ነበር።
ባለፈው መጋቢት ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ያወጀውን የተኩስ አቁም የህወሓት መሪዎች ከተቀበሉት በኋላ የጎላ ወታደራዊ ግጭት ሳይከሰት ቆይቷል።
ነገር ግን ከሚያዚያ ወር ወዲህ የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ ውጥረት እንዳለ ሲነገር የቆየ ሲሆን አልፎ አልፎ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተዘግቧል።
ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተው ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱን ታማኝ ምንጮች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለው በራማ እና ባድመ አካባቢ ባለው የኤርትራ ጦር ላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ጥቃቱን ተከትሎ በትግራይ ኃይሎችና በኤርትራ ጦር መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል።
ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኤርትራ ሠራዊት ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት የህወሓት ኃይሎች ተደጋጋሚ የሮኬት ጥቃቶችን በኤርትራ ላይ መፈጸማቸው ይታወሳል።
የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልል ተስፋፍቶ ለወራት የቆየ ሲሆን አስካሁን መቋጫ አላገኘም።
ከፌደራልና ከክልል ኃይሎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ የሆኑት የህወሓት ኃይሎች፤ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ያወጀውን ተኩስ አቁም ተከትሎ ጦርነቶች ጋብ ያሉ ቢመስሉም በድንገት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አለ።












