ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል አካላትን በጀልባ ያጓጓዘው ግለሰብ የ40 ዓመት እስራት ተፈረደበት
የአሳ ማጥመጃ ጀልባን በመጠቀም የባለስቲክ ሚሳኤል ክፍሎችን ከኢራን በየመን ወደሚገኙት የሁቲ አማጺያን ያጓጓዘው ግለሰብ አሜሪካ ውስጥ የ40 ዓመት እስራት ተፈረደበት።
ፓኪስታናዊው ሙሐመድ ፓህላዋን በጥር 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋለው አሜሪካ በአረቢያን ባሕር ላይ ባካሄደችውን ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት ነው። በዚህ ዘመቻ ሁለት አሜሪካ ባህር ኃይል አባላት ሰጥመው ሕይወታቸው አልፏል።
ፓህላዋን የሚመራው ቡድን የባለስቲክ ሚሳኤል የማስተላለፉ ተግባር ላይ የተሳተፉት በአሳ አጥማጅነት እንደሚሠሩ የተነገራቸውን በማመን እንደሆነ መስክረዋል።
በወቅቱ የሁቲ አማጺያን በእስራኤል ላይ ተከታታይ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን እየፈጸሙ ነበር።
በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት እንደሚያሳዩ በመግለጽም በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ይንቀሳቀሱ በነበሩ ዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦችን ዒላማ አድርገዋል።
ኢራን 'የሁቲ አማጺያንን ታስታጥቃለች' በሚል የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
የባለስቲክ ሚሳኤል ክፍሎችን የጫነችው ጀልባ አባላት በአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ግዛት በሚገኝ በፍርድ ቤት የሰጡት ምስክርነት፤ ይህ ዓይነቶቹን ጥቃት ለመፈጸም የሚውሉት መሣሪያዎች እንዴት እንደሚጓጓዙ የጠቆመ ነው።
የአሜሪካ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ፤ በፓህላዋን ጀልባ ላይ የተገኙት የባለስቲክ ሚሳኤል ክፍሎች፤ "ኢራን ለሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ከምታሰራጫቸው እጅግ የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎች መካከል" የሚመደቡ መሆኑን ከችሎት ውሎው በኋላ ተናግሯል።
ሐሙስ ዕለት የቅጣት ውሳኔው የተሰማው የ49 ዓመቱ ፓኪስታናዊ በአምስት ክሶች ወንጀለኛ ተብሏል። ከክሶቹ ውስጥ የሽብር ወንጀል መፈጸም እና ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ማጓጓዝ የሚሉት ይገኙበታል።
የፍርድ ቤት መዝገቦች እንደሚያሳዩት ከአምስቱ ክሶች ውስጥ ሁለት 20 ዓመት እስራት አስፈርደውበታል። ሌሎቹ ሦስት ክሶችም በተመሳሳይ 20 ዓመት ቅጣት ያስጣሉበት ሲሆን በድምሩ 40 ዓመት ተፈርዶበታል።
በፍርድ ቤት የመሰከሩት ስምንት የባሕር ጉዞ ሠራተኞች፤ የኑስ በተባለችው ጀልባ ላይ የተጫኑት ትላልቅ እቃዎች ምን እንደሆኑ የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ ተናግረዋል።
አንድ ሠራተኛ ስለ እቃዎቹ ምንነት ለፓህላዋን ጥያቄ ቢያቀርብም የራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲያተኩር እንደተነገረው ገልጿል።
ፓህላዋን በበኩሉ ጭነቱ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ያውቅ ነበር ተብሏል። የጀልባ ጉዞውን ከመጀመሩ ከቀናት በፊት ከባለቤቱ ጋር በነበረው የመልዕክት ልውውጥ ወቅት ራሱን "በቁሙ የሞተ ሰው" በማለት ሲጠራ ነበር።
"ደኅና እንድመለስ ብቻ ጸልይ" በማለት የላከው መልዕክት በማስረጃነት በፍርድ ቤት ቀርቧል።
ባለቤቱም በምላሹ፤ " 'ተመልሼ ልመጣም ላልመጣም እችላለሁ' እያልክ የምትናገረው ለምንድን ነው" ስትል ጠይቃዋለች። ለዚህ ሰጣት ምላሽ "ውዴ ይህ የሥራው ባህሪ ነው" የሚል ነበር።
ፓህላዋን ይህንን ጉዞ ለማድረግ 33,374 ዶላር እንደተከፈለው ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል።
ባለ ጀልባው ከመያዙ በፊት በጥቅምት 2016 ዓ.ም. እና በታኅሣሥ ወራት ሁለት የተሳኩ ጉዞዎችን አድርጓል። አብረውት እንዲሠሩ የቀጠራቸው ከ10 በላይ ፓኪስታናውያን ሥራ ፍለጋ ወደ ኢራን ድንበር የተጓዙ ናቸው ተብሏል።
ጉዞው የኑስ እና ሻሃብ ሚርካዚ በተባሉ ሁለት ኢራናውያን ወንድማማቾች በገንዘብ የሚደገፍ እና የሚቀናጅ "ትልቅ ኦፕሬሽን አካል" መሆኑን አሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ሰኔ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
ወንድማማቾቹ በኢራን እጅጉን ጠንካራ ከሆነው አገሪቱ እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ጠቅሷል።
የአሜሪካ መንግሥት በሌሉበት ወንድማማቾቹ ላይ ክስ የመሠረተ ሲሆን አሁንም ኢራን ውስጥ እንዳሉ ይታመናል።