ማረጥን ተከትለው የሚመጡ የጤና ቀውሶችን ለመከላከል የምትሰራው ሴት

የፎቶው ባለመብት, Leonie Painter
አንዲት ሴት ብቸኝነት፣ ጭንቀት እና ግራ መጋባት ስሜት ስትናወጥ ያበደች መስሏት ነበር። ስለዚህ ሥራዋን ለቀቀች።
ሥራዋን ያስለቀቃት ስሜት ግን በኋላ ላይ የማረጥ (ሜኖፖዝ) ምልክት መሆኑን አወቀች።
በማንቸስተር ከተማ ሞስተን የምትኖረው ሊዮኒ ፔንተር እንደዚህ አይነት ስሜት ለምን እንደሚሰማት እንዳላወቀች እና ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ምልክቶች መታየት ሲጀምሩ ሰዎችን ማውራት እንደምትችል አላወቀችም ነበር።
የ50 ዓመቷ ሊዮኒ "የምልክቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ካወቅኩ በኋላ ጥሩ ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ነገር ግን እዚህ ላይ ለመድረስ ጊዜ ፈጅቶብኛል" ትላለች።
ከዚህ ገጠመኝ በኋላ እያረጡ ያሉ ሴቶችን በማሰባሰብ ቡድን የመሰረተች ሲሆን፤ የቡድኑ ተሳታፊዎችም ስብስቡን "የሕይወት መስመር" ሲሉ ገልፀውታል።
እ.አ.አ መስከረም 2024 የተጀመረው የቡድኑ ስብሰባዎች አላማው ሀፍረት መስበር ነው።
ሊዮኒ ፔንተር በማረጥ ላይ ያለውን መጥፎ ስም ሴቶች እንዲያወሩ እና እንዲመካከሩ ምህዳር መፍጠር እና በቅድመ ማረጥ እና በማረጥ ዙሪያ ዕውቀታቸውን ማሳደግ እንዲሁም አፈ ታሪኮችን የመቀልበስ ግብ እንደያዙ ትገልፃለች።
እንቅስቃሴው ፍሬ ማፍራቱን ተከትሎ የማንቸስተር ከተማ ምክር ቤት በጀት መድቦለት በየሳምንቱ የሚካሄድ የማኅበረሰብ ቡድን ሆኗል።
ሊዮኒ የእርሷ ልምድ በማረጥ ዙሪያ ያለው መደባበቅ ለመስበር እና ለሴቶች ደኅንነቱ ያለው ምህዳር መስጠት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተረድታለች።
"ማረጥ የሕይወት መጨረሻ አይደለም፤ አዲስ ምዕራፍ ነው" በማለት ዋናውን የማዕከሏን መልዕክት ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, North Manchester menopause hub
ሊዛ ዴቪስ ማዕከሉ "የሕይወት መስመር" እንደሆነላት ትናገራለች።
ከመስከረም 2024 ጀምሮ በሕይወቷ እጅግ ፈታኝ በሆነው ጊዜ እየተሰቃየች የነበር ሲሆን፤ "አብዛኛውን ጊዜ" ራሷን የማጥፋት ስሜት ውስጥ እንደነበረች ተናግራለች።
"ምክንያቱን መረዳት ያልቻልኩት የመንፈስ መረበሽ እና ንዴት" ይሰማት እንደነበርም ገልፃለች።
የ46 ዓመቷ ሊዛ "ከአቅሜ በላይ ሆኖ ነበር፣ ግራ ተጋባሁ እና እያበድኩ እንዳለሁ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል።
"አካላዊ ምልክቶቹ የሚያቋርጡ አልነበሩም፤ እና ስሜታዊ ጫናውን ደግሞ ለመግለፅ እንኳ ከባድ ነበር።"
"በእውነት አድኖኛል" የምትለው ሊዛ ቡድኑ ምክቶቿን እንድትረዳ መንገድ ከመጥረጉ ባለፈ እንድታድግ አድርጓታል።
ማዕከሉ "ግልፀኝነትን፣ ሩኅሩኅነት እና ከሁሉም በላይ ያስፈለገኝን ግንኙነት ሰጥቶኛል" ትላለች።
ሊዛ እንዲህ ትላለች፤ "የሚረዳኝን ማኅበረሰብ አግኝቻለሁ፤ የሚያሳድገኝን ሃብት እና ብቸኝነት እንዳይሰማኝ ያደረገ ድጋፍ አግኝቻለሁ።"
"ሙሉ ለሙሉ ከስሜቱ አልወጣሁም፤ ነገር ግን ረጅም ርቀት ተጉዣለሁ" ስትልም ታክላለች።
"ሕይወቴን ዳግም መገንባት ጀምሬያለሁ፤ እናም በጊዜ፣ በትዕግስት እና በሊዮኒ እና በቡድኑ ድጋፍ እደርሳለሁ።"
ሊዛ እንደ እርሷ በማረጥ ምዕራፍ ላይ ያሌ ሴቶችን በመደገፍ እና "በማረጥ ዙሪያ ያለውን ዝምታ ለመስበር" እየረዳች ነው።
"ሰዎች የሚረዳ፣ የሚሰማ እና ስሜታቸውን የሚያረጋግጥ ምህዳር ፈጥሯል።
"በእውነት አድኖኛል እና አሁን ሌሎችን ለማዳን ቁርጠኛ ነኝ" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Deena Banister
ዲና ባንስተር ከምልክቶች ጀምሮ እስከ አጥንት ጤና፣ የሕይወት ዘይቤ እና አዕምሯዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ባለሙያዎችን የሚጋብዘውን ማዕከል በሐኪሟ ጠቋሚነት ከተቀላቀለች አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል።
የ60 ዓመቷ ዲና "በእኔ ላይ ልዩነቱ አስገራሚ ነው" ትላለች።
"በማረጥ ምልክቶች ጋር የተያያዘ ከባድ የጤና ችግር የገጠመኝ መስሎኝ ሥራዬን ለቀቅኩ።
"በራስ መተማመኔ ተንኮታከተ፤ እና ባለማወቅ በድብርት እና በከፍተኛ ጭንቀት እየተሰቃየሁ ነበር" ትላለች።
ቡድኑ "መሠረታዊ መረጃ እና ድጋፍ" እና የአዕምሮ ጤና እና አካላዊ ጤና ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት እንድትፈጥር ዕድሉን እንደሰጣትም ትገልፃለች።
"ለማረጥ እና ለአዕምሮ ጤና እክሌ ትክክለኛውን መድኃኒት አግኝቻለሁ። በማዕከሉ መሪ የሚመራ ጂም ተቀላቅያለሁ እና አሁን ራሴ ላይ እየሰራሁ ነው።"
"ጥንካሬዬ እና በራስ መተማመኔ ጨምሯል እና በሰውነቴ እና በአዕምሮዬ ውስጥ እየተለወጠ ስላለው ነበር ያለኝ አረዳድ በጣም ተሻሽሏል።"
እንደ ሊዛ ዲናም የተማረችውን ለሌሎችም በማጋራት እገዛ ታደርጋለች።
"ማዕከሉ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ትክክለኛ፣ ጊዜውን የዋጀ መረጃ ይሰጣል፤ ከሕክምና እና አዕምሮ ጤና አገልግሎት ጋር ጠቃሚ መስመር ይመሰርታል እና የሴቶችን ሕይወት እያሻሻለ ነው።"
የአካባቢው የጤና አስተዳዳሪዎች ማዕከሉ እንደ ሞዴል ሆና በማንቸስተር ከተማ እና በሌሎችም አካባቢዎች እንዲስፋፋ ተስፋ ሰንቀዋል።














