ማረጥን የተለመከቱ ሰባት የተዛቡ አመለካከቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በየዓመቱ የዓለም የማረጥ ቀን ጥቅምት 7 የሚከበረው ስለ ማረጥ ግንዛቤ መስጠትን ዋነኛ ግብ በማድረግ ነው።
በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶች ማረጥን የተለመከተ የተለያዩ የተዛቡ አመለካከቶች አሏቸው።
ሴቶች በሕይወት የሚቆዩበት ዕድሜ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የሚያርጡ ሴቶችም ቁጥርም ከፍ ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው፣ እአአ በ2021 ዕድሜያቸው 50 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች ቁጥር ከአጠቃላይ ሴቶችና ልጃገረዶች ቁጥር 26 በመቶ ነበር። ይህ አሃዝ ባለፉት አስር ዓመታት 22 በመቶ ነበር።
በማንኛውም ሴት ሕይወት ውስጥ ማረጥ መደበኛ ነገር ቢሆንም በርካቶች ስለ ማረጥ የተዛባ አመለካከት ነው ያላቸው።
ማረጥን የተለመከቱ ሰባት የተዛቡ አመለካከቶችን ቢቢሲ እንዲህ አዘጋጅቷል።
1. ማረጥ በሁሉም ሴት ላይ ተመሳሳይ ነው
የሁሉም ሴት የሆርሞን ለውጥ የተለያየ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ማኅበራዊና ባህላዊ ሁነት፣ የሰውነት አወቃቀር እና አኗኗር የሚወሰን ነው።
የሚታየው ለውጥ የሚጀርምርበት ጊዜና ለውጡ እንደየሴቷ አኗኗር ይለያያል።
አማካዩ የማረጥ ዕድሜ 51 ሲሆን፣ ከ40 እስከ 60 ዕድሜ ውስጥ ባለው ሊሆንም ይችላል።
እንደየአካባቢውና የሴቶች የዘር ግንድ የሚለያይ ነው።
2. በማረጥ ወቅት የሰውነት ክብደት ይጨምራል
በማረጥ ወቅት የሰውነት ክብደት መጨመሩ አይቀርም የሚለው ሁለተኛው የተዛባ አመለካከት ነው።
የሰውነት ምግብን የማብላላት ፍጥነት ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ መቀነሱ አይቀርም። ይህ ግን ማረጥ ከሚያመጣው ለውጥ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ አይደለም።
ሐኪሞች እንደሚሉት ተከታታይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የተመጣጠነ ምግብ ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ያስችላሉ።
3. የሰውነት ሙቀት መጨመር ብቸኛው የማረጥ ምልክት ነው
የሰውነት ሙቅተ ከመጠን በላይ መጨመር የተለመደው ወይም ብቸኛው የማረጥ ምልክት ነው የሚል ዕሳቤ አለ።
የሰውነት ሙቀት መጨመር ቢከሰትም በሁሉም ሴቶች ላይ የሚያጋጥም አይደለም።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት የማረጥ ዓመታት የሚስተዋል ምልክት ነው።
60 በተሞ ሴቶች በሰባት ዓመት ውስጥ የሰውነት ሙቀት መጨመር ይጠፋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
4. ማረጥ የወሲብ ስሜትን ይገድላል
የወሲብ ስሜት ሊቀንስ ከሚችልባቸው ምክንያቶች መካከል የመራቢያ አካል እርጥበት ማጣት እና ድባቴ ይጠቀሳሉ።
ሆኖም ግን በሕክምና እርዳታ እንዲሁም በፍቅር አጋሮች ድጋፍ የተሻለ የወሲብ ሕይወት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል።
5. ማረጥ ድባቴ ያስከትላል
ማረጥ ድባቴ፣ ጭንቀት፣ የስሜት መናወጥን የመሰሉ ተጽዕኖዎች ያስከትላል የሚለው አምስተኛው የተዛባ ዕሳቤ ነው። ማረጥ ድባቴ ወይም የእንቅልፍ ማዛባት አያስከትልም።
የሰውነት ሙቀት መጨምር ምቾት ማጣት ወይም የስሜት ከፍና ዝቅ ሊያመጡ ይችላሉ።
6. የሆርሞን ሕክምና ጎጂ ነው
በእርግጥ ሆርሞን መጠቀም ለጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። ሆኖም ግን ከልብና ደም ሥር ጋር የተያያዙ ሕመሞችን ለመቀነስ ያግዛል።
7. ስለዚህ ማረጥ ምንድን ነው?
ጥናቶች እንደሚሉት፣ ጤናማ ለሆኑ ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል።
ማረጥ የሆርሞን ለውጥን ተከትሎ ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ ነው የሚመጣው።
እንቁላል በየወሩ መለቀቅ አቁሞ የኦኤስትሮጅን መጠን ሲቀንስ ነው ማረጥ የሚባለው።
ከ45 እስከ 55 ባለው ዕድሜ በመደበኛነት ቢከሰትም ከዚያ ቀደም ሊልም ይችላል።
ለ12 ወራት በተከታታይ የወር አበባ አለመታየቱ ሴት ልጅ መውለድ የምትችልበት ወቅት የማብቃቱ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።
ይሄ በሂደት ነው የሚሆነው። የመሸጋገሪያ ወቅት የሆነ የወር አበባ ጊዜ እስከ ሰባት ዓመታት በመደበኛነት የሚቆይ ሲሆን በአንዳንድ ሴቶች ላይ እስከ 14 ዓመታት ሊሆንም ይችላል።
በሦስት ደረጃዎች ነው የሚከሰተው።
አንደኛው ቅድመ ማረጥ ነው።
በ30ዎቹ መጨረሻና በ40ዎቹ መጀመሪያ አብዛኞቹ ሴቶች ላይ የሚታይ ነው።
በዚህ ወቅት ሴቶች የወር አበባ ያያሉ። ሆኖም ግን የኦኤስትሮጅን እና ፕሮጀስእተሮን መጠን ለውጥ ያሳያል።
ሁለተኛው ወደ ማረጥ የመቃረብ ወቅት ነው። ይህ መውለድ የሚቆምበት ጊዜ ነው። የኦኤስትሮጅን መጠን መቀነስ ይከሰታል።
የወር አበባ መዛበት የሚጀምርበት፣ አንዳንዴ የወር አበባ የሚቀርበትና የወር አበባ የሚመጣበት ዑደት የሚቀንስበት ወይም የሚረዝምመበትም ነው።
የሰውነት ሙቀት፣ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት ሊገጥም ይችላል።
የመጨረሻው ድኅረ ማረጥ ነው። ይህም ለ12 ተከታታይ ወራት የወር አበባ ሲቀር ነው። ወደ ማረጥ መቃረብ ላይ የታዩ ምልክቶች ይቀንሳሉ።
የማረጥ ምልክቶች
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ወደ 48 የሚደርሱ የማረጥ ምልክቶች አሉ።
ዋና ዋናዎቹ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ለሊት ላይ ማላብ፣ የወር አበባ የሚመጣበት ወቅትና መጠን መለወጥ፣ የመራቢያ አካል መድረቅ፣ በወሲብ ወቅት ሕመም መሰማት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድባቴ ወይም ጭንቀት፣ የአጥንት አቅም ማነስ ይጠቀሳሉ።
አንዳንድ ሴቶች ለማስታወስ መቸገርና ትኩረት መቀነስን ይጠቅሳሉ። የመገጣጠሚያ ሕመምና የቆዳ መድረቅም ይጠቀሳሉ።
ሁሉም ሴቶች እነዚህን ምልክቶች ያሳያሉ ማለት ግን አይደለም። ወደ 75% ሴቶች ምልክቶቹን ያሳያሉ።












