ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዘሌንስኪ የሰሜን ኮሪያ ምርኮኞችን በሩሲያ በተያዙ ዩክሬናውያን ለመቀያየር ሐሳብ አቀረቡ
ዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሁለቱን ሰሜን ኮሪያዊያን ምርኮኞች በማስረከብ በሩሲያ የተያዙ የዩክሬን ወታደሮችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አሳወቁ።
በኤክስ ገፃቸው በፃፉት መልዕክት "መመለስ ለማይፈልጉ ሰሜን ኮሪያዊያን ወታደሮች አማራጭ ይፈለግላቸዋል" ብለዋል።
"በኮሪያ ቋንቋ ስለጦርነቱ እውነታውን ለሚያስፋፉ እና ሰላም ማምጣት ለሚፈልጉ ወታደሮች ዕድል ይሰጣቸዋል" ሲሉም አክለዋል።
የዩክሬን ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ (ኤስዩቢ) እንዳለው ከተማረኩት ሁለት ወታደሮች መካከል አንዱ ወደ ሩሲያ ያቀናው ለሥልጠና መስሎት እንጂ ለጦርነት መሆኑን እንደማያውቅ ተናግሯል።
ወታደሮቹ በጄኔቫ ስምምነት መሠረት ሕክምና እንደተደረገላቸውና በተገቢው ሁኔታ እንደተያዙ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
አንደኛው ወታደር ሲማረክ የሩሲያ ወታደራዊ መታወቂያ ይዞ ነበር። የተሰጠው ስምም የተለየ ነበር።
የጦር ምርኮኞቹ ዩክሬንኛ፣ እንግሊዝኛ ወይም ሩስኪ ስለማይችሉ ከደቡብ ኮሪያ የደኅንነት ተቋም ጋር በመተባበር በኮርያኛ አስተርጓሚ በኩል እየተነጋገሩ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን ወታደሮች ስለማሰማራቷ ተጠይቀው አላስተባበሉም። የሩሲያ "ሉዓላዊ ውሳኔ ነው" ሲሉ መልሰዋል።
ዜሌንስኪ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሯቸው ምሥሎች በጦር ምርኮኛነት የተያዙት ወታደሮች ቆስለው ያሳያሉ።
የሩሲያ መታወቂያ የተሰጠው ወታደር የተወለደው ሞንጎሊያ አቅራቢያ በሚገኘው ቱቫ ሪፐብሊክ እንደሆነ ተደርጎ መፃፉን ዩክሬን ትገልፃለች።
ኤስዩቢ እንደሚለው አንዳንድ ወታደሮች የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የአንድ ሳምንት ሥልጠና ብቻ እንደወሰዱ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ ሩሲያዊያን" ከሰሜን ኮሪያ የመጡትን በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ከምትገኘው ቱቫ ግዛት እንደመጡ በማስመሰል ለመደበቅ እየሞከሩ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
የዩክሬን ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደሚለው መታወቂያ ካርድ ይዞ የተገኘው ወታደር የተወለደው እአአ በ2005 ሲሆን ከ2021 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ጦር ውስጥ ሲያገለግል ቆይቷል።
ሁለተኛው ወታደር አገጩ ስለተጎዳ በጽሑፍ በሰጠው መልስ መሠረት የተወለደው እአአ በ1999 ሲሆን ከ2016 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ጦር ውስጥ ዒላማ ተኳሽ ሆኖ ቆይቷል።
የጄኔቫ ስምምነት የጦር ምርኮኞች በሚገባቸው ቋንቋ ጥያቄ እንዲጠየቁ ያትታል።
ቢቢሲ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሁለቱ ምርኮኞች ሰሜን ኮሪያዊያን ስለመሆናቸውም ሆነ እንዴት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ በተናጠል ማጣራት አልቻሉም።
ዩክሬን እንደምትለው ሰሜን ኮሪያ 10 ሺህ ገደማ ወታደሮች ወደ ሩሲያ መላኳን የሚያሳይ መረጃ ከደቡብ ኮሪያ አግኝታለች።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ ደኅንነት ደግሞ በሩሲያ እየተዋጉ ካሉት ወታሮች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት ተገድለዋል ብሎ 2700 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።