ትራምፕ ኳታርን ለመከላከል የገቡት ቃል ሰላም ለራቀው ቀጠና መረጋጋት አሊያም ጦስ ሊሆን ይችላል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኳታሩ ኢሚር ታሚም ቢን ሀማድ አል ታኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት የባህረ ሰላጤው አገር የሆነችውን ኳታር የአሜሪካን ጦር ጨምሮ በየትኛውም መንገድ ለመከላከል ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

የዚህ ትዕዛዝ ጽሑፍ በነዳጅ የበለፀገችው አገር ላይ የሚቃጣ የትኛውም ወታደራዊ ጥቃት በዩናይትድ ስቴትስ ስጋት ተደርጎ እንደሚታይ እና "የአሜሪካን እና የኳታርን ፍላጎት ለመከላከል እና ሰላምና እና መረጋጋትን ለማምጣት ሁሉንም ሕጋዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አስፈላጊ ከሆነም ወታደራዊ እርምጃ ትወስዳለች" ይላል።

ትዕዛዙ በአሜሪካ እና ኳታር መካከል ግዙፍ የደኅንነት አጋርነት ሆኖ የሚታይ ሲሆን፤ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ትብብር ጋር የሚመሳሰል ነው። በጎረቤት አረብ አገራት ቅናት ማሳደሩም አይቀሬ ነው።

ኳታር ከጥቂት ዓመታት በፊት በጎረቤቶቿ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ማዕቀብ ማዕከል ከመሆን የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም አምባሳደር በመሆን ያደረገው ሽግግር አስደናቂ ከመባል የሚተናነስ አይደለም። በቅርቡ ሐማስ እና እስራኤልን ለማስታረቅ ያደረገችው ሚና የሚጠቀስ ነው።

ሐማስ የፖለቲካ ቢሮው በዶሃ የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ ሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገውን ባለ 20 ነጥብ የፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰላም ስምምነትን እየተመለከተ ነው። ዶሃ በቀጠናው ትልቁ የሆነው የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያ አል ኡዲስ መቀመጫ ናት።

የትራምፕ የከለላ እርምጃ እስራኤል ባለፈው ወር የሐማስ መሪዎችን ዒላማ አድርጋ በኳታር በፈፀመችው የአየር ጥቃት ዝቀተኛ የቡድኑ አባላት እና የኳታር የፀጥታ መኮንኖች ከተገደሉ እና ከገዢው ንጉሳዊ የአል ታኒ ቤተሰብ ቁጣን ተከትሎ የመጣ ነው።

ኳታር ከወራት በፊት አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ላደረሰችው ጥቃት አፃፋዊ ምላሽ በቴህራን ጥቃት ተፈፅሞባታል።

ከአሜሪካ ጋር ባላት አጋርነት እና ወታደራዊ ሰፈር በማስተናገዷ የሚጠበቀውን ከለላ አላገኘችም በሚል ኳታር በገልፍ አረብ አገራት ውስጥ እያደረገ የመጣው ስጋት አንዣቦባታል።

እስራኤል ኳታር ላይ የፈፀመችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የትራምፕን አዲስ ትዕዛዝ "የሁለቱ አገራትን ጥብቅ የመከላከያ አጋርነት ለማጠናከት ጠቃሚ እርምጃ" ሲሉ በደስታ ተቀብለውታል።

ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንት ትራምፕ እርምጃ የመጣበት ወቅት እና ምክንያቱ እንዲሁም በዋሽንግተን ተፈፃሚነቱ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳ ነው።

እርምጃው ትራምፕ የጋዛን እጣ ፈንታ በሚወስነው እቅድ ዙሪያ ሐማስ እየተነጋገረ ባለበት ወቅት ስጋት ያለበት የቀጣናው ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ነው።

በእስራኤል የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዳን ሸፒሮ ትራምፕ ከዶሃ መተማመኛ ሳያገኙ ለኳታር ትልቅ ሽልማት እየሰጡ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ትራምፕ ለኳታር የሰጡት የደኅንነት ከለላ ሐማስን ስምምነቱን እንዲቀበል ካላደረጉ አሊያም ቡድኑ ካልተስማማ ከአገሪቱ ካላባረሩ ምንም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም ሲሉ እርምጃው ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልፀዋል።

የእስራኤሉ ሀርትዝ ጋዜጣ እርምጃው በእስራኤል ምን ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ሲያጠቃልል፤ "ኔታኒያሁ የትም ቢሄዱ ደኅንነት እንደማይሰማቸው ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም ትራምፕ በኳታር ለሚኖሩ የሐማስ አመራሮች ያለመነካት ዋስትና ሰጥተዋል" ብሏል።

ይሁን እንጂ የገልፍ ተንታኞች እስራኤል ከድንበሯ አልፋ የምትፈፅመው ጥቃት እያደረ ባለበት በዚህ ወቅት እና በአሜሪካ የደኅንነት ጥላ ስር መግባት አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ጊዜ ቀጣናውን ለማረጋጋት የትራምፕ ከለላ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የዩሮኤዢያ ቡድን አባል የሆኑት ፊራስ ማክሳድ የትራምፕ እርምጃ ኳታርን እና ሌሎችን የገልፍ አጋራት ዳግም ለማስተማመን "የሆነ ያህል መንገድ ነው" የሚሉ ሲሆን፤ ሳዑዲ አረቢያም ተመሳሳይ ከለላ ይሰጣታል ብለው እንደሚጠቁ ተናግረዋል።

ለኳታር የተሰጣት የደኅንነት ዋስትና ጥቃት ከተሰነዘረባት እስከ አሜሪካ የጦር ድግፍ ድረስ ሰፊ ነው። በዚህ እይታ ከለላው በአንድ አባል አገር ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከተሰነዘረ የጋራ ምላሽ እንዲሰጥ ከሚጠይቀው የኔቶ አንቀፅ 5 ጋር የሚመሳሰል ነው።

ነገር ግን ከለላው በዋይት ሐውስ የወጣ የአስፈፃሚ ትዕዛዝ መሆኑ አሜሪካ የኃይል እርምጃ ከመውሰዷ በፊት በፕሬዝዳንቱ ለምክክር መቀመጥ ያለበትን የኮንግረሱን ሥልጣን የሚተላለፍ ነው።

ይህም ማለት ትዕዛዙ ሕጋዊነት የሚጎድለው እና በቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሊሻሻል አሊያም ላይፈፀም የሚችል ነው። ከዚህ ባሻገርም በኮንግረሱ አባል በሆኑ ዲሞክራቶች ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል።

ይህ ትዕዛዝ "አሜሪካ ትቅደም" በሚል አጀንዳ በሚታወቀው የትራምፕ 'አሜሪካን ዳግም ታላቅ የማድረግ' የድጋፍ እንቅስቃሴ ውስጥም ተቃውሞ ገጥሞታል።

ለትራምፕ ቅርብ የሆኑት የቀኝ ዘመም ተሟጋች ሎራ ሎመር ኳታር ለአሜሪካ አጋር ከመሆን ይልቅ ስጋት ናት ሲሉ አመልክተዋል።

የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት የሬዲዮ አቅራቢ ማርክ ሌቪን የአሜሪካን በቀጣናው የተለመደ አጋርነት አፍራሽ ነው የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን፤ "በኳታር ያለው የሐማስ አመራር በእስራኤል ቢገደል ከእስራል ጋር ወደ ጦርነት ልንገባ ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

በሌላ ጎን ደግሞ በኳታር የትራምፕ ቤተሰብ ግላዊ እና የንግግድ ትስስር የሚገኝ ሲሆን፤ በትራምፕ ተቀናቃኞች ከባለፀጋ የገልፍ አገራት ጋር የሚደረግ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የጥቅም ግጭት ሆኖ ይታያል ይላሉ።

በልጆቻቸው ኤሪክ እና ዶናልድ ጁኒየር የሚመራው የትራምፕ ኩባንያ በኳታር ቅንጡ የጎልፍ ሪዞርት ለመገንባት ባለፈው ሚያዚያ ውል አስሯል።

ኳታር ለአሜሪካ አዲስ 747 አውሮፕላን ያበረከተች ሲሆን፤ ትራምፕ 'ኤር ፎስስ ዋን' በዚህ አውሮፕላን ለመተካት አስበዋል።

የዋይት ሐውስ እና የኳታር ባለሥልጣናት በንግድ ግንኙነቶች እና በፖሊሲ መካከል ምንም የጥቅም ግጭት የለም ሲሉ ያስተባብላሉ።

ይሁን እንጂ አካውንተብል ዩኤስ የተባለው ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ቶኒ ካርክ በሁለቱ መካከል ያለውን መስመር በመጣስ ትራምፕን ይወቅሳሉ።

"ከኳታር መንግሥት ጋር የንግድ ስምምነት ያለው ዶናልድ ትራምፕ ለቅንጡ የኳታሩ የጎልፍ ሜዳ ወታደራዊ ጥበቃ ግብር ከፋዮችን አሜሪካዊያንን ገንዘብ ማስከፈል ይፈልጋል" ሲሉ ተችተዋል።

ትራምፕ ባለፈው ግንቦት የንግድ ንግግሮችን ባካተተው የቀጣናው ይፋዊ ጉዟቸው ዶሃን ጎብኝተዋል።

ይሁን እንጂ ዋይት ሐውስ የጥቅም ግጭት ክስን ሁሌም ውድቅ ያደርጋል።

የዋይት ሐውስ ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪ የሆኑት አና ኬሊ ለቢቢሲ "የፕሬዝዳንት ትራምፕ ኩባንያዎች በልጆቻቸው በአደራ ይተዳደራሉ። ምንም የጥቅም ግጭት የለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።