ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጦርነቱን በሰላም የመቋጨት ሂደት ውስብስብ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ
የኢትዮጵያን የርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገው ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
ሆኖም የሰላም ሂደቱ ውስብስብና ረጅም እንደሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ሰኞ ግንቦት 29፣2014 ዓ.ም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“የትኛውም የሰላም ሂደት ረጅም ነው። ቀላል አይደለም። ውስብስብና የተደራረቡ ሁነቶችን የያዘ ነው” ብለዋል።
አንድ አመት ከሰባት ወር የዘለቀውን የርስ በርስጦርነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለማግኘት የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የትግራይ አመራሮችንና የፌደራሉን ባለስልጣናትን ባናገሩበት ማግስትም ነው ይህ የተነገረው።
የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ ለሆኑት ኦባሳንጆ ኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ እንዳላትም ቢልለኔ አስረድተዋል።
በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር አደራዳሪ የሆኑት ኦባሳንጆ በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን በአሁኑ ጉብኝታቸውም የትግራይ አመራሮችንና በፌደራሉም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናትን አግኝተዋል።
ኦባሳንጆ ከውይይታቸውም በኋላ የሰላም ሂደቱ የዘገዬ ቢሆንም ከስድስት ወር በፊት ከነበረው የተሻለ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሰብዓዊ ተኩስ አቁም በስራ ላይ ያለ ቢሆንም በድርድር ላይ የተመሰረተ የግጭት ማቆምና ሰላምም እንዲመጣ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሆኖም በትናንትናው ዕለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ በባለፉት ሳምንታት የትግራይ ሃይሎች የጦርነት “አታሞ እየመቱ” ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
የትግራይ ሃይሎች በበኩላቸው ለሰላም ጥረቱ ቁርጠኛ እንደሆኑ ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል።
በባለፉት ሳምንታት መንግሥት ህግን ማስከበር በሚለው ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ለእስር ተዳርገዋል።
ከነዚህም ውስጥ 18 ጋዜጠኞች የታሰሩ ሲሆን የመንግሥት አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እርምጃውን “ህገወጥ ብሎታል”።
ቢልለኔ ግን ከኮሚሽኑ በተቃራኒ ከታሰሩት መካከል አብዛኛዎቹ በመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ አካል እውቅና የተሰጣቸው እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለው የጅምላ እስራት “ከተፈቀደላቸው የጸጥታ አካላት ውጭ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ” እና “ስልጣን በማን እጅ” መሆን እንዳለበት ግልጽ ለማድረግ” መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ነው ሲሉ ተናግረዋል።