የቀድሞው የአንጎላ መሪ አስከሬን ስፔን ውስጥ እንዲመረመር ቤተሰቦቻቸው ጠየቁ

በቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ሞት ዙሪያ ቤተሰቦቻቸው አንዳች ሴራ ሳይኖር አቀይርም በማለታቸው ምርመራ እንዲደረግ የስፔን ፍርድ ቤት አዘዘ።

ስፔን ባርሴሎና ውስጥ በሕክምና ላይ ሳሉ ሕይወታቸው ማለፉ የተነገረው ዶስ ሳንቶስ፣ ቤሰቦች ሳይገደሉ አልቀሩም በሚል ጥርጣሬ ነው ምርመራው እንዲደረግ የከተማዋን ፍርድ ቤት የጠየቁት።

ምርመራው እንዲደረግ ጥያቄ ያቀረበችው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሴት ልጅ ቺዜ ዶስ ሳንቶስ ናት።

ለዚህም ምክንያቷ በአገራቸው አንጎላ ያሉ የአባቷ የፖለቲካ ጠላቶች፣ በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ዶስ ሳንቶስ ተቃዋሚዎችን ሊደግፉ ስለሚችሉ በሕይወት እንዲመለሱ አይፈልጉም ብላለች ልጃቸው።

ለ38 ዓመታት አንጎላን የመሩት የ79 ዓመቱ ዶስ ሳንቶስ፣ ስፔን ውስጥ የሕክምና ክትትል እያደረጉ ሳለ ነው በልብ ችግር ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቤተሰብ ጠበቃ እንዳሉት፣ ዶስ ሳንቶስ ስፔን ውስጥ እንዲቀበሩ ከሰጡት ኑዛዜ በተቃራኒ የአንጎላ መንግሥት ይፋዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማካሄድ በቶሎ አስከሬናቸው እንዲመለስ መሞከሩን ተቃውመዋል።

ጨምረውም ልጆቻቸው ወደ አንጎላ በመሄድ በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ለመታደምም ሆነ ያረፉበትን ቦታ መጎብኘት ስለማይችሉ መንግሥት የዶስ ሳንቶስ ሞትን ፖለቲካዊ እያደረገው ነው ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞት በቤተሰባቸውና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ አበላሽቶታል።

አሁን ከአገር ውጪ የምትገኘው የፕሬዝዳንቱ ልጅ ኤዛቤላ ዶስ ሳንቶስ የአገሪቱን የነዳጅ ዘይት ተቋም በምትመራበት ጊዜ የሕዝብ ገንዘብ በመመዝበርና በማባከን ተከሳለች።

ነገር ግን ኤዛቤላ የሚቀርብባትን ክስ ሆን ተብሎ የተቀነባበረባት ፖለቲካዊ ክስ ነው በማለት አስተባብላለች።

ኤዛቤላ ባላት የሀብት መጠን የተነሳ በአፍሪካ የናጠጡ ባለፀጋዎች ናቸው ከሚባሉ ሴቶች መካከል ቀዳሚዋ እንደሆነች ይነገራል። ከሙስና ጋር በተያያዘ በሚቀርብባት ክስ የተነሳም ወደ አሜሪካ እንዳትገባ እገዳ ተጥሎባታል።

የአንጎላን የመሪነት መንበር እንዲይዙ በዶስ ሳንቶስ በራሳቸው የተመረጡት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆአዎ ሎሬንዞ፣ የመንግሥታቸው ስም ከቀድሞው መሪ ሞት ጋር መነሳቱን ፓርቲያቸው አስተብብሏል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም መንግሥታቸው አገሪቱን ለረጅም ጊዜ ለመሩት ግለሰብ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት ብለዋል። በተጨማሪም በፕሬዝዳንቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት የሚፈልግ ማንኛው የአገሪቱ ዜጋ እንደማይከለከል አመልክተዋል።

ሟቹ ዶስ ሳንቶስ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ተቀስቅሶ ሌሎች አገራት የተሳተፉበትን አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም እንዲያበቃ በማስቻላቸው “የሰላም መሃንዲስ” እየተባሉ ይታወሳሉ።

ነገር ግን በሥልጣን ዘመናቸው መጠነ ሰፊ ሙስና እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውም ይጠቀሳል።

ለ27 ዓመታት በአንጎላ የተካሄደው ጦርነት አገሪቱ ላይ ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ሲሆን፣ 500,000 የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት ማጥፋቱም ይነገራል።