በዓለም የመጀመሪያው ግማሽ ትሪሊየነር ኤሎን መስክ የአንድ ትሪሊየን ዶላር ክፍያው ጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቴስላ አለቃ ኤሎን መስክ ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ክፍያው በባለድርሻዎች ጸደቀለት። ይህም ክብረ ወሰን የሰበረ ክፍያ ነው።
ስምምነቱ በ75 በመቶ ድምጽ ጸድቋል። ሐሙስ ዕለት በተከናወነው የድርጅቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ውሳኔውን ታዳሚዎች በከፍተኛ ጭብጨባ አጅበዋል።
የዓለም ቁጥር አንዱ ከበርቴ መስክ የኤሌክትሪክ መኪናውን የገበያ ዋጋ በ10 ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ አለበት። ይህንን ካደረገ እና የተለያዩ ግቦችን ካሳካ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አዳዲስ አክሲዮኖችን ያገኛል።
የክፍያ መጠኑ ትችት አስከትሏል። የቴስላ ቦርድ ግን ውሳኔው ባይጸድቅ መስክ ኩባንያውን ሊለቅ እንደሚችል ተከራክሯል። ኩባንያው እሱን ማጣት እንደማይፈልግም ገልጿል።
መስክ በኦስተን፣ ቴክሳስ የተደረሰውን ውሳኔውን ተከትሎ መድረክ ላይ ወጥቶ ስሙን እያነሱ ለዘፈኑለት ባለአክስዮኖች ሲደንስ ታይቷል።
"የምንጀምረው የቴስላን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ አዲስ ምዕራፍ ነው" ብሏል።
"ሌሎች የባለድርሻ ስብሰባዎች የእንቅልፍ ፌስቲቫሎች ናቸው። የእኛ እኛ ግን ሞቅ ያለ ነው" ሲል አክሏል።
መስክ ክፍያውን ከፍ ለማድረግ በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ሊያሳካቸው ከሚገቡት ወሳኝ ነገሮች አንዱ የቴስላን የገበያ ዋጋ አሁን ካለበት 1.4 ትሪሊየን ዶላር ወደ 8.5 ትሪሊየን ዶላር ማሳደግን ያካትታል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ራሳቸውን የሚያሽከረክሩ የሮቦታክሲ መኪናዎችን ወደ ሥራ ማስገባትም ይጠበቅበታል።
መስክ በኦፕቲመስ ሮቦት ላይ ትኩረት አድርጓል ሲሉ ተንታኞች ገልጸዋል።
የዲፕዋተር አሴት ማኔጅመንት ባልደረባው ጂን ሙንስተር "የ 'አዲሱ ምዕራፍ' ራዕዩ የሚጀምረው በኦፕቲመስ ነው። እስካሁን ስለ መኪኖች፣ ራሳቸውን ስለሚያሽከረክሩ መኪናዎች እና ስለሮቦታክሲ አልተጠቀሰም" ብለዋል።
መስክ ግን በኋላ ላይ ራሳቸውን ስለሚያሽከረክሩ መኪናዎች ጠቅሷል። ኩባንያው አሽከርካሪዎች "የጽሑፍ መልዕክት እየላኩ እንዲነዱ" በመፍቀድ "ምቹ" እንደሆነ ተናግሯል።
የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ቴስላ መኪናዎቹ ራሳቸውን በሚያሽከረክሩበት ወቅት ብዙ አደጋዎች መከሰታቸውን ተከትሎ እየመረመሩት ነው። መኪናዎቹ በቀይ መብራት አለመቆም ወይም በተሳሳተ መንገድ በመነዳታቸው አንዳንዶቹ አደጋዎች እና ጉዳቶች አስከትለዋል።
የቴስላ አክሲዮኖች ከሰዓታት በኋላ በትንሹ ከፍ ያከሉ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ከ62 በመቶ በላይ ጨምረዋል።
መስክ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር አብሮ መሥራት መጀመሩን ተከትሎ ሽያጩ ቀንሷል። አሁን ግን ግንኙነታቸው ሻክሯል።
የቴስላ ባለአክሲዮን የሆኑት ሮስ ገርበር ለቢቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት የመስክ የክፍያ ስምምነት "በሥራ ላይ ከሚታዩ ለማመን የሚከብዱ ነገሮች የደረሱበት ደረጃን ያሳያል።"
መስክ ለቴስላ ያለውን ግብ ግልጽ ቢያደርግም ግን ኩባንያው የገንዘብ አፈጻጸሙን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጥሙታል ሲሉ ገርበር ካዋሳኪ የተሰኘው የኢንቨስትመንት ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ገርበር ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ገርበር አክለውም ለሮቦቶች ትልቅ ፍላጎት ይኖራል ወይ የሚለው አሁንም ግልጽ አይደለም። ቴስላ እንደ ዌይሞ ካሉ ተቀናቃኞቹ በሮቦትታክሲ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጠንካራ ፉክክር ይገጥመዋል።
የዌድቡሽ ሴኩሪቲስ የቴክኖሎጂ ተንታኝ የሆኑት እና የመስክን የቴስላ አመራር ለረዥም ጊዜ ሲደግፉ የቆዩት ዳን ኢቭስ፣ ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ "የቴስላ ትልቁ ሃብት" ሲሉ ጠርተውታል።
"የሰው ሠራሽ አስተውሎት ግምገማው እየተፈታ መሆኑን እናምናለን። በሚቀጥሉት 6 እና 9 ወራት ውስጥ ለቲኤስኤልኤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የተመሠረተ ግምገማ ላይ የሚደረገውን ጉዞ አሁን መጀመሩን እናምናለን" ሲሉ ኢቭስ አክለዋል።
መስክ 13 በመቶ የቴስላ አክሲዮኖች ባለቤት ነው። ባለአክሲዮኖች የኩባንያውን የገበያ ዋጋ በአሥር እጥፍ ካሳደገ በአሥር ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ክፍያ እንዲያገኝ ሁለት ጊዜ ወስነ ይህንንም አሳክቷል።















