ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አስተያየትን ተከትሎ ትራምፕ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸው እንዲንቀሳቀሱ አዘዙ
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬድቭ "ተንኳሽ" አስተያየት ሰጥተዋል ያሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸው ተንቀሳቅሰው "በተገቢው ቀጣና" ላይ እንዲሰማሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ ሁለቱ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦች "በተገቢው ቀጣና" ከማለት ውጭ የት እንደሚሰፍሩ ያልገለጹ ሲሆን ይህም የአሜሪካን ወታደራዊ ፕሮቶኮል ጋር ተያይዞ ነው።
ትራምፕ፤ ለሩሲያ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ቋጭታ የተኩስ አቁም እንድታደርግ ቀነ ገደብ አስቀምጠው ካለበለዚያ ማዕቀብ ይጣልባታል በሚል ማስፈራራታቸውን ተከትሎ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት "እያንዳንዷ አዲስ ቀነ ገደብ ዛቻ እንዲሁም የጦርነት እርምጃ ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ትራምፕ "እነዚህ ሞኝ እና ተንኳሽ አስተያየቶች ከቃላት በላይ ከሆኑ በሚል እርምጃ ወስጃለሁ። ቃላቶች መሰረታዊ ናቸው እናም ብዙውን ጊዜ ወደማይፈለጉ ውጤቶች ሊመሩ ይችላለ። ይህ ከእነዚህ አጋጣሚዎች አንዱ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
ሩሲያ እና አሜሪካ በአለማችን የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችን በማከማቸት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሲሆን ሁለቱም አገራት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦች አሏቸው።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አርብ ዕለት ባሰፈሩት ጽሁፍ "የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዚዳንት እና የአሁኑ የአገሪቱ የጸጥታ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በሰጡት ቆስቋሽ አስተያየቶች ምክንያት ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦች በተገቢው ቀጣናዎች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በዚህ ማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ወይስ ኒውክሌር የታጠቁ የባህር ሰርጓጅ መርከቦች ማለታቸውን አልገለጹም።
ከዚህ ልጥፋቸው በኋላ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ትራምፕ "ዛቻ ተፈጽሞብናል፤ ይህም ተገቢ ነው ብለን አናስብም። ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ መውሰድ አለብኝ" ብለዋል።
"ይህንን ያደረግኩት በህዝባችነ ደህንነት መሰረት ላይ ተመርኩዤ ነው። በቀድሞው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ዛቻ ተፈጽሟል ። እናም ህዝባችንን እንጠብቃለን" ብለዋል።
የሩሲያ ባለስልጣናት በትራምፕ አስተያየት ላይ ምንም አይነት ይፋዊ ምላሽ አልሰጡም።
ትራምፕ እና የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ እርስ በርስ እየተዋረፉ ይገኛሉ።
ትራምፕ ለሩሲያ አቻቸቸው ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት እንዲቋጩ ነሐሴ 2/ 2017 ዓ.ም አዲስ ቀነ ገደብ ካስቀመጡ በኋላ ነው የሁለቱ ባለስልጣናት የቃላት ጦርነት የተጧጧፈው።
ፑቲን የትራምፕን ቀነ ገደብ ከቁም ነገር እንዳልቆጠሩት ተገልጿል።
ትራምፕ ከዚያ ቀደም ብሎ ተፈጻሚ ያልሆነ "የ10 ወይም የ12" ቀናት ቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር።
ከዚያ በተጨማሪም ፑቲን ጦርነቱን በ50 ቀናት ውሰጥ ካላቆሙ ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልካቸው ነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ያነጣጠረ ከባድ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።
ሩሲያን ከአውሮፓውያኑ 2008 እስከ 2012 የመሩት ሜዴቬዴቭ ትራምፕ ከሩሲያ ጋር "በቀነ ገደብ እየተጫወተ ነው" ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት አክለውም "እያንዳንዷ አዲስ ቀነ ገደብ ዛቻ እንዲሁም የጦርነት እርምጃ ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ከዚያ ቀደም ብሎም ትራምፕ ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ "ትያትር" ሲሉ ጠርተው "ሩሲያ ግድ የላትም" ብለዋል።
ሜድቬዴቭ ሐሙስ ዕለት በቴሌግራም ገጻቸው" የማያስፈልግ ዛቻ" ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን ይህንን ለመግለጽ የተጠቀሙበት "ዴድ ሃንድ" የሩሲያ አጸፋዊ የኒውክሌር ስርዓት ኮድ ስም መሆኑን አንዳንድ ወታደራዊ ተንታኞች ገልጸዋል።