ኢትዮጵያ ከዓለም 22ኛ ደረጃን በመያዝ ያለወርቅ ያጠናቀቀችበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

በጃፓን ቶኪዮ እየተካሄደ የነበረው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እሁድ ዕለት መስከረም 11/2017 ዓ.ም. ተጠናቋል።

በውድድሩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን 36 አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያ ማሳካት አልቻሉም።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኬንያ እና ካናዳ በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ውድድሩን በበላይነት አጠናቅቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ 20 ወርቅ፣ ኬንያ 7 ወርቅ እና ካናዳ በበኩሏ 3 ወርቅ ማግኘት ችለዋል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በሁለት ብር እና በሁለት ነሐስ ከዓለም 22ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

በዘንድሮው ውድድር ላይ የተመዘገበው ትልቁ ውጤት የብር ሜዳሊያ ሆኗል።

ኢትዮጵያ እአአ ከ1993 የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለወርቅ ሜዳሊያ ውድድሩን አጠናቅቃ ተመልሳለች።

በአንፃሩ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ተቀናቃኝ ኬንያ በመጨረሻው ቀን ውድድር ሰባተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች።

በዚህም የተነሳ ለጎረቤት ኬንያ ስኬታማ ከሚባሉት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አንዱ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በቶኪዮ ሻምፒዮና ሁለት የብር እና ሁለት ነሐስ ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች።

ከአራቱ ሜዳሊያዎች ሦስቱን ያስመዘገቡት ሴቶች ናቸው።

ትዕግስት አሰፋ በዘንድሮው ሻምፒዮና በሴቶች ማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች።

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ዮሚፍ ቀጄልቻ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።

በቡዳፔስት በተካሄደው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር አሸናፊ የነበረችው ጉዳፍ ጸጋይ በቶኪዮ ሦስተኛ ሆና አጠናቅቃለች።

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሲምቦ አላማየሁ የነሐስ አሸናፊ ለመሆን ችላለች።

በወንዶች ማራቶን ሦስቱም ኢትዮጵያውያን ውድድራቸውን አቋርጠው ወጥተዋል።

በወንዶች 3 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ለሜቻ ግርማ በዶሃ፣ በኦሪገን እና ቡዳፔስት የብር ሜዳሊያ ማሸነፉ ይታወሳል።

በዚህ ዓመት ግን ቶኪዮ ላይ የሜዳሊያ ተሸለሚ መሆን አልቻለም።

በሴቶች 800 ሜትር ትልቅ ተስፋ የተጣለባት እና የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ፅጌ ዱጉማም በፍጻሜው ላይ ሳይሳካላት ቀርቷል።

በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ጉዳፍ እና ሌሎች አትሌቶች ሜዳልያዎችን ማሳካት አልቻሉም።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሚጠበቀውን ያህል መሆን አልቻሉም።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ እና በፓሪስ ኦሊምፒክ የተገኙ ውጤቶችም በተመሳሳይ መነጋገሪያ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

ለረጅም ጊዜ ሲንከባልል የዘለቀውና ያልተፈታው ችግር የአትሌቶችን፣ የአሰልጣኞችን በዋነኛነትም የአገርን ውጤታማነት እያዳከመው ይገኛል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለ ወርቅ ከውድድሩ ስትመለስ ከ32 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያዋ ሆኖ ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለምንም የወርቅ ሜዳሊያ የተመለሰችው እአአ በ1991 በቶኪዮ በተካሄደው ውድድር ነበር።

በወቅቱ በተካሄደው 3ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ፊጣ ባይሳ በ5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ማሸነፉ ይታወሳል።

ከ1993 ጀምሮ ግን ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለ ወርቅ አጠናቅቃ አታውቅም።

በስቱትጋርት ሻምፒዮና አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በ10ሺህ ሜትር ወርቅ አሸንፏል። በ5 ሺህ ሜትር ደግሞ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።

ከ32 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ያለ ወርቅ ሜዳሊያ ከውድድሩ ተመልሳለች።