የተዘጉ ዳቦ ቤቶች እና በፈረቃ የሚከፋፈሉ የሕመም ማስታገሻዎች - የእስራኤል እርዳታ እገዳ በጋዛ

እስራኤል ወደ ጋዛ ማንኛውም እርዳታ እንዳይገባ ካገደች አንድ ወር ያለፈ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ ዳቦ ቤቶች በሙሉ መዘጋታቸው ተገለፀ።

በጋዛ የሚገኙ ገበያዎችም ቢሆን አትክልቶች አይገኙባቸውም። ሆስፒታሎች ለታካሚዎቻቸው የሕመም ማስታገሻዎች እና ፀረ ተህዋሲያንን መድሃኒት (አንቲባዮቲኮችን) በፈረቃ እያከፋፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።

እስራኤል ከሃማስ ጋር ለ18 ወራት እያካሄደችው ባለው ጦርነት ውስጥ የተጣለ ረዥሙ እገዳ ነው።

በዚህ ሳምንት በተከበረው የዒድ አል-ፈጥር በዓል ላይ ብዙ ጋዛውያን "ርቦናል" ሲሉ ተሰምቷል።

ከቤቴ ላሂያ የተፈናቀለችው ኡም አሊ ሃማድ በጋዛ ከተማ ምግብ እየፈለገች መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻ "ይህ ለእኛ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የከፋው ዒድ ነበር" ብላለች።

"መብላትም ሆነ መጠጣት አልቻልንም። መዝናናት አልቻልንም። ደክሞናል።"

"ከእንግዲህ እንደ ቲማቲም፣ ስኳር ወይም ዘይት ያሉ ነገሮች ማግኘት አንችልም። አይገኙም። በቀን አንድ ምግብ የማገኘው በመከራ ነው። አሁን የምግብ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች የሉም" ስትል አክላለች።

ሃማድ "አንድ የልጅ ልጅ ብቻ ነው ያለኝ፤ የተወለደው በጦርነቱ ወቅት ነው። ዕድሜው ሦስት ወር ቢሆነውም ወተትም ሆነ ዳይፐር ልናገኝለት አልቻልንም" ስትል ተናግራለች።

እስራኤል ሃማስ በጥር ወር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ ለማራዘም እና ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኗ እአአ ከመጋቢት 2 ጀምሮ ወደ ጋዛ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ እገዳ መጣሏን ተናግራለች።

ሃማስ በበኩሉ የሁለተኛ ምዕራፍ ድርድር ከዚህ በፊት ስምምነት በተደረሰበት መንገድ እንዲሆን በማለት በሕይወት ያሉ ታጋቾችን ለመልቀቅ፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ጠቅልሎ እንዲወጣ ጠይቋል።

እአአ ጥር 19 በተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት 33 እስራኤላውያን ታጋቾች እና 1,900 የሚጠጉ የፍልስጤም እስረኞች ተለቅቀዋል።

በተጨማሪም ወደ ጋዛ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ርዳታ መግባት ችሎ ነበር።

የእርዳታ ድርጅቶች እስራኤል በጋዛ ምግብ፣ መድኃኒቶች፣ የንጽህና ምርቶችን እና ነዳጅን ጨምሮ አስፈላጊ ሸቀጦችን እንዲገቡ እንድትፈቅድ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ግዴታዎችን አንድታከብር ኃያላን አገራትን ግፊት እንዲያደርጉ እየጠየቁ ነው።

አክሽን ኤይድ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ለአንድ ወር ያህል ምንም ዓይነት እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ መከልከሉን "አሳዛኝ" ሲል ገልጾ፣ "አዲስ የረሃብና የጥማት አዙሪት" እያንዣበበ መሆኑን ገልጿል።

ማክሰኞ ዕለት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በጋዛ ሁለት ሚሊዮን ለሚጠጉ ነዋሪዎች ለረዥም ጊዜ የሚበቃ በቂ ምግብ እንዳለ የተናገረችውን በመጥቀስ "አስቂኝ" ሲል አጣጥሎታል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ "አቅርቦታችንን እያሟጠጥን ነው" ብለዋል።

መተላለፊያዎችን የሚቆጣጠረው የእስራኤል ወታደራዊ አካል፣ ኮጋት በቅርቡ በተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ወደ 450,000 ቶን የሚጠጋ እርዳታን የጫኑ 25,200 የሚጠጉ የጭነት መኪናዎች ወዳ ጋዛ ገብተዋል ብሏል።

የእስራኤል ባለስልጣናት ሃማስ የእርዳታ እህል አቅርቦቶችን ለራሱ ያከማቻል ሲሉ ይከሳሉ።

ሆኖም ዱጃሪች የተባበሩት መንግሥታት "በሚያከፋፍላቸው ዕርዳታዎች ሁሉ በጣም ጥሩ የሆነ የቁጥጥር ሰንሰለት" እንዳለው ተናግረዋል።

በጋዛ ነዋሪ የሆኑት አቡ አላ ጃፋር "ዳቦ መጋገሪያውን መዝጋት ከፍተኛ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም ለእኛ በጣም አስፈላጊው ምግብ እርሱ ነው" በማለት ተስፋ በመቁረጥ ተናግረዋል።

"ያለ ዳቦ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም፤ ከዚህ በፊት ካየነው በጣም የከፋ ረሃብ ይኖራል።"

እርሳቸው እና ሌሎች የሰርጡ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአንድ 25 ኪሎ ግራም ዱቄት ዋጋ በ10 እጥፍ ጨምሯል።

እስራኤል ለብዙ ወራት የንግድ ዕቃዎች ሃማስን ይጠቅማሉ በሚል ወደ ጋዛ እንዳይገቡ ከልክላለች።

በጦርነቱ ምክንያት የአካባቢው የምግብ ምርት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሟል።

በዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚደገፉ ብዙ መመገብያ ጣብያዎች በቅርቡ ሥራቸውን ያቆሙ ቢሆንም፣ የዓለም ምግብ ድርጅት ግን ቢበዛ ለሁለት ሳምንታት ምግብ ማከፋፈሉን እንደሚቀጥል ይጠብቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ (UNRWA) ያለውን የምግብ ክምችት ለማጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀረው አስታውቋል።

እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን የአየር ድብደባ እአአ ከማርች 18 ጀምሮ ዳግም ቀጥላለች።

በአየር እና የምድር በሚፈጸመው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መጥተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ለ18 ወራት በዘለቀው ጦርነት በአሰቃቂ ሁኔታ ከተጎዱት ሆስፒታሎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አሁን ሙሉ በሙሉ ሞልተዋል ብሏል።

አክሎም የተሰበሩ አጥንቶችን ለማጠገን የሚረዱ መሳሪያዎች ማለቃቸውን ገልጾ፣ ለቆሰሉ ታካሚዎች ማደንዘዣ ፣ አንቲባዮቲክ እና ፈሳሾች እያለቁ መሆናቸውን አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አክሎም ለነፍሰ ጡር እናቶች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚያልቁ አስጠንቅቋል።

እስራኤል በጋዛ አዲስ ወታደራዊ ጥቃት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ቢያንስ 1,066 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ተገልጿል።

በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አንድ ሶስተኛው የሚሆኑት ደግሞ ሕጻናት ናቸው ሲል በሃማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት ተላላፊ በሽታዎችን ለመመርመር የሚረዱ ተቋማት በግዛቲቱ መዘጋታቸውን ጠቅሶ፣ ከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶችን እንደሚኖሩ አስጠንቅቋል።

የዓለም አቀፍ ድንበር የለሽ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር (ኤምኤስኤፍ) እስራኤል "ፍልስጤማውያን በጅምላ እየቀጣች ነው" በማለት እርምጃዋን እንድታቆም ጠይቋል።

የሕክምና ባለሙያዎች አንዳንድ ታካሚዎች የሕመም ማስታገሻ ሳይሰጣቸው እየታከሙ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሚጥል በሽታ ያለባቸው ወይም የስኳር ሕሙማን የሚያስፈልጋቸውን መድሃኒት በፈረቃ ለማከፋፈል መገደዳቸውን ተናግረዋል።

እአአ ጥቅምት 7 2023 ሃማስ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ በጋዛ ጦርነት ተቀስቅሷል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከ50,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አሸማጋዮች የተኩስ አቁምን ለማስቀጠል ጥረት እያደረጉ ነው።

ሃማስ ቅዳሜ ዕለት ከግብፅ የቀረበለትን አዲስ የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበሉን ሲገልጽ፣ እስራኤል በበኩሏ ከአሜሪካ ጋር በመመካከር አዲስ ምክረ ሃሳብ አቅርባለች።