ኢትዮጵያ ውስጥ "መገንጠልም፣ መጠቅለልም አይሠራም" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, EBC/YOUTUBE SCREENSHOT
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች "መገንጠልም፣ መጠቅለልም" አይሠራም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ። "ከሰሜን እስከ ደቡብ" ባለው የአገሪቱ ክፍሎች "ልገንጠል" በሚል የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ የገለጹት ዐቢይ፤ "አንዱም አገሩን አያውቅም" ሲሉ ተችተዋል።
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር የተሰማው በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ባደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት ወቅት በተካሄደ "ውይይት" ላይ ነው።
ሰኞ ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም. በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተላለፈው ይህ "ውይይት"፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደ ባሌ ዞን የተጓዙ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የቀድሞ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት ነው።
ሁለት ሰዓት ገደማ የሚጠጋው ይህ ውይይት በአብዛኛው ያተኮረው በባሌ ዞን የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ማልማት እና መጠቀምን በተመለከተ ነው። መጨረሻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም እንደ ሌሎቹ ተሳታፊዎች ሁሉ በአካባቢው ያለው ሀብት በሚገባው ልክ ባለመልማቱ የተሰማቸውን ቁጭት ገልጸዋል።
ዐቢይ በንግግራቸው "ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም፣ ሰላም መቅደም አለበት" የሚል ቅሬታ በተለያየ መንገድ እንደሚነሳ ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት አቋም፤ "ሰላም እንዲመጣ እንለምናለን፣ ሰላም እንዲመጣ እንሠራለን። ሰላም እስከሚመጣ ግን አንቀመጥም፤ እናለማለን" የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 100 ዓመታት ሰላም አልነበረም። አሁን ፌስቡክ እና ዩቲዩብ ስላለ፣ በየቀኑ ስለምንሰማው ነው እንጂ የበዛው ሰላም አልነበረም" ሲሉ ተደምጠዋል።
"ሽፍታ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠፍቶ አያውቅም" ያሉት ዐቢይ፤ ከነገሥታቱ ጀምሮ የነበሩ የአገር መሪዎች ጊዜያቸው "በዘመቻ" የተሞላ እንደነበር አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሥልጣን ዘመናቸው "ሽፍታ ለማሳደድ 100 ፐርሰንት የደከሙ መሪዎችን" ተችተዋል። የእርሳቸው መንግሥት "ሽፍታ ባህል ስለሆነ እያጠፋነው በአንድ እጃችን እናለማለን" የሚል አካሄድ እንደሚከተል ተናግረዋል። "ሰላም ከልማት ውጪ አይጸናም" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ኢትዮጵያ ትውልድ ተቀባብሎ የሚያጸናት አገር ትሆናለች። በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እንዳንድ አካባቢ የምናያቸው ጉዳዮች መልክ እየያዙ ይሄዳሉ" ብለዋል።
"'ልገንጠል' ብሎ ከሰሜን እስከ ደቡብ የተደራጀ ፓርቲ" መኖሩን ያነሱት ዐቢይ፤ ከእነዚህ አካላት ውስጥ "አንዱም አገሩን አያውቅም፣ ሕዝቡን አያውቅም፣ ባህሉን አያውቅ" በማለት ተችተዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ 'ልጠቅልል' የሚለውም ኢትዮጵያን አላወቃትም። 'ልገንጠል' የሚለውም ኢትዮጵያን አላወቃትም" ያሉት ዐቢይ፤ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን (ኦነግ) በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
"የእነ ጻድቃን ህወሓት 'ልገንጠል' በሚልበት ሰዓት፤ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ እነዚህ ወጣቶች በዚያ ዘመን ትግራይን፣ ባህሉን አያውቁትም። ያላቸው እልህ እና ቁጣ ነው እንጂ የበቃ እውቀት አልበነራቸውም" ብለዋል።
ኦነግ "እንኳን ኦሮሚያን መገንጠል ቀርቶ የትውልድ ስፍራውን እንኳን በትክክል አያውቀውም፤ ባሌን አያውቅም። ሌላውም ነጻ አውጪ ይኸው ነው፤ የሶማሌውም የምናምኑም..." በማለት ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
"ልጠቅልል ባዩም ዘመኑን አያውቅም" በማለት የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ብትፈልግም ባትፈልግም አይቻልም፤ አለፈ ያ ታሪክ። ከኋላ ጋር መታሰር አያስፈልግም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "መገንጠልም፣ መጠቅለልም አይሠራም። መስማማት፣ በትብብር ሁሉም ያለውን ሀብት እያወጣ እንዲለማ አድርጎ መኖር ብቻ ነው የሚያዋጣው። ይህንን መገንዘብ አለመቻል ነው ችግር ያመጣብን" ሲሉ በውይይቱ ላይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሃሳብ የሰነዘሩት የውይይቱ ተሳታፊዎች በተመለከቱት ነገር በእጅጉ መደነቃቸውን እና እንዲህ ያለው ሥራ በመላው አገሪቱ ተስፋፍቶ መከናወን ያለበት መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያለውን ሰላም ማስጠበቅ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
በውይይቱ ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተሳትፈዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም እንዲሁም የቀድሞው የክልሉ መሪዎች አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ ጁነዲን ሳዶ እና ወርቅነህ ገበየሁም የውይይቱ አካል ነበሩ።
የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤም ከተሳተፉት መካከል ናቸው።















