አሜሪካ ሐማስ በጋዛ ሰላማዊ ዜጎች ላይ "በተጨባጭ" ጥቃት ለማድረስ ተዘጋጅቷል አለች

አሜሪካ ሐማስ በጋዛ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጽመው ትቃት የተኩስ አቁሙን መጣስ ነው ብላለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሐማስ በጋዛ በሰላማዊ ሰዎች ላይ "በተጨባጭ" ጥቃት ለመሰንዘር ማቀዱን የሚገልጹ "አሳማኝ መረጃዎች" እንዳሉት አስታወቀ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ይጥሳል ብሏል።

ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ በፍልስጤማውያን ላይ ለመፈጸም የታቀደ ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነቱን "በቀጥታ እና በከባድ" ሁኔታ መጣስ ነው፤ እንዲሁም "በድርድር ጥረቶች የተገኘውን ከፍተኛ ውጤት የሚጎዳ ነው" ብሏል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ጥቃቱ ተጨማሪ ዝርዝር ነገር አልሰጠም፤ እንዲሁም የትኞቹን መረጃዎች እንደጠቀሰ ግልፅ አይደለም ።

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ነው።

ሁሉም በሕይወት ያሉ ታጋቾች የተለቀቁ ሲሆን የሟቾች አስከሬን ቀስ በቀስ እየተመለሰ ይገኛል።

በስምምነቱ መሠረት እስራኤል በእስር ቤቷ ውስጥ የሚገኙ 250 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እና ከጋዛ ያገተቻቸውን 1,718 ሰዎች ለቅቃለች።

ዋሽንግተን ግብፅ፣ ኳታርን እና ቱርክን ጨምሮ የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ታዛቢ ለሆኑ ስለ ሁኔታው እንዳሳወቀች እና ሐማስ የተኩስ አቁም ውሉን እንዲያከብር ጠይቃለች።

"ሐማስ በዚህ ጥቃት ከቀጠለ የጋዛን ሕዝብ እና የተኩስ አቁምን ኅልውና ለመጠበቅ እርምጃዎች ይወሰዳል" ሲል በመግለጫው ላይ ተገልጿል ።

በጉዳዩ ላይ ሐማስ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያ በተመለከተ ከዚህ ቀደም አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "ሐማስ በጋዛ ሰዎችን መግደሉን ከቀጠለ፣ ይህ ስምምነታችን አልነበረም፣ ገብተን ከመግደል ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖረንም" ብለው ነበር።

በኋላም የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ ጋዛ እንደማይልኩ ግልጽ አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንት ቢቢሲ በጋዛ በሐማስ ታጣቂዎች በአደባባይ የተፈፀመን ግድያ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተመልክቶ እውነተኛነታቸውን አረጋግጧል።

በቪዲዮዎቹ ላይ ብዙ ሰዎች ጠመንጃ ይዘው የሚታዩ ሲሆን፣ ስምንት ሰዎች ደግሞ እጆቻቸው ወደ ኋላ ተጠፍሮ ታስሮ አደባባይ ላይ ሕዝብ በተሰበሰበበት ሲረሸኑ ይታያል።

ቢቢሲ ጭንብል የለበሱ ታጣቂዎችን ማንነት ማረጋገጥ ያልቻለ ሲሆን፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ የሐማስ መለያ የሆነውን አረንጓዴ ጨርቅ ጭንቅላታቸው ላይ አስረዋል።

ቅዳሜ ዕለት እስራኤል እስካሁን በይፋ ማንነታቸው ያለየቻቸውን ሁለት የታጋቾች አስከሬን ከሐማስ ተረክባለች።

እስካሁን ድረስ ከሞቱት 28 ታጋቾች መካከል የአስሩ አስከሬን ብቻ ወደ እስራኤል ተመልሷል።