ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ109 ዓመታት በፊት በጠርሙስ የተላኩ ደብዳቤዎች ተገኙ
ሁለት አውስትራሊያውያን ወታደሮች የጻፏቸው ደብዳቤዎች ከ109 ዓመታት በኋላ ተገኙ።
ጠርሙስ ውስጥ የተገኙት ደብዳቤዎች የተጻፉት በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር።
ደብዳቤዎቹ የተገኙት በአውስትራሊያ ደቡብ ምዕራብ ባሕር ዳርቻ ነው።
ሁለቱ ወታደሮች ጦርነቱን ከመቀላቀላቸው ከቀናት በፊት ደብዳቤ ጽፈው ጠርሙስ ውስጥ አኑረዋል።
ማልኮም ኔቫል የተባለው ወታደር መርከብ ላይ የቀረበላቸው ምግብ "በጣም ቆንጆ" እንደሆነ በደብዳቤው ለእናቱ ገልጿል።
"በጣም ደስተኛ ነን" ሲል ለእናቱ መልዕክት ያስተላለፈው ወታደሩ፤ ደብዳቤውን በጻፈ በወራት ውስጥ በ28 ዓመቱ ተገድሏል።
ሌላኛው የ37 ዓመቱ ወታደር ዊልያም ሀርሊ ከጦርነቱ ተርፎ ወደ ቤተሰቡ ተመልሷል።
ደብዳቤዎቹ ለወታደሮቹ ቤተሰቦች ተሰጥተዋል።
በምዕራብ አውስትራሊያ የባሕር ዳርቻ ደብዳቤዎቹን የያዘውን ጠርሙስ ያገኘችው ደብ ብራውን "የባሕር ዳርቻውን ስናጸዳ ጠርሙሱን አየነው" ትላለች።
ከባለቤቷ እና ልጇ ጋር በባሕር ዳርቻ ሲንሸራሸሩ አካባቢውን የማጽዳት ልማድ አላቸው።
ጠርሙሱ ውስጥ ያለው ወረቀት በተወሰነ ደረጃ እርጥበት ቢያገኘውም ጽሑፉ በግልጽ ይነበባል።
ደብ ብራውን ደብዳቤዎቹን ካነበበች በኋላ የወታደሮቹን ቤተሰቦች አፈላልጋ አስረክባለች።
ማልኮም ኔቫል የእናቱን አድራሻ ደብዳቤው ላይ ስለጻፈ የቤተሰቡን የልጅ ልጆች ማግኘት ችላለች።
ደብዳቤውን የተረከበው ሐርቢ ኔቫል "ደብዳቤውን ስናይ ማመን አልቻልንም" ሲል ለኤቢሲ ኒውስ ተናግሯል።
ማሪያን ዴቪስ የተባለችው የወታደሩ የእህት ልጅ፤ አጎቷ ወደ ጦርነት ሄዶ አለመመለሱን ታስታውሳለች።
ደብዳቤውን ስትረከብ የተሰማትን ደስታ ለመግለጽ አልቻለችም።
የዊልያም ሀርሊ የልጅ ልጅ አን ተርነር "እኔና የተቀሩት አራት የልጅ ልጆቹ በጣም ነው የተደነቅነው" ብላለች።
"ተዓምር ነው የሆነብን። አያታችን ከመቃብር በታች እንዳነጋገረን ነው የተሰማን" ስትል ለኤቢሲ ኒውስ ተናግራለች።
"በጣም ስሜታዊ ሆኛለሁ። ያኔ ወጣት ሳለ ለእናቱ የጻፈው ደብዳቤ ነው። ከጦርነቱ ከተመለሰ በኋላ እናቱን አጥቷል" በማለትም አክላለች።
ወታደሮቹ ደብዳቤውን ጽፈው፣ ጠርሙስ ውስጥ አኑረው ባሕር ውስጥ ከተውታል።
አንድ የባሕር ጥናት ባለሙያ እንደተናገሩት፤ ጠርሙሱ ለ100 ዓመታት ባሕር ውስጥ ተቀብሮ ቆይቶ በስተመጨረሻ ተንሳፏል። ለቀናት በባሕሩ ከተጓዘ በኋላም በባሕር ዳርቻው ተገኝቷል።