ለረጅም ዓመታት ጃፓንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ሺንዞ አቤ ሲታወሱ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ለጃፓን የላይኛው ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩን ወክለው ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በብዙ መልኩ ይታወሳሉ።

“ጠብ አጫሪ” በሆነው የውጭ ፖሊሲያቸው እንዲሁም 'አቤኖሚክስ' ተብሎ በሚጠራው ለየት ያለ የምጣኔ ሀብት ስትራቴጂያቸው በጃፓን ስም አትርፈዋል።

ህያው ሥራ ከመቃብር በላይ ነው እንዲሉ፣ በርካቶች ሲገልጿቸው “ወግ አጥባቂ ብሔረተኛ ይሏቸዋል” የ67 ዓመቱን ፖለቲከኛ።

አቤ ፓርቲያቸውን ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲን (ኤልዲፒ) ሁለት ጊዜ አሸናፊ እንዲሆን አድርገውታል።

የመጀመሪያው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቆይታቸው አጭር ነበር። በአውሮፓውያኑ 2006 ወደ ሥልጣን መጥተው አንድ ዓመት አካባቢ አገሪቱን የመሩት አቤ የሥልጣን ቆይታቸውም አወዛጋቢ ነበር።

ነገር ግን ከስድስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2012 በአስገራሚ ሁኔታ ተመልሰው በጤና ምክንያት ከሥልጣን እስከለቀቁበት 2020 ድረስ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።

አቤ ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ አገራቸው የምጣኔ ሀብት ድቀት ላይ ነበረች። የገንዘብ ፖሊሲውን በማላላት፣ ማነቃቂያዎች እንዲሁም መዋቅራዊ የሆኑ ማሻሻዎችን በማድረግ እያሽቆለቆለ የነበረውን ምጣኔ ሀብት ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንደሚመጣ አድርገዋል ተብለው ይወደሳሉ።

ጃፓን በአውሮፓውያኑ 2011 በቶሁኩ ከደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት እንዲሁም ሱናሚ እንድታገግም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

በዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሱናሚ ወደ 20 ሺህ የሚደርሱ ጃፓናውያን ሕይወት ከመቅጠፍ በተጨማሪ የፉኩሺማ የኒውክሌር ማመንጫዎችን አቅልጦ ከፍተኛ ቀውስ አድርሷል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2020 አቤ በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው ወረዱ። ለሳምንታት ያህል የጤናቸው ሁኔታ መወያያ ከሆነም በኋላ ነበር ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት።

መጀመሪያም ከስድስት ዓመት በፊት ሥልጣን በለቀቁበት ወቅት በአንጀት አልሰር (ቁስለት) ህመም ሲሰቃዩ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት ይህ ቁስለት ማገርሸቱን አስታውቀው ነበር።

እሳቸውንም በመተካት የፓርቲያቸው አባልና የቅርብ አጋር የሆኑት ዮሺሃዴ ሱጋ ወደ ሥልጣን መጡ። ሆኖም አቤ በጃፓን ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው ሰው ተደርገው መታየታቸው አላከተመም።

አቤ ወደ ሥልጣን እንዴት መጡ?

አቤ ከፖለቲከኛ ቤተሰብ ነው የመጡት። አባታቸው የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም አያታቸው ደግሞ ጃፓንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ኖቡሱኬ ኪሺ ናቸው ።

ለፓርላማ አባልነት የተመረጡት በአውሮፓውያኑ 1993 ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2005 የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁኒቺሮ ኮይዙሚ ከፍተኛ የካቢኔ ፀሐፊ አድርገው ሾሟቸው።

ከዚያም በአውሮፓውያኑ 2006 ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በዕድሜ የጃፓን ትንሹ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ቻሉ።

ነገር ግን አስተዳደራቸው በተከታታይ ቅሌቶች የተሞላ ነበር። ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ጉዳዮችን የያዘው የመንግሥት የጡረታ መዝገብ መጥፋት አስደዳደራቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2007 ለተደረገው የላይኛው ምክር ቤት ምርጫም ፓርቲያቸው ኤልዲፒ ከባድ ኪሳራን አስተናገደ። በዚያው ዓመትም በአንጀት አልሰር (ቁስለት) ምክንያት አቤ ከሥልጣናቸው ለቀቁ።

ከስድስት ዓመት በኋላም በህክምና በሽታውን አሸንፌያለሁ በማለት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ተመለሱ።

በመቀጠልም በነበሩት ምርጫዎች በአውሮፓውያኑ 2014 እና 2017 በድጋሚ ተመርጠዋል። ይህም ለረጅም ዓመታት ጃፓንን የመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደርጋቸዋል።

ተወዳጅነታቸውም በዓመታት ውስጥ ቢለዋወጥም በፖርቲያቸው ኤልዲፒ ውስጥ በነበራቸው ከባድ ተፅእኖ ምክንያት የተገዳደራቸው አልነበረም። የፓርቲያቸውንም ደንብና ሕግ በማሻሻል ለሦስተኛ ጊዜ የፓርቲው መሪ ለመሆን ችለዋል።

አወዛጋቢው ብሔረተኛ

አቤ በመከላከያ እና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቁርጠኛና 'ጠብ አጫሪ' የሚባል አቋም ነበራቸው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ሰላማዊ የሚባለውንም የጃፓን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ሲጥሩ ቆይተዋል።

በአሜሪካ የተረቀቀውን የጃፓን ሕገ መንግሥት ወግ አጥባቂዎች፣ የጃፓን ወታደሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደረሰባቸውን አሳፋሪ ሽንፈት ማስታወሻ ነው ሲሉ ይተቹታል።

ጭፍን ብሔረተኛነታቸውም ከቻይና እና ከደቡብ ኮሪያ ጋር ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል። በተለይም በሁለተኛው ከዓለም ጦርነት በፊትና በዚያው ወቅት ጃፓን ነበራት ከሚባለው የጦረኝነት አቋም ጋር ተያይዞ አወዛጋቢ የሆነውን በቶኪዮ የሚገኘውን ያሱኩኒ ቤተ መቅደስ በአውሮፓውያኑ 2013 መጎብኘታቸውን ተከትሎ ከሁለቱ አገራት ጋር ነገሮች ተጋግለው ነበር።

አቤ ያሱኩኒን በተደጋጋሚ መጎብኘታቸውም በጃፓን የሚገኙ የግራ ዘመም ፖለቲከኞችን ያስቆጣ ነበር። አቤ በጦርነቱ ወቅት ጃፓን ያደረሰችውን የመብት ጥሰቶችና ጭካኔዎች ለማንፃት እየሞከሩ ነው ብለዋቸዋል።

የጃፓንን ሰንደቅ አላማ የያዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የጋራ የራስ መከላከል መብት የሚል ፅንሰ ሃሳብ በማስተዋወቅ ሰነዱ ተቀባይነት እንዲያገኝ በአውሮፓውያኑ 2015 ይከራከሩ ነበር። ይህም ጃፓን እንዲሁም ጥቃት የደረሰባቸውን አጋሮቿን ለመካላከል በውጭ አገራት ወታደሮችን እንድታሰማራ የሚል ነው።

ይህ ሰነድ ከጃፓን ጎረቤት አገራት እንዲሁም ከጃፓን ሕዝብ እንኳን ሳይቀር ተቃውሞ ቢገጥም የአገሪቱ ፓርላማ ይህንን አወዛጋቢ ዕቅድ አጸደቀው።

ሆኖም የጃፓንን ጦር እንደገና ለማወቀር ሕገ መንግሥቱን የመከለስ ትልቁ አላማቸው አልተሳካም ነበር። እናም በአሁኑ ወቅትም ይህ ዕቅዳቸው በአገሪቱ ውስጥ ከፋፋይ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።

በተጨማሪም ጃፓን ሰሜናዊ ግዛቶቼ ብላ የምትጠራቸውን ቦታዎችን ማስመለስ አልቻሉም። ይህ ቦታ ጃፓን እና ሩሲያ ይገባኛል ብለው የሚወዛገቡባበቸውና በሰሜናዊ የሆካይዶ ግዛት ውስጥ ያሉ የደሴቶች ሰንሰለትን ይሸፍናል።

አቤ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፣ አሜሪካ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለችውን አስከፊ የንግድ ታሪፍ በጃፓን ላይ ተግባራዊ እንዳይሆን ተከላክለዋል በሚልም በበጎ ይነሳሉ።

የጃፓንን ምጣኔ ሀብት የማስመንደግ ጉዞ

'አቤኖምክስ' በመባል የሚታወቀው የአቤ ለየት ያለ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው እድገት እንዲታይ እንደረዳቸው ታይቷል።

ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ነጌቲቭ (አሉታዊ) የወለድ ተመን በማስተዋወቅ ሸማቾች እና ኩባንያዎች ገንዘብ እንዲበደሩና እንዲያወጡ ረድቷቸዋል።

የመንግሥት ወጪን በመሰረተ ልማት ላይ ማሳደግ፣ የግብር እፎይታን የመሳሰሉ ማበረታቻዎችንም አመጡ።

በተጨማሪም በርካታ ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም እንዲመጡና የጉልበት ጫናን ለማቃለል ስደተኞች ወደ ሥራ እንዲገቡ የመሳሳሉ በርካታ ስር ነቀል ማሻሻያዎችን አመጡ።

ነገር ግን ጥረታቸው ፈተና ገጠመው። በተለይም በአውሮፓውያኑ 2020 ጃፓን እንደገና ምጣኔ ሀብቷ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ዘላቂነቱና ውጤታማነቱ ላይ ጥያቄ ተነሳባቸው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ስልጣን መልቀቃቸውን ሲያስታውቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በምጣኔ ሀብት ፖሊሲያቸው ዘላቂነት ላይ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበረው አቤ፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ አያያዛቸው ጋርም ተያይዞ ስጋቶች መነሳት ጀመሩ።

ተቺዎቻቸው እንደሚሏቸው የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ በሚል ያደረጓቸው ዘመቻዎች ወረርሽኙ እንዲባባስ አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለው ያምናሉ።

ሌሎች በአቤኖሚክስ ፖሊሲ የተገቡ ቃሎች ለምሳሌ ተጨማሪ ሴቶችን በሥራ ኃይል ማብቃት፣ ወገንተኝነትን መዋጋት እና ጤናማ ያልሆኑ የሥራ ባህሎችን መለወጥ ሳይፈጸሙ ቀርተዋል ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በ11 አገራት መካከል የተካሄደውን ግዙፍ የንግድ ስምምነት፣ ትራንስ ፓስፊክ ፓርትነር ሺፕ፣ በተለይም በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገዛዝ ዘመን አሜሪካ በድንገት መውጣቷን ተከትሎ አጋርነቱን በማስጠበቅ ዕውቅና ተችሯቸዋል።

ከሥልጣን መልቀቅ እና ሞት

አቤ ከሥልጣን የለቀቁት ከሁለት ዓመት በፊት ነሐሴ መጨረሻ ገደማ በአውሮፓውያኑ 2020 ነበር። ተተኪ ባለመምረጣቸውም በፓርቲያቸው ኤልዲፒ ውስጥ ባሉ አንጃዎች መካከል የውስጥ ትግል አስከተለ።

በመጨረሻም በአንጋፋው ፖለቲከኛ እና የረዥም ጊዜ የካቢኔ አባል በሆኑት ዮሺሂዴ ሱጋ ተተኩ።

ነገር ግን አቤ በጃፓን የውስጥ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ቦታ ነበራቸው። ሱጋ በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ቢተኩም የአቤ በፖለቲካው ላይ የቁንጮነት ቦታ አልተነካም።

በዛሬው ዕለት አርብ ሐምሌ 01/2014 ዓ.ም አቤ በደቡባዊ ናራ ከተማ ለጃፓን የላይኛው ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩን ወክለው ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር።

ንግግር እያደረጉ ባለበት ወቅት በአንድ ታጣቂ በጥይት ተመቱ። የተኮሰባቸው የ41 ዓመቱ ግለሰብ በጃፓን እንደ ባሕር ኃይል የሚታየው የራስ መከላከያ ኃይል የቀድሞ አባል እንደሆነም ይታመናል።

አቤ በጥይት ተመትተው ሲወድቁና ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱም ራሳቸውን ያውቁ ነበር። ነገር ግን ከደረሰባቸው ጉዳት አላገገሙም፤ ላይመለሱ አሸለቡ።