“በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ የታቀዱ የሽብር ጥቃቶች ከሽፈዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, pm office
በዚህ ሳምንት ብቻ በአዲስ አበባ ከስድስት በላይ የሽብር ጥቃቶች መክሸፋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
በዛሬው ዕለትም አሶሳ ላይ የሽብር ጥቃት የመፈጸም እቅድ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄ አስመልክቶ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው የተናገሩት።
የዛሬው ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሎን ረዘም ባለ መልኩ የፈጀው ከሰሞኑ በቄለም ወለጋ የደረሰውን ጭፍጨፋ ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ በደረሱ የጅምላ ግድያዎች ላይ አተኩሯል።
ከፓርላማ አባላትም ዘንድ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋ እልባት የሚያገኘው መቼ ይሆን? የመንግሥት መዋቅሮች ተሳትፎ አለበት? የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ችላ ብለውታልና ሌሎች ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን የጀመሩት በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ፣ ለተገደሉ ንጹሃን ዜጎች የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ነው።
“ሕይወታቸውን ለመታደግ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ መንግሥት ባለመቻላችን ጥልቅ ሐዘን ይሰማናል” ብለዋል።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የደረሰው ጥቃት ኢላማ ያደረገው ከወሎ ወደ ወለጋ በ1977 ዓ.ም ረሃብ ወቅት ወደ ስፍራው የሄዱትን ሲሆን፣ እነዚህ ግለሰቦች ለአስርት ዓመታት የኖሩበትና ቀያቸው አገራቸው ነው ብለዋል።
ሰሞኑን በሕዝብ ላይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ባሻገር “በአዲስ አበባ በዚህ ሳምንት የታቀዱ የሽብር ጥቃቶች ከሽፈዋል” ብለዋልጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
“እነዚህን ሰዎች በግፍ መግደል የሚያሳካው የፖለቲካ አላማ የለም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሹ ወገኖች የደቀኑት አላማ ማሳያ ነው” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ላይ በየቀኑ ሰፋፊ ጥቃቶች ታቅደው ቦምቦች፣ መሳሪያዎች፣ መሳሪያዎችና የሰለጠኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ከሦስት ቀን በኋላ ሃምሳ አምስት ሰዎች ወደ ከተማዋ ለመግባት ሲሞክሩ ለገጣፎ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስረድተዋል።
በትናንትናው ዕለትም በቁጥጥር የዋሉ እንዳሉም አስረድተዋል።
የፀጥታ ኃይሎች ቸልተኝነት አሳይተዋል?
ከሰሞኑ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ በንጹሃን ዜጎች ላይ በደረሱ የጅምላ ግድያዎች የመንግሥት ፀጥታ ተቋማት በቸልታ እየተመለከቱት ነው፤ እንዲሁም ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚለው አስተያየት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይስማሙም።
“በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸውን እየገበሩ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች መስዋዕትነት ከመክፈላቸው በተጨማሪ በዝቅተኛ ደመወዝና በፈታኝ ሁኔታ እየሰሩ ነው ብለዋል።
“ዜጎቻቸውን ለመታደግና ሕዝባቸውን ስለሚወዱ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው” በማለትም አክለዋል።
ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት በደራሼ ላይ በነበረው ግጭት ፖሊስና የአካባቢው አስተዳሪዎች ከ80 በላይ ሞተዋል፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች በርካታ የፀጥታ ኃይሎች እንደተገደሉም ገልጸዋል።
በዚህም በርካታ ዜጎችን መታደግም እንደተቻለ አበክረው ተናግረዋል።
ሆኖም "የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈሱ የትኛውም ስብስብ ሸኔም ይሁን የትኛውም አሸባሪ ኃይልን ለማጥፋት በጀመርነው ጥረት የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋሉ።" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል።
“አሸባሪዎች የራሳቸው ጭንቅላት የላቸውም ታስቦ ሥራ ሲሰጣቸው ጥቃት ይፈፅማሉ፣ ሕዝቡ አሸባሪውን ከለየ በኋላ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ጥፋት እንዲቀንስ ማድረግ ይኖርባታል። የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈስ የትኛውም አሸባሪ ኃይል እስኪጠፋ የጀመርነው እርምጃ ይቀጥላል” ሲሉም አጠናክረዋል።
የመንግሥት መዋቅር ተሳትፎ በጥቃቱ ውስጥ?
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በደረሱ ጥቃቶችም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ተሳትፎ አለበት በሚል የተለያዩ አካላት ወቀሳዎችን ሲያቀርቡ ተሰምቷል። በዛሬውም ዕለት አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ይህንን ጉዳይ ያነሱ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የተገዙ ሰዎች አሉ" ሲሉ “መዋቅር ውስጥ ችግር አለ” በማለት አምነዋል።
ከዚህ ቀደም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ 5 ሺህ ያህል የተባረሩ፣ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው የማጥራት ሥራው እንደሚቀጥልም በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
በጅምላ ግድያዎቹ ላይ የተጠረጠሩ ሰዎች ምን ያህል ለፍርድ ይቀርባሉ በሚል በርካታ የፓርላማ አባላት የሽብር ህጉን አንቀፅ እየጠቀሱ ጥያቄ አቅርበዋል።
በባለፉት ዓመታት በተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች ላይ 11 ሺህ ክስ መቅረቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ከሙዚቀኛ ሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ በደረሱ ጥቃቶች በሺዎች ላይ ክስ ቀርቦ በብዙዎች ላይ መፈረዱንም አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, pm office
“ሸኔን ለማውገዝ አይደፍሩም”
ከሰሞኑ የደረሱ ጥቃቶችን ያደረሰው መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው በማለት መንግሥትና ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ ጥቃቱ በመንግሥት ታጣቂዎች የተፈጸመ ነው በማለት አስተባብሏል።
"ሸኔ የሚያደርሳቸውን ጥቃቶችን አላወገዙም የሚል ሃሜት ይቀርብብዎታል?" ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄው ተገቢ አይደለም ብለዋል።
"ሃሜት በምክር ቤት አባላት መቅረቡ ተገቢ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሸኔን አሸባሪ ያለው ይህ ምክር ቤት ሳይሆን እኛ ነን፤ ቸል እንዳልነው አታስመስሉት” ሲሉም ወቅሰዋል።
በቅርቡ አባቱን ያቃጠለ የሸኔ አባልን ጠቅሰው እንዲሁም ልጆቻቸውን ወደ ጦርነቱ የላኩ ቤተሰቦችን የገደሉ የሸኔ አባላት አሉ በማለት “እንደነዚህ አይነት አውሬዎች የኦሮሞ ተወካይ አይደሉም። ህፃናትንና ቤተሰብን የሚገድሉት አካላት የፖለቲካ አላማ የላቸውም፣ አገርም ማስተዳደር አይችሉም” ብለዋል።
ጉዳዩን ከዘር (ብሔር) ጋር የምታይይዙ ሰዎች ሸኔ በኦሮሞነቱ ብቻ ሳይሆን “የኦሮሞ ጠላት ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ከተሰለፉት ውስጥ ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ከደቡብና ከትግራይ የማረክናቸው አሉ በማለት “ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ጠላት ሁሉ ስብስብ ነው” ብለዋል።
ወለጋ ላይ በመቶ የሚቆጠሩ የወረዳና የዞን አመራሮች መገደላቸውን በመጥቀስ እንዲሁም ወለጋ ላይ የሚሰሩ መሠረተ ልማቶች መቆማቸውን በማንሳት የኦሮሞ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው ብለዋል።
"ብልጽግናን “እኛን” በብሔር መነጽር ማየቱ ትክክል አይደለም" ሲሉ በወቀሳ መልኩ ተናግረዋል
“በሰፈር የተደራጃችሁና ያልኖራችሁበትና በዘር ለማየት የምትፈልጉ ትክክል አይደለም። እኛ ከዘር በላይ ነን። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርባት አገር ነው የምንፈልገው። እኛ ኢትዮጵያዊ ነን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጨምረውም “ሳናቅ የምናበላሸው ነገር ካለ በእናንተ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብና በእናቶች ምክር እንታረማለን እንጂ ሆን ብለን አንዱን ብሔር የበላይ በማድረግ የማፋጀት ሥራ አንሰራም” ብለዋል።
ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ የጋረጠው ፈተና
ሽብርተኝነት ዓለም አቀፉ ፈተና እንደሆነ ለምክር ቤቱ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለኢትዮጵያ ተለይቶ የሚያጋጥማት ፈተና አይደለም ብለዋል።
በበርካታ አገራትም ቀዳሚና ዋነኛም አጀንዳም እንደሆነ ጠቅሰው፣ ጠንካራ የፀጥታ ኃይል፣ የላቀ ቴክኖሎጂና ሃብታም በሆኑ እንደ አሜሪካ ያሉ አገራትም ሽብርተኝነት እየፈተናቸው ነው ብለዋል።
ሽብርተኝነት በዓለም ላይ ባሉ ሃገራት የሚከሰትና የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች መግታት ያልቻሉት የሚል አንድምታ መሰጠት የለበትም ብለዋል።
"ሽብርን መገንዘብ ያስፈልጋል" የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት በተሻለ መንገድ መረጃ ስላለው የተሻለ ሥራ መስራት እንደሚችል ሕዝቡ መገንዝብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የመከላከያና የፀጥታ ኃይል ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው በላይ ቁመና ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም የሆነው አገሪቷ የሽብር ጥቃት ስለተደቀነባት እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይህንንም በመገንዘብ መከላከያን፣ ፖሊስን፣ የፌደራል ፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች ተጠናክረዋል ብለዋል።
እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች በሚጠናከሩበት ወቅት ከዘር፣ ከእምነት እና ከፖለቲካ አመለካከት ነፃ በሆነ መልኩና በጥቅም እንዳይገዛ ባደረገ ሁኔታ ተጠናክሮ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
“ትናንት ከነበረው በተሻለ ሁኔታና በማይወዳደር መልኩ በደህንነት ተቋማት ላይ ባተኮረ መልኩ ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆንና ኢትዮጵያን በሚታደግ መልኩ ተገንብቷል” ብለዋል።
በዚህም 95 በመቶ ተሳክቶለታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም መቶ በመቶ ማድረግ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።
"በየትኛውም አገር የሽብር ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልተቻለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያም ከዚያ ማዕቀፍ ውጭ ባትሆንም አገሪቱ መከላከል፣ መከታተል፣ መጠበቅ፣ መዘጋጀት በሚሉ አራት ዕቅዶችን ይዛ እየተንቀሳቀች ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት ግራጫ ነው”
የኢትዮጵያን ፈተና በሁለት ፈርጆች መታዬት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም ያላት አስተዋፅኦና ኢትዮጵያ ለማደግ ያላት አቅም ነው” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት የግራጫ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም ሲያብራሩ የመረጃ ጦርነት አንደኛው ነው ብለዋል።
ጭፍጨፋዎች ወይንም ግድያዎችን አጀንዳ ያደረገና የኢትዮጵያን ልማት ባላየ መልኩ የመረጃ ጦርነት ይደረጋል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም አገሪቱ የተከፈተባት መጠነ ሰፊ ጥቃት ነው ይላሉ።
በተጨማሪም ዲፕሎማሲያዊ፣ የሳይበር ጥቃትና የተልዕኮ ውጊያም እንደተጋረጠባት አስረድተዋል።
በተልዕኮ ውጊያ “እግር አልባ ባንዳዎች” ብለው የጠሯቸው ኃይላት የሕዝቡን ስሪት እያፈራረሱ ነው በማለት፣ በዚህም አማራና ኦሮሞን ማፋጀት፣ አማራን እርስ በርስ፣ ኦሮሚያን እርስ በርስ፣ ሶማሌና አፋርና፣ እንዲሁም ክርስቲያንና እስላምን ማፋጀት በዋነኝነት አጀንዳቸው ነው ይላሉ።
"ሰው አብሮ ከተዋለደው፣ ከኖረው ጎረቤቱ ጋር ጠላት መሆን አይቻልም። አማራና ኦሮሞ በጠላትነት ተሳስበው መቀጠል አይቻልም።" በማለትም የማህበረሰቡን ስሪት አስረድተዋል
“በዚህ ሁሉ መጠነ ሰፊ ጥቃት ኢትዮጵያን ማፍረስ አልተቻለም። ኢትዮጵያን ማጋደል፣ ማሸበር፣ በኢኮኖሚ ጫና ለማንበርከክ ቢሞከርም ማፍረስም አይቻልም” ብለዋል።
"ሆኖም የኢትዮጵያ ጠላቶች አጥብቀው አይተኙም" በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።
“በየቀኑ እየተወጋን፣ መስዋዕትነት እየከፈልን፣ በማይታመኑ ነገሮች ውስጥ እያለፍን ቢሆንም እየጠነከርን ነው፤ ወደፊት እየተጓዝን ነው።”
"ከማበልጸግና አገር ከማሻገር አላማችን ንቅንቅ አንልም አስፈላጊ ከሆነም መስዋዕት እየከፈልን፣ በየቀኑ እየቀበርን፣ የሕፃናቱ ደም ቢጣራም በዚህ ፈተና ውስጥ እናሸንፋለን፤ ኢትዮጵያ ዳገት ላይ ናት” ሲሉ አስተዳደራቸው እያለፈበት ያለውን ሁኔታ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
የገዢው ፓርቲ ለመደራደር መወሰን
ሌላኛው ከምክር ቤት አባላት የቀረበው ጥያቄ ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ከህወሓት ጋር ድርድር ማድረግ ብቻውን ለምን ወሰነ? የሚል ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሲመልሱ ገዥው ፓርቲና ሕዝቡ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላም ነው ብለዋል።
የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ደኅንነትን በሰላም ለማስጠበቅ ካልተቻለ ብቻ ነው ወደ ጦርነት የሚገባው በማለት “ሰላምን እንዴት እንጠላለን” ሲሉም ጠይቀዋል።
ሆኖም ለውይይቱ አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተወያዩም አስታውሰዋል።
ህወሃት በፓርላማ አሸባሪ ተብሎ ከመፈረጁም ጋር ተያይዞ “ከአሸባሪ ጋር ድርድር አይካሄድም የሚለውን በጥልቀት ሊታይ ይገባል ብለዋል። በርካታ አገራት በጦርነት ወቅት ሆነው አሸባሪ ብለው ከፈረጇቸው አካላት ጋር ድርድር እንደሚያደርጉም የተለያዩ ሃገራትን ተሞክሮ ጠቅሰዋል።
ሁልጊዜም ድርድር ይደረጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደርግ ከህወሓትና ከሻዕቢያ ጋር ያደረገውን ድርድር በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
የሽግግር መንግሥት ምስረታ
ሌላው በምክር ቤት አባላቱ የተነሳው ጥያቄ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ያስፈልጋታል የሚሉ አካላትን አስመልክቶ ነው።
የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን የሚጠይቁ ሥርዓት የማፍረስ አደጋ አልታያቸውም ብለዋል።
“የሽግግር መንግሥት ሃሳብ የሚያነሱ ግለሰቦች ቀበሌ መርተው የማያቁና ስለተቋምም የማያቁ ናቸው” ሲሉ ተችተዋል።
ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ ማቋቋምን ጨምሮ፣ በምርጫ እንዲወዳደሩ መድረክ ክፍት በማድረግ ምህዳሩ ሰፍቷል ብለዋል።
"ያለፈው ምርጫ በዲሞክራሲያዊነቱ እስካሁን ካለው የተሻለ መሆኑን ዓለም መስክሮከለታል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ምርጫም ብልጽግና በከፍተኛ ድምፅ መንግሥት መመስረት ችሏል ብለዋል።
“ሆኖም ከተሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማምጣት አብረን እንስራ በሚል ብልጽግና ሥልጣን አጋርቷል” ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህም ተግባሮች ተከናውነው ችግሮች ባለመፈታቱ እየተንከባለሉ ያሉ ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ እንዲፈታ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መቋቋሙን በማንሳት “በሕዝብ ድምፅ የመጣ ኃይልን በጋጋታ ማፍረስ አይቻልም” በማለት አስረድተዋል።












