“በቄለም ወለጋው ጥቃት ሕጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያንን ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል” የዐይን ምስክሮች

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዛ የምታለቅስ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተፈፀሙ ያሉ ግድያዎችን በመቃወም በውጭ አገር ሰልፎች ተካሂደዋል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሃዋ ገላን ወረዳ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የዐይን እማኞቹ ትናንት ሰኞ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም ከማለዳው 12፡00 ገደማ እስከ ረፋድ 4፡00 ሰዓት ድረስ በዘለቀው ጥቃት በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል ብለዋል።

የሟቾች አስክሬን ገና እየተሰበሰበ በመሆኑ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር በትክክል መግለጽ ያልቻሉት የዐይን ምስክሮቹ፣ ሕጻናትን ጨምሮ ከ150 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ምሽት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በወለጋ በዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሸኔ የሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድን በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው በቄለም ወለጋ፣ ማቻራ የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች "በአገዛዙ ታጣቂዎች ነው" ያሉ ሲሆን "ስፍራውን የተቆጣጠሩት የመከላከያ ሰራዊትና አጋር ኃይሎች ምንም አላደረጉም" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በተጨማሪም "ገዥው አካል ጣቶቹን በመቀሰር ከተጠያቂነት ለማምለጥ እየሞከረ ነው" ሲሉም ወቅሰዋል።

ይህ መቀጠል የለበትም ሲሉ ያሰፈሩት ቃለ አቀባዩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አካላት ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲደረግም አፅንኦት ሰጥተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈፀመ ስላሉት ጭፍጨፋ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ አላሰፈሩም።

ትናንት የተፈፀመው ጥቃት፣ በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር አባላት ላይ ጭፍጨፋ ከተፈፀመ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሆነ ነው።

በዚህ ጥቃት ከተገደሉ ሰዎች አብዛኞቹ ህጻናትና ሴቶች መሆናቸውም ተገልጿል።

መንግሥት በቶሌ ቀበሌው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 338 መሆኑንና ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጿል።

የዐይን እማኞች ቁጥሩ ከተገለጸው በላይ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በአሜሪካ የአማራ ማኅበር የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ወደ 600 እንደሚጠጋ እና የ455 ሟቾችን ስም መለየት እንደቻለ አመልክቷል።

ትናንት ሰኞ በቄለም ወለጋ የተፈፀመው ጥቃት፣ በቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች በተቀናጀ የፀጥታ ኃይል ቁጥጥር ሥር ሙሉ በሙሉ መግባታቸውን የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ካስታወቀ ከአምስት ቀናት በኋላ ነው።

ቄለም ወለጋ ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ትናንት ቢቢሲ ያናገራቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ፣ ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትን አግኝቶ ለማነጋገር የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራም አልተሳካም።

ቢቢሲ ስለጥቃቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑትን ዶክተር ዳንኤል በቀለን ጠይቆ፣ተቋሙ ጥቃት ስለመፈጸሙ እንደሚያውቅ ተናግረዋል።

ነገር ግን ስለተከሰተው አጠቃላይ ሁኔታ ዝርዝር ለማግኘት ከጥቃቱ ከሸሹ ሰዎች መረጃ እያሰባሰቡ እንደሆነ እና የተፈጸመውን ጥቃት ኮሚሽኑ እየተከታተለው እንደሆነ አመልክተዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት አካባቢ በአገሪቷ በ1977 ዓ.ም. የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በመንግሥት እንዲሰፍሩ በተደረጉ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የአማራ ብሔር ተወላጆች መኖሪያ መንደር ነው።

ስለጭፍጨፋው ከዐይን እማኞች አንደበት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያናገራቸው የዐይን እማኞች ጥቃቱ ሰኞ ማለዳ ከ11፡30 ጀምሮ መንደር 20 የሚባለውና ብዙ የአማራ ተወላጆች ባሉበት አካባቢ መፈፀሙን ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሲፈፀም በአካባቢው ሚሊሻዎች እንጂ ሌሎች የፀጥታ አካላት እንዳልነበሩ የገለጹት የዐይን እማኞቹ እስከ ረፋዱ 4፡00 ድረስ ተኩሱ እንዳላባራና ተኩሱ ከሚሊሻዎቹ አቅም በላይ እንደነበር ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና አብዛኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች የወራት እድሜ ያላቸው ጨቅላ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከጥቃቱ እንደተረፉ የሚናገሩት የዐይን ምሥክር “አስክሬን ገና ለቅመን አልጨረስንም። በረሃ ላይ ወስደው ሰው ጨፍጭፈዋል፤ መስጊድም የተሰበሰበ አስክሬን አለ። ሐኪሞች መጥተው ማድረቂያ አድርገውልን ሄደዋል። የሚታየውን ነገር ለመግለጽ ይከብዳል” ብለዋል።

ጭፍጨፋው በቦምብ፣ በስለት እና በጥይት እንደተፈፀመም የዐይን እማኙ አክለዋል።

በጥቃቱ ከ45 በላይ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውንና ሆስፒታል ከገቡት ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈ እንዳለም የዐይን እማኙ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በንብረት ላይ ዘረፋ እና ውድመት መፈፀሙን ገልጸው፣ ከ50 እስከ 70 የሚሆኑ ቤቶች መቃጠላቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው የመንደር 10 ነዋሪ እና ተኩሱ ካባራ በኋላ ወደ አካባቢው እንዳመራ የሚናገረው የዐይን እማኝ፣ ጥቃቱ መንደር 20 በተባለው አካባቢ በስፋት እንደተፈጸመ ገልጿል።

“ሌሊት 12፡00 ገቡ ተባለ። ከዚያም እስከ 4፡00 ድረስ ተኩስ ነበር። ብዙ ጊዜ በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ ስለነበረ የተለመደው መስሎን ነበር። ግን ተኩሱ እስከ አራት ሰዓት ቀጥሎ ጋብ አለ” ይላል።

ከዚያም ወደ ስፍራው ሲደርስ ያየውን ነገር “ከአዕምሮ በላይ ነው” ሲል ገልጾታል።

“በዐይኔ ያየሁት ነገር አሰቃቂ ነው። የሁለትና የሦስት ወር ሕጻናት፣ እናት እና ልጆች በግፍ ተገድለዋል። በጣም ያሰቅቃል” ብሏል።

እርሱ እንደሚለው ብዙ ሰዎች አልቀዋል፤ከቤት ወደ ጫካ ተወስደው በአንድ ላይ ሕጻናትና ሴቶችን ተጨፍጭፈዋል።

ገና የሟቾች አስክሬን እየተሰበሰበ መሆኑን የገለጸው የዐይን እማኙ፣ የተገደሉት ሰዎች ከ150 እስከ 160 እንደሚሆን ግምቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

“መንደሩ ውስጥ የተገደሉት ሽማግሌዎች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። ወጣቶችን ደግሞ አስገድደው ወደ ጫካ ይዘው ሄደዋል ተብሏል። ግን እስካሁን አልተመለሱም” ሲልም በታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱ ሌሎች ሰዎች መኖራቸውንም ተናግሯል።

የዐይን እማኞቹ ጭፍጨፋውን የፈፀመው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው፣ ኦነግ-ሸኔ ነው ብለዋል።

“ልዩ ኃይል የገባው ጥቃቱ ከቆመ በኋላ ነው”

የዐይን እማኞቹ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ በአካባቢው ገብተው ጥቃቱን ሲፈፅሙ በሰፈር ከተቋቋመ ሚሊሻ በስተቀር ሌላ የፀጥታ ኃይል አልነበረም።

“የተወሰኑት ታጣቂዎች ከሚሊሻዎቹ ጋር ሲገጥሙ ገሚሶቹ በየሰፈሩ እየሄዱ ጭፍጨፋውን ፈፀሙ” ይላሉ።

ቢቢሲ ያነጋገረው የዐይን እማኝ ‘ብልጽግናዎች’ ብሎ የጠራቸው የክልሉ ልዩ ኃይሎች መቀመጫቸው መቻራ የሚባል ከተማ እንደሆነ ገልጾ፣ ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ 6፡00 ሰዓት ገደማ ወደ አካባቢው መግባታቸውን ተናግሯል።

ከዚያም መከላከያ ከሰዓት በኋላ 8፡00 አካባቢ መግባቱንም የዐይን እማኙ አክሏል።

በአካባቢው ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ የገለጸው ነዋሪው፤ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ያደርሱባቸው እንደነበርና ደኅንነት ይሰማቸው እንዳልነበርም ለቢቢሲ ገልጿል።

ከጥቃቱ የተረፉ በርካታ ነዋሪዎችም ወደ ሌላ መንደር ሸሽተዋል ብሏል።

ሌላኛው የዐይን እማኝም የአካባቢው አስተዳደር ልዩ ኃይል ይዞ የደረሰው ከ4 ሰዓት በኋላ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚያም ከሰባት ሰዓት በኋላ የተወሰነ የመከላከያ ኃይል መግባቱንና ከ10 ሰዓት በኋላ በርካታ የመከላከያ ሠራዊት ኃይል ወደ ስፍራው መድረሱን፤ ነገር ግን ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው ምንም የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩን አስረድተዋል።

“በጥቃቱ መንደር 20 እና መንደር 15 የሚኖሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች በስለት፣ በቦምብ እና በጥይት በአስቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል” ብለዋል ነዋሪው።

በተለይ ካላፉት አራት ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በታጣቂዎቹ በተፈፀመ ጥቃት ሕጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል።