ከጭፍጨፋ የተረፉ እና የአጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች ሰቆቃና ስጋት

ከሰሞኑ ጭፍጨፋ ከተፈፀመባቸው የምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ አካባቢዎች ከጥቃት የተረፉ ነዋሪዎች አሁንም ስጋት እንዳላቸው ገለጹ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ እና በቄለም ወለጋ፣ ሃዋ ገላን ወረዳ፣ ለምለም ቀበሌ ነዋሪዎች አሁን የፌደራል የፀጥታ አካላት በአካባቢው ቢኖሩም ጥቃት ባልተፈፀመባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ሊፈፀም ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቢቢሲ ለደኅንነታቸው ሲል ስማቸውን የማይጠቅሳቸውና በቄለም ወለጋ፣ ሃዋ ገላን ወረዳ፣ መቻራ በምትባል የገጠር ከተማ የሚኖሩ ግለሰብ በእነርሱ አዋሳኝ ባሉ መንደሮች የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ፣ ከጥቃቱ ለተረፉ መንደሮች ነዋሪዎች ስጋት ነው ብለዋል።
ከ1977 ዓ.ም አንስቶ ነዋሪነታቸው እዚያ እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ፣ በሟቾች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ገልጸው፤ “ዘግናኝ” ያሉትን ጭፍጨፋ የተመለከቱና ከጥቃቱ የተረፉ ሕጻናትም ሆኑ አዋቂዎች በተረበሸ ስሜት ውስጥ እንዳሉ አክለዋል።
“ሕጻናቱም፣ ከብቱም፣ ንብረቱም ብትንትን ብሎ ሜዳ ላይ ነው የቀረው። ለተመለከተው ልብ ይሰብራል” ይላሉ ነዋሪው።
እርሳቸው የሚኖሩበት መቻራ ከተማም “ጥቃት ከተፈፀመባቸው፣ መንደር 20፣ መንደር 15፣ መንደር 16 አካባቢዎች በተፈናቀሉ እናቶች እና ሕጻናት ተጥለቅልቃለች” ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ሰኔ 27/2014 ዓ.ም. እናቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የተጨፈጨፉበትና በለምለም ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው መንደር 20 ከመቻራ በእግር አንድ ሰዓት ቢያስጉዝ ነው።
በጭፍጨፋው መንደር 20 ክፉኛ መጎዳቱን የገለጹት ነዋሪው፣ “ንብረት ተዘርፏል፤ ተቃጥሏል። ከብት ተነድቷል። በሕይወት ያለው ነዋሪ መንከራተት ይዟል” ብለዋል።
ወደ ከተማዋ ጥቃት ሸሽተው የሄዱት ነዋሪዎችም “በዚህ የክረምት ወቅት ያለመጠለያ በየበረንዳው፣ መንገድ ላይ፣ ዘመድ ያለው በየዘመድ ቤት ተጠልለው ይገኛሉ” ሲሉም ስላሉበት ሁኔታ ተናግረዋል።
“አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሁሌም ስጋት ላይ ናቸው” ያሉት ነዋሪው፣ አካባቢውን ለቀው የሚወጡ ሰዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
“እስካሁን ቤት ንብረቱን ላጣውና ወደ መቻራ ከተማ ለተፈናቀለው ሰው፣ በመንግሥት በኩል የሚደረግ ድጋፍ አላየሁም፤ ሰው ሲንከራተት ብቻ ነው የማየው” ብለዋል።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የሃዋ ገላና ነዋሪም በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች መግባታቸውን ገልጸው፣ ነዋሪዎች ግን አሁንም አለመረጋጋታቸውን ገልጸዋል።
“እነዚህ ሰዎች ካለቁ ጀምሮ ሰው መረጋጋት አልቻለም። ጥቃቱ ድጋሜ ይፈፀማል በሚል ስጋት ውስጥ ነው ያለነው” ብለዋል።
“ተረጋግተን እንኖራለን የሚል ተስፋ የለንም”
በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሃዋ ገላና ወረዳ ሰኞ፣ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም በተፈፀመ ጭፍጨፋ ከ150 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል። ከተገደሉት መካከል አብዛኞቹም ሕጻናትና ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥቃቱ በተፈፀመበት ዕለት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ መንግሥት ሸኔ በሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቡድን በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው በቄለም ወለጋ መቻራ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉት “በአገዛዙ ታጣቂዎች ነው” ሲሉ ክሱን አጣጥለዋል።
“ሥፍራውን የተቆጣጠሩት የመከላከያ ሠራዊት እና አጋር ኃይሎች ምንም አላደረጉም” ሲሉ በመውቀስም የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አካላት ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ጭፍጨፋ በተፈፀመበትና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገደሉበት ምዕራብ ወለጋ ቶሌ ቀበሌ ነዋሪው በበኩላቸው የአካባቢው ሰው በሐዘን በመጎዳቱ መረጋጋት ባይችልም የፀጥታ አካላት ግን በሥፍራው እንደሚገኙ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
“መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ነው። ረቡዕ ሰኔ 29/2014 ዓ.ም. ማርፈጃውን ከፍተኛ ተኩስ ነበር” ብለዋል ነዋሪው።
“የተፈፀመው የሚዘገንን ድርጊት ስለሆነና ከአንድ ቤት በርካታ የቤተሰብ አባላት ስለተገደሉ፣ ተረጋግተን እንኖራለን የሚል ተስፋ የለንም” ሲሉም ያላቸውን ስሜት አጋርተዋል።
ምንም እንኳን አሁን የፌደራል ኃይሎች በአካባቢው በመኖራቸው ለጊዜው የጥቃት ስጋት እንደሌላቸው የሚገልጹት ነዋሪው፣ “የፀጥታ ኃይሎቹ መቼ ጥለው እንደሚወጡ ስለማናውቅ አሁንም ስጋት ላይ ነን” ብለዋል።
አሁንም ከታጣቂዎቹ [ሸኔ] “አንምራችሁም!” የሚል ዛቻ እንደሚደርሳቸውም አክለዋል። በስልክ ጭምር እየተደወለ ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው ቢቢሲ ያናገራቸው ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ይናገራሉ።
“መውጣት የሚችለው ነዋሪ ተወልጄበታለሁ ወዳለው አካባቢ [ወደ ከሚሴ ዙሪያ] እየወጣ ነው” ሲሉም ለአስርት ዓመታት ኖረው፣ ወልደው ከብደው ከኖሩበት አካባቢ ለመውጣት መንገድ የጀመሩ መኖራቸውንም አስረድተዋል።
በጊምቢ በተፈፀመው ጭፍጨፋ 338 ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት የገለጸ ቢሆንም የዐይን እማኞች ግን ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሜሪካ የአማራ ማኅበር አሰባሰብኩት ያለውን መረጃ ጠቅሶ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 600 እንደሚጠጋ እና 455 የሚሆኑትን በስም እንደለየ መግለጹ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደምም በምዕራብ ኦሮሚያ የነበሩ ጥቃቶችን ሸሽተው የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች በየስፍራው ተጠልለው ይገኛሉ፤ ከነዚህም መካከከል የደብረ ብርሃን ከተማ ተጠቃሹ ነው።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻድቅ በተለያየ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጥቃቶችን ተከትሎ 70 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል 17 ሺህ የሚሆኑት ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ ብለዋል አስተዳዳሪው።
ከአራቱ የወለጋ ዞኖች ውጭ ካሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች የተወሰነ መረጋጋት ባለባቸው አካባቢዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም አስተዳዳሪው አክለዋል።
ከሰሞኑ የተፈፀሙትን እነዚህ ጥቃቶች ተከትሎ ከምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን የገቡ ተጨማሪ ሰዎች መኖራቸውንም የከተማዋ ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ማን ምን አለ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም መንግሥት ሸኔ በሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሲል በሚጠራው ቡድን በዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ገልጸዋል።
በጥቃቱም ማዘናቸውን ገልጸው፤ “ይህንን አሸባሪ ቡድን እስከ መጨረሻው ተከታትለን ከሕዝባችን ጋር እናስወግደዋለን” ብለዋል።
የቄለም ወለጋው ጥቃት ከመፈፀሙ ከአምስት ቀናት በፊት፣ በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ገልጸው ነበር።ይህም በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ በተፈፀሙት ጥቃቶች ላይ መረጃዎችን እያሰባሰበ እንደሆነ ገልጾ፣ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት በአስቸኳይ እንድንቆም እና ተጨማሪ የሰላማዊ ሰዎችን ሞት ለመከላከል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን በአስቸኳይ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ፣ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት መግታት የሚያስችል እርምጃዎችን ለመውሰድ ዳተኛ እና ለጥቃቱ ተባባሪ ሆነዋል ብለዋል።
ኢዜማ በበኩሉ ማንነትን መሠረት አድርገው የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማስቆም መንግሥት ግዴታውን እንዲወጣ በተደጋጋሚ ባሳስብም፣ ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ማሳሰቢያዎቹን ለመቀበል ምንም ዓይነት ፍላጎት አላሳየም ብሏል።
አብን ትናንት፣ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ በኦሮሚያ ክልል ሥር ያሉ የምዕራብ፣ ምሥራቅ፣ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች “ ላልተወሰነ ጊዜ” ከፌደራሉ መንግሥት በሚመደቡ የሲቪል እና የፀጥታ አስተዳደር አካላት እንዲተዳደሩ ጠይቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ዝግ ስብሰባ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች የተፈፀሙ ግድያዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የተፈፀሙ ኢ- ሰብዓዊ ጭፍጨፋዎችን የሚያጣራ ልዩ ኮሚቴ እንዲቋቋም ወስኗል።
ይሁን እንጂ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ ቢነሳም ምክር ቤቱ ሳይቀበለው መቅረቱ በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ቅሬታን ፈጥሯል።
ከአንድ ወር በፊት [ግንቦት 22/ 2014 ዓ.ም ] የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ፣ መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለውና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል የተቆጣጠራቸው ወረዳ፣ ቀበሌ አሊያም ምንም መንደር አለመኖሩን መናገራቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቦ ነበር።
ከዚህ ቀደም ብሎ በኦሮሚያ በምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ እና ምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ተከትሎ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ አብዛኛው የምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በፌደራል ኮማንድ ፖስት ሥር መሆናቸው የሚነገር ቢሆንም፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ግን አሁንም አላባሩም።
በተለያየ ጊዜ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ከጥቃት የተረፉ ነዋሪዎች እና የዐይን ምስክሮች ከፀጥታ አካላት አፋጣኝ ምላሽ አለመኖሩ የሚደርሰውን ጉዳት እንዳከፋው ተናግረዋል።
















