ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ66ቱ አብዮት፡ በዘውዳዊው ሥርዓት ሙስሊም የመኾን አንዳንድ ፈተናዎች እና ገጠመኞች
በ1966 - የዛሬ 50 ዓመት ገደማ- ሥር ነቀል ለውጥን በመሻት በኢትዮጵያ አብዮት ተነሳ።
ለአብዮት ፍንዳታ የሚያበቁ በርካታ ጭቆናዎች ሞልተው ይፈሱ ነበር።
ከገጠር ከከተማ፣ ከጭሰኛው እስከ ታክሲ ሾፌር፣ ከወዛደር እስከ ወታደር ለውጥን ያልሻተ ማን ነበር?
ሃይማኖታዊ ጭቆና እና መገለል ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ መልክና ገጽታ እንደነበረው ታሪክ ፀሐፊዎች ያወሳሉ፤ ድርብ ድርብርብነቱን ያነሳሉ።
ለመሆኑ በዘውዱ ሥርዓት ውስጥ ሙስሊም ኾኖ መኖር እንዴት ያለ ነበር? የነበሩት - የኖሩትን ሕይወት ቢነግሩንስ?
ከአቶ አሕመድ ሑሴን እንጀምር። በዘመኑ በሙስሊሞች እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው። ከአገር ከወጡ በኋላም በተማሪዎች ትግል ተሳታፊ ነበሩ።
ላለፉት አስርታት በአሜሪካ ነዋሪ ናቸው።
“አሕመድ ብሎ ስም፣ ለአየር ኃይል አይሆንም”
“ከምን ልጀምርልህ? ከእኔ ከራሴ ገጠመኝ ልጀምርልህ?
መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት 2ኛ ደረጃ እያለን ተሰማ እና ከበደ የሚባሉ ጓደኞች ነበሩኝ። ሦስታችንም ስፖርተኞች ነበርን። ጡንቻችን ፈርጣማ ነበር።
አንድ ቀን ‘ጥሩ አቋም ያለው ወጣት አየር ኃይል ይፈለጋል’ ሲባል ‘እንሂድ! እንሂድ!’ ተባባልን።
ልንመዘገብ ደብረ ዘይት ሄድን። በተለይ እኔ ከልጅነት ጀምሮ አውሮፕላን አብራሪ መሆን ነበር ምኞቴ። በእውነቱ እንደ አውሮፕላን የሚደንቀኝ ነገር አልነበረም።
አስታውሳለሁ ሦስታችንም በጉጉት ነው አየር ኃይል የሄድነው።
ተሰማና ከበደ አንተ ቅደም አሉኝ። ቀደምኩ።
የተቀበለኝ አንድ አስር አለቃ ይሁን መቶ አለቃ ማዕረጉን አሁን ረሳሁት፣ ብቻ ሲያየኝ በጣም ደስ አለው። እንዳልኩት ሰውነቴ በስፖርት የዳበረ ነበር፣ እንዳሁኑ ሳይሆን።
“ጎረምሳው ስምህ ማነው?” አለኝ።
“አሕመድ ሑሴን እባላለሁ - በቅጽል ስሜ አሕመድ ሪንጎ” አልኩት።
ድንገት ፊቱ ቅጭም አለ። ለአፍታ አተኩሮ ካየኝ በኋላ “ምን መሰለህ፣ ልምከርህ? ያንተ ስም አየር ኃይል ውስጥ ትንሽ ያስቸግራል” አለኝ።
“ለምን?” አልኩት።
ያን ዘመን የጀብሃ እንቅስቃሴ ነበር። እነ ኡስማን ሳሊህ ሳቢ እና ብዙዎቹ የጀብሃ አመራሮች ደግሞ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ሙስሊሞች ነበሩ።
የእኔ ስም በፍጹም ሊታመን እንደማይችል አስረዳኝ። ቀጠለና እንዲህ አለኝ፦
“... ከዚህ ሁሉ ስምህን ለምን አንቀይረውም? የሚሻለው እንደዚያ ነው፤ ላንተው ብዬ ነው። ወጣት ነህ፤ ወደፊት ጃንሆይም ጋ ስትቀርብ፣ ለማዕረግም ለምኑም ለምኑም ስምህ እንዲመች አድርገን እንቀይረው፤ አይሻልም?” አለኝ።
ያኔ ጉርምስናውም አለ፣ ድንገት ብልጭ አለብኝ።
“ስማ! ለምን እዚሁ ድንጋይ ሆኜ አልቀርም - ስሜን አልቀይርም” ብዬው ጥዬለት ወጣሁ።
እውነት ለመናገር ችግር ሊያደርስብኝ ይችል ነበር። ዕድለኛ ነኝ ምንም አላለኝም። እንዲያውም ተከትሎኝ ወጣ።
ጓደኞቼ ተሰማ እና ከበደ ውጭ እየጠበቁ ነበር።
“ሪንጎ ምንድነው?” አሉኝ።
“ስምህን ቀይር አለኝ” አልኳቸው። እነሱም ተናደዱ። ወታደሩ ትንሽ መንገድ እየተከተለ፣ “ኑ እናንተ ተመዝገቡ” አላቸው።
“ሪንጎ ካልተመዘገበ እኛም አንመዘገብም” አሉት። እኔን ትተው እነሱ እንዲመዘገቡ ብወተውታቸውም እምቢ አሉ።
አሁን ተሰማ እና ከበደ በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም። ውድ ክርስቲያን ጓደኞቼ ነበሩ። መቼም አልረሳቸውም።
“ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መስሊሞች”
“ድሮ ወላጆቻችን ሙስሊም በመሆናቸው የደረሰባቸውን ሲነግሩን ለማመን ይከብደን ነበር። አሁን ላይ ሳስበው በንጉሡ ጊዜ መሻሻል ነበር እላለሁ፤ ከወላጆቻችን አንጻር ሲታይ ማለቴ ነው። ሆኖም ግን በቂ አልነበረም።
ለምሳሌ ኢትዮጵያዊነታችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስንጠራም “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መስሊሞች” እያሉ ነበር የሚጠሩን። እንደ ኮሚኒቲ ነበር የሚያዩን።
ኢትዮጵያዊነታችን 2ኛ ደረጃ ነበር የሚሰጠው። የኖርኩት ስለሆነ ይሄን የሚያሳዩ መአት አጋጣሚዎችን ልዘረዝርልህ እችላለሁ።
የሙስሊም ስም የመያዝ ጣጣን ካነሳሁ አይቀር አንድ ልጨምርልህ።
ጃቢር የሚባል ታላቅ ወንድሜ የምለው ልጅ ነበር። ትምህርት ቤት ለምዝገባ ይሄዳል።
መጀመሪያ ምኒልክ ነበር የሚማረው። ትንሽ ስለራቀው ነው መሰለኝ ትምህርት ቤት መቀየር ፈለገ። ወደ ቀኃሥ (አሁን ኮከበ ጽባህ ነው የሚባለው) ይሄዳል።
እዚያ ሲሄድ ስምህን ካልቀየርክ አሉት። ቢለምን ምን ቢል በፍጹም ተባለ። በመጨረሻ ስሙ ገብረማርያም ተብሎ ተመዘገበ። አማራጭ አልነበረውም። ሁንም በሕይወት አለ። እዚህ አሜሪካ ነው የሚኖረው።
እንዲህ ዓይነት ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። ነገር ግን ሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ነበር ማለት አይደለም።
በንጉሡ ጊዜ ሙስሊም ሆነው ትልቅ ሥልጣን የነበራቸው፣ በትልቅ ኃላፊነት ላይም የነበሩ አልነበሩም ማለትም አይደለም። ጥቂት ቢሆኑም ማለቴ ነው።
ነገር ግን ብዙ ቦታ ሙስሊም ስም ከያዝክ እንቅፋት ይጋጥምህ ነበር።”
የስም ጉዳይ ሲነሳ በዚያ ዘመን ወጣት የነበሩትና በኋላ በአየር መንገድ በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት ዶ/ር አሕመድ ቀሎ ‘በድር’ ለተባለ መጽሔት በጊዜው የገጠማቸውን እንዲህ አካፍለዋል።
“...12ኛ ክፍል ሆኜ ኮሜርሻል ባንክ ክፍት የሥራ ቦታ አለ ሲባል እኔ እና ጓደኞቼ ለመቀጠር ፈልገን ገብተን ስንጠይቅ በቃ ሳቁብን። [ግራ ገባን]
“ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ፣ ‘እንዲህ ዓይነት ስም ይዛችሁ ነው ደግሞ የምትቀጠሩት?' አሉን። አዲስ አበባ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ብዙ ላይገጥም ይችል ይሆናል። ክፍለ አገር ግን የተመለደ ነበር።”
የግብረ-ገብ ትምህርት
አቶ አሕመድ ሐሰን እና ሌሎች ያነጋገርናቸው በተለይ በንጉሡ ጊዜ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የነበሩ ሙስሊሞች የግብረ ገብ ትምህርት ላይ መጠነኛ ቅሬታ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።
የአቶ አሕመድ ትዝታ የሌሎችንም የሚወክል ነው።
“7ኛ እና 8ኛ ክፍል አርበኞች የሚባል ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። ክርስቲያን ወንድሞቼም የሚያስታውሱት ትምህርት ቤት ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ጸሎት የምናደርገው ከሃይማኖታችን ጋ በማይጣጣም መልኩ ነው።
አንዳንዴ እሱን ለማለፍ አርፍደን ለመግባት እንሞክራለን፤ ዘበኛ ደግሞ አያስገባንም። ለነገሩ ሙስሊም ተማሪዎች በጣም ትንሽ ነበርን። የትም ትምህርት ቤት ሙስሊም ተማሪ ብዙ አልነበረም።
ብቻ ክፍል ከገባን በኋላ ደግሞ ሌላ ፈተና አለ። ምን በለኝ!
ከቤተ ክህንት የሚመጡ ቄስ ግብረ ገብ ያስተምሩናል። ይሄ ከላይ ከላዩ ሲታይ “ምን ችግር አለው አንድ ቄስ ግብረ ገብ ቢያስተምሩ?” ልትለኝ ትችላለህ። እውነት ነው - በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ችግር አልነበረመውም።
ነገር ግን ነገሩን ሙስሊም ሆነህ ስታየው ምቾት አይሰጥም። ወይም ደግሞ ነገሩን ገልብጠህ ካላየኸው ላትረዳው ትችላለህ።
ቁርአን እየጠቀሰ አንድ ሼክ ክፍል ገብቶ ግብ ረገብ ቢያስተምር ክርስቲያን ወንድሞች ምቾት እንደማይሰማቸው ዓይነት ነው ነገሩ።
ይህ ብቻም ሳይሆን በወቅቱ እኛን የማይመለከቱ፣ ከዕምነታችን ጋ የሚቃረኑ፣ የማንቀበላቸው ይዘቶችን በግድ እንድንማር ይደረግ ነበር።
ፍዝ የሙስሊም በዓላት ትዝታ
ልጅ እያለሁ የሙስሊም በዓል በመጣ ቁጥር ይሰማኝ የነበረውን ልንገርህ?
የተክለሃይማኖት ሰፈር ልጅ ነኝ። እና ልጅ እያለን ልብስ የሚገዛልን ለኢድ እና ለአረፋ ብቻ ነው። እና ልዩ ደስታ ነበር የሚሰማን። ከዚያ ግን ዕለቱ በዓል በዓል አይመስልም። እንደ ክርስቲያን በዓል አይደምቅም።
ግራ ሲገባኝ ሐደሬ ሰፈር ጓደኞቼ ጋ እሄዳለሁ። ዝንጥ ብለናል። ግን በበዓሉ ቀን ምንም አዲስ ነገር የለም። ሱቅ ሁሉ ክፍት ነው። ከሌላው ቀን በምንም አይለይም።
በቃ ሲኒማ ኢትዮጵያ እንግባ ብለን ወደ ፒያሳ ሄድን። ዓመት በዓሉን የሆነ ፊልም እያየን አሳለፍን። ምንም ነገር ስለሌለ ነው እኮ ፊልም ገብተን በዓል ለማክበር የምንሞክረው።
በልጅነቴ በቃ ይህ ነገር ስሜቴን ይጎዳው ነበር።
የክርስቲያን ጓደኞቼ በዓል ሲመጣ ግን ደማቅ ነው። የእኛ አውዳመት ፍዝ ነው። ለምን የእኛ በድምቀት አይከበርም እያልኩ እጠይቅ ነበር።
ከብዙ ዓመት በኋላ እኔም አድጌ የ66ቱ አብዮት ላይ ከጠየቅናቸው ጥያቄዎች አንዱም ይህ ነበር። ኢድ ብሔራዊ በዓል እንዲሆን።
ሌላ ከበዓል ጋ ተያይዞ ትዝ የሚለኝን ነገር ልንገርህ?
ሌሊት መድፍ ይተኮስልን ነበር። ጃንሜዳ ደግሞ ኢድ እንዲሰገድ ተፈቅዶ ነበር። ይሄ ትልቅ ለውጥ ነው በእርግጥ። ታሪክ ማዛባት የለብንም። በዘመኑ ብዙ ለውጦች እንደነበሩ መካድ አይቻልም።
ነገር ግን ማታ ላይ ዜና ሲታይ የአብሬት ሼኮች ወይም ያኔ ኢማም የነበሩት ሐጂ መሐመድ ሳኒ ሐቢብ ንጉሡን እጅ ሲነሱ እየታየ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ እስላሞች ዛሬ በዓላቸው አከበሩ” ተብሎ ነበር ዜና የሚሠራው።
የ66ቱ ሰልፍ ላይ አንድ የጠየቅነው ጥያቄም ይሄ ስሜት የሚጎዳ አገላለጽ እንዲቀር ነበር።
ከበዓል ጋ ተያይዞ ሌላ ትዝ የሚለኝ ምን መሰለህ?
ረመዳን ላይ እንደዚህ በቃ አገር ውስጥ ምንም ነገር በሬዲዮ ስለሌለ የኡምዱርማን ጣቢያ በአጭር ሞገድ እየፈለግን ኢስላማዊ ነገር እንሰማ ነበር።
የኢድ ዋዜማ ላይ የሆነች የምትዘጋጅ ፕሮግራም ነበረች።
በጊዜው አንድ አምስት ሙስሊም ትምህርት ቤቶች ነበሩ። በኒ መስጊድ አካባቢ ሰለፊያ ትምህርት ቤት። አሜሪካን ግቢ ደግሞ ጃሊያ የሚባል፣ አደሬ ሰፈር አባድር የሚባል ኢስላማዊ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ትንንሽ ናቸው።
ከዚህ ትምህርት ቤት የተውጣጡ ተማሪዎች የቁርአን እና የነሺዳ ውድድር እናደርግ ነበር። ካልተሳሳትኩ አባቢያ አባጆቢር ነበር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚያስተባብረው።
ከ1950ዎቹ ጀምሮ ጥቂት ዩነቪርስቲ መግባት የቻሉ ሙስሊሞች “ኢድ ፓርቲ” የሚባል የበዓል ዝግጅት ነበራቸው። በኋላ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን ማሳተፍ ጀመሩ።
እና ለኢድ ዋዜማ በዓሉን የምናከብርበት አዳራሽ ማግኘት ለሙስሊሞች ከባድ ነበር።
አምባሳደር፣ መዘጋጃ ቤት፣ ራስ ኃይሉ አንዳቸውም አይፈቅዱልንም። በገዛ ገንዘባችን ለመከራየት እኮ ነው የማይፈቅዱልን። ማታ-ማታ ብቻ ይፈቀድልናል።
በዚያ ምሽት ትዝ እንደሚለኝ ለሕዝቡ መዝሙር እናቀርብና ሽልማት ይሰጣል በቃ። ዋዜማ ላይ ይቺ ዝግጅት ነበር የነበረችው። ለእኛ ግን ትልቅ ነገር ነበር። ትዝታው ከ50 ዓመት በኋላም ዛሬም አብሮኝ አለ።”
የሙስሊም ኮፍያ
አንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ በወቅቱ ሕዝብ እንዴት ያስብ እንደነበር ሊያስረዱ ስለሚችሉ ልንገርህ።
አንድ አጎት ነበሩኝ። ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ ነበር የሚኖሩት። ቮልስ ዋገን ነበረቻቸው። ያኔ መኪና ብርቅ ነበር።
እና የሙስሊም ኮፍያ (ቆብ) ያደርጉ ስለነበር በተደጋጋሚ ትራፊክ ያስቆማቸው ነበር። በጣም ሲቸገሩ ኮፍያውን አውልቀው መንዳት ጀመሩ።
ይሄ ማለት በዚያ ዘመን የሙስሊም ኮፍያ ማድረግ በሕግ ተከልክሎ ነበር እያልኩ አይደለም። ሙስሊም በመሆን ያጋጥሙ ከነበሩ ነገሮች መካከል የማስታውሰውን ገጠመኝ ለማንሳት ነው።
ከስምህ ጀምሮ ትንንሽ የሚመስሉ ነገሮች እንቅፋት የመሆን ዕድል ነበራቸው። በተለይ ደግሞ በወቅቱ በኤርትራ ከነበሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም ጋ ተያይዞ ሙስሊሙ በዜግነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖር ይደረግ ነበር።
‘አንተ እስላም!’ ብሎ ስድብ
በዚያ ዘመን ሙስሊም የመሆን ፈተናዎችን መጠቃቀስ እንዴት ተኑሮ እዚህ እንደተደረሰ ማሳያ ስለሚሆን መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።
ለምሳሌ ‘እስላም’ ብሎ ስድብ ነበር። ወይም ደግሞ እንደ ስድብ ይቆጠር ነበር።
“እስላም አገሩ መካ” እያሉ አገራችን ሳዑዲ እንጂ ኢትዮጵያ እንዳልሆነች በሾርኔ ጠቆም ያደርጉን ነበር። የዕውቀት ማነስ ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል።
እኔ ከአብዮቱ በኋላ ወደ ሆላንድ ነው የወጣሁት። የኢህአፓ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበርኩ።
የተማሪው ማኅበር ላይ ሆላንድ አንድ ስብሰባ ተሰብስበን ሐሳብ ከሰጠሁ በኋላ አንድ አዲስ አበባ የማውቀው ልጅ እምር ብሎ ተነሳና፣ “ቁጭ በል አንተ እስላም” ብሎ ዘለፈኝ።
ወላሂ ከስድቡ ይልቅ አሁንም ድረስ የሚታወሰኝ ምኑ መሰለህ፤ ጓደኞቼ በፖለቲካ የነቁ ስለነበሩ ልጁን የወቀሱበት መንገድ።
እንዲያውም ከማዕከላዊ ኮሚቴ “ልጁን አስወጡት” ብለው ወሰኑ። ለ15 ቀን ገለጻ (የፖለቲካ ኦረንቴሽን) እንዲሰጠው ተደረገ።
ከእምነት ጋር ተያይዞ ተራ ዘለፋዎች ይሰነዘሩ ነበር። ይሄ እኔም ላይ ደርሷል። ነገር ግን ብዙዎቹ ክርስቲያን ጓደኞቼን የሚወክል አልነበረም። እንዲያውም በሚገርም ሁኔታ እነሱ ይጋፈጡልኝ ነበር።
ፓስፖርት የማግኘት ፍዳ
በወቅቱ በነበሩ የሃይማኖት መብት እና የእኩልነት ትግሎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው እና በንጉሡ ጊዜ ወጣት ሙስሊሞችን በማሰባሰብ ታሪካዊ ንቅናቄ መፍጠር ችለው የነበሩት አቶ መሐመድ ሐሰን ደግሞ ይህን ያስታውሳሉ።
“…ብዙ ሰው አሁን ላይ ይህን ሲሰማ ሊደነቅ ይችላል። ድሮ በንጉሡ ጊዜ ለአንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ፓስፖርት ማግኘት ቀላል አልነበረም። እርግጥ ነው በሕግ ለሙስሊሞች ፓስፖርት አይሰጥ የሚል ነገር አልነበረም። በተግባር የነበረው ነገር ግን ከክልከላ የሚተናነስ አልነበረም።
ይሄ በተጨባጭ የነበረ ነገር ነው። አሁን በሕይወት ያሉ ምስክሮች አሉ። አባቶችም በጊዜው ያዩትን ፍዳ ብዙ ጊዜ ያጫውቱናል።
አንዱን ብቻ ብነግርህ ማሳያ ይሆናል። በቅርቡ ወደ አኼራ የሄዱት (ሕይወታቸወ ያለፈው) ታዋቂው ሐጂ በሺር ዳውድ በዘመኑ ፓስፖርት ከተከለከሉት አንዱ ናቸው።
ብዙ ደረሳዎች ፓስፖርት ስለማይሰጣቸው ወደ አል አዝሃር ዩኒቨርስቲ በሱዳን በኩል በእግር አቆራርጠው ወደ ግብፅ የሚሄዱ ነበሩ።
ሊሴ ፓሴ ተከልክለው ሱዳን ሲያዙ ደግሞ ትምህርት ፈላጊ እንደሆኑ አስመስክረው እዚያ ደግሞ በልመና ሃይማኖታዊ ትምህርት ጨርሰው ይመጡ ነበር።
አንድ አባት የነገሩኝን ላጫውትህ።
የሆነ ጊዜ በፓስፖርት የተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ነገሩ አንገሽግሿቸው ካይሮ የኢትዮጵያ ቆንስላ ሰልፍ ወጡ። ዶክመንት ይሰጠን ብለው ጠየቁ፤ ዜጋ መሆናችን ይታወቅልን አሉ።
በወቅቱ ካይሮ የነበሩት አምባሳደር አቤቱታቸውን ከተቀበሉ በኋላ “ሁለተኛ እዚህ ድርሽ እንዳትሉ” ብለው ፖሊስ ጠሩባቸው።
የሚደንቀው ደግሞ ፖሊስ መጥቶ ሰልፈኞቹ ከቦታው በሰላም እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ አምባሳደሩ ቄስ ጠርተው ግቢውን ጸበል አስረጩት።
ይህን የነገሩን አባቶች በጊዜው ከፍተኛ ቅሬታ ተፈጥሮባቸው ነበር። ኢትዮጵያዊ ስሜታቸው ተጎድቶ ነበር።
የዚያ አምባሳደር ድርጊት ግለሰቡን ነው የሚወክለው ወይስ አገርን የሚለው ሊያነጋግር ይችላል። ሆኖም ግን ይሄን ይሄን ዓይነቱን የበደል ታሪክ ከሃይማኖት አባቶቻችን ስንሰማ ነው የኖርነው።
ውስጣችን ቅራኔ ዘርቶ ነበር።
ይህ ደግሞ በ66 ለተደረገው የሙስሊም ትዕይንተ ሕዝብ ገፊ ምክንያት ሆኗል ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ ባሻገር በንጉሡ ጊዜ ቢሮክራሲው ላይ ሙስሊም መሆንህ ሲታወቅ ሥራ ለመቀጠር ትቸገራለህ። በግልጽ ክልከላ ላይኖር ይችላል ነገር ግን መቀጠር ፈተና ነበር።
ብዙዎቹ ተምረው ከመጡ በኋላ ዘለግ ላለ ጊዜ ያለ ሥራ ይቀመጣሉ።
በአጭሩ ሙስሊም፣ አንዳንዴ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ-ብዙውን ጊዜ ደግሞ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ በአገሪቱ ላይ የዜግነት ተሳትፎ እንዳያደርግ ይደረግ ነበር።
ይህ በገዛ አገር መገፋት ቁጭት ተደማምሮ ነው በ66ቱ አብዮት ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ የነበረው” ይላሉ።
አቶ መሐመድ ሐሰን በ50 ዓመታት በሃይማኖት ነጻነት እና እኩልነት ብዙ ርቀት መኬዱን ባይክዱም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ያምናሉ።
“...አንድ ሕዝብ በብሔርም ይሁን በሃይማኖቱ ምክንያት ሲገለል ዞሮ ዞሮ የምትጎዳው አገር ናት። ሙስሊሙ ከትምህርት ዕድሎች ለዘመናት ገሸሽ በመደረጉ እኮ ኢትዮጵያ አላተረፈችም። የምንጎዳው አብረን ነው። የምትጎዳው አገር ናት። የዓለም ታሪክ የሚነግረን ይህን ሐቅ ነው።
ብቻ ለአብዮቱም ሆነ በጊዜው ለተደረገው ታላቅ የሙስሊም ሰልፍ ከበቂ በላይ ምክንያቶች ነበሩ ልልህ ፈልጌ ነው።”