የ1966ቱን የሙስሊሞች ሰልፍ በኅቡዕ ያስተባበሩት እነማን ናቸው?

ግማሽ ክፍለ ዘመን የዋዛ አይደለም።

ንጉሡ ራሱ በመንበሩ የፀኑት ከዚያ ላነሰ ጊዜ ነው።

ግማሽ ክፍለ ዘመን የዋዛ አይደለም።

ከ'አንተ' ወደ 'አንቱ' የሚያሸጋግር የጊዜ ኬላ ነው።

ግማሽ ክፍለ ዘመን ቀላል አይደለም።

“ያ ወለድ!” ከመባል “ያ ሼኽ!” ወደመባል የሚወስድ ማቱሳላዊ የዕድሜ አውራ ጎዳና ነው።

የዛሬ 50 ዓመት ምን ሆነ?

ይህን ሊመልሱ የሚችሉ ሁነኛ ሰዎችን በቀላሉ ማግኘት ቀላል ያልሆነውም ለዚያ ነው። ብዙዎች ወደ 'አኼራ' ነጉደዋል።

በሕይወት ያሉትም ትዝታቸው ሳስቷል። አንዳንዶቹ ወደ ሚዲያ ለመውጣት አልፈቀዱም። አንዳንዶቹ ደግሞ መልካቸው ብቻ ሳይሆን ዘመን ዜግነታቸውን ቀይሮታል።

ያኔ አብዮቱ ሲፈነዳ ኢትዮጵያዊ ነበሩ - አሁን ኤርትራዊ ሆነዋል።

ሦስት-አራቱ ብቻ ትዝታቸውን ሊያወጉን ፈቅደዋል።

በዘመኑ ‘ምድር አንቀጥቅጥ’ የተባለውን የ66ቱን የሙስሊሞች ሰልፍ በኅቡዕ ካደራጁት መካከል አንዱ አቶ መሐመድ ሐሰን የዛሬ 50 ዓመት ጎረምሳ ነበሩ።

አሁን ትልቅ ሰው ሆነው በጀርመን ጉተንበርግ የሃይማኖቶች አማካሪ ምክር ቤት አባልም አባትም ናቸው።

በተለይ እሳቸው ድሮ እንደ ዋዛ የመሠረቱት “ኢስላማዊ ክበብ” በኋላ ላይ ለሰልፉ ፊታውራሪዎች ሁነኛ መድረክ ሆኗቸዋል።

የአቶ መሐመድ ሐሰን አባት በንጉሡ ጊዜ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት (ፓርላማ) አባል ነበሩ።

ይህ ጥቂቶች ብቻ ያገኙት የነበረ ልዩ ዕድል ነው።

የአባታቸው ለዘውዱ የነበረቸው ቅርበት ጠቅሟቸው ብዙ እንዲያነቡ እንዲሁም የመንግሥት ሥርዓት እና አሠራርን በቅርብ እንዲመረምሩ አስችሏቸዋል።

እሳቸው አብዮቱ በፈነዳ ሰሞን ለትምህርት ወደ ምዕራብ ጀርመን አቀኑ።

አውሮፕላን ከመሳፈራቸው በፊት በአዲስ አበባ የሆነውን፣ ያዩትን፣ የተሳተፉበትን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

የግማሽ ክፍለ ዘመን የትዝታ ከፍ እና ዝቅ ሲተረክ ይህን ይመስላል።

“ድሮ ሃይማኖት የግል፤ አገር የጋራ አልነበረም”

“ምን መሰለህ? አንድን አብዮት ለመረዳት የጊዜውን አውድ መረዳት አለብህ። አለበለዚያ ስህተት ላይ ትወድቃለህ።

ድሮ 'ሃይማኖት የግል፣ አገር የጋራ' ይባል ነበር። አገር ግን የጋራ አልነበረችም። ለምሳሌ የኛ አባቶች ለቤተ ክህነት ግብር ለመገበር ይገደዱ ነበር።

የሚገብሩት እንዴት ነው ያልክ እንደሁ፣ 'ሲሦ ለነጋሽ፣ ሲሦ ለአንጋሽ፣ ሲሦ ለቀዳሽ' በሚል ስሌት ነው። የመሬት ስሪት ከቦታ ቦታ ቢለያይም ብዙ አካባቢ አሠራሩ ይኸው ነበር።

ሌላ ምሳሌ ብነግርህ በንጉሡ ካቢኔ ውስጥ ፓትሪያርኩ ነበሩበት። ይሰበሰባሉ።

ለምሳሌ በንጉሡ ጊዜ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር የሚባል ነበረ። በሸፍጥ ተሰፍሮ ከተሰጠው ተግባር አንዱ፣ አንድን ሃየማኖት የማስፋፋት ተልዕኮን ማገዝ ይገኝበታል።

በአጭሩ በዚያ ዘመን መንግሥታዊ ሃይማኖት ነበር እያልኩህ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል አልነበሩም እያልኩ ነው።

ወደ ኋላ ትንሽ ሸርተት ብለን ታሪክ ከፈተሽን ደግሞ ሌላ ተቃርኖ እንመዛለን።

ለምሳሌ አብረሃማዊ ሃይማኖቶች አይሁድም፣ ክርስትናም እስልምናም ከውጭ የገቡ ሃይማኖቶች እንደሆኑ ይታወቃል። ሦስቱም ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው የመጡት።

ሐቁ ይሄ ሆኖ ሳለ ክርስትና አገር በቀል ተደርጎ እንዲወሰድ፣ እስልምና ደግሞ መጤ ሆኖ እንዲታይ ብዙ ተሠርቶ ነበር።

ሙስሊሞች በቃ ምን ልበልህ፣ ከሆነ አገር መጥተን ጥገኝነት ተሰጥቶን የምንኖር ‘ኮሚኒቲ’ እንጂ ሙሉ ዜጋ አድርጎ ያለማየት ችግር ተንሰራፍቶ ነበር።

እንግዲህ ልብ አድርግ፤ ክርስትና እና እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከሦስት መቶ ዓመት ያነሰ ልዩነት ቢኖራቸው ነው። በ4ኛው ክፍለ ዘመን ክርስትና ገባ፤ በ7ኛው ክፍለ ዘመን እስልምና ገባ።

ሙስሊሞች ግን በቀደም የመጡ እንግዶች ሆነው ነበር የሚሳሉት።

በዚያ ዘመን የኖርን ሙስሊሞች የቦሩ ሜዳን ዓይነት የጭቆና እና የግፍ ታሪኮች ከአባቶቻችን ስንሰማ ነው የኖርነው። ውስጥ ውስጡን የሙስሊም ለዘመናት በገዛ አገሩ መገፋት ቅሬታ ፈጥሮብናል።

ሌላም ልጨምርልህ።

ከመካ ቀጥሎ ሙስሊሞች ያለ ተጽእኖ በይፋ በሃይማኖታቸው የኖሩት በየትም ሳይሆን በኢትዮጵያ ነው። እነሱ [አረቦች] ከዚያ መጥተው የተሰጣቸውን መብት አባቶቻችን በገዛ አገራችው አልተሰጣቸውም። መብታቸውን በአገራቸው ተነፍገው ነው የኖሩት።

ለመቶ ዓመታት ሙስሊሞች የዜግነት እና የአገር ባለቤትነት ስሜት እንዳይኖራቸው ተደርጓል።

ከ896 ወዲህ በአዳል፣ በቤኒሻንጉል፣ በሐዲያ፣ በደራ፣ በባሌ፣ በይፋት፣ በደዋሮ፣ በአፋር፣ በሐረር ሙስሊሞች የራሳቸው ሱልጣኔት አቋቁመው አስተዳድረዋል። ይሄ በታሪክ ብዙ አይነገርም።

በአጠቃላይ ነገሮች ለሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ጥሩ አልነበሩም። ታሪክ መፈተሽ ከጀመርን ይረዝምብናል እንጂ ብዙ ማንሳት ይቻላል። በአጭሩ ድሮ በንጉሡ ጊዜ እና ከዚያም ቀደም ብሎ ሃይማኖት የግል፣ አገር የጋራ አልነበረችም ልልህ ፈልጌ ነው።

በኔ አስተያየት፣ ይሄ የዘመናት ቅራኔ ነው ሕዝበ ሙስሊሙ ለ66ቱ ታላቅ ትዕይንተ ሕዝብ ያበቃው። እንጂ ብዙ ሰው እንደሚገምተው በአንድ ጀንበር የመጣ ግብታዊ ሰልፍ አይደለም።”

የሙስሊሞችን ሰልፍ እነማን አስተባበሩት?

ከ66ቱ አብዮት በፊት ሙስሊሞች ተቋም አልነበራቸውም። ሰልፍ ለማስተናበር ይቅርና የሚወክላቸው አንድም ተቋም አልነበረም።

ይሁንና ሙከራዎች አልነበሩም ማለት አይደለም።

ለምሳሌ “ሰላማዊ ማኅበር” ይጠቀሳል።

ይህ ማኅበር ምናልባት በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ኢስላማዊ አደረጃጀት ይሆን?

ኢስላማዊ ማኅበር ለመመሥረት ቀደም ብሎ አንድ ሁለት የከፈሸ ሙከራ እንደነበር አሁን ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት አቶ አሕመድ ሑሴን (ሪንጎ) ያስታውሳሉ።

“ከአባቶቼ እንደሰማሁት ድሮ ሙስሊም ሆኖ ከሻለቃ በላይ ማዕረግ ማግኘት ፈተና ነበር። ሻለቃነት የደረሱ ሙስሊሞች አልነበሩም ማለት ግን አይደለም። ከዚያም በላይ ይኖራሉ። ቀላል አልነበረም ነው ያልኩህ።

መጀመሪያ ሙስሊሙን የማደረጃት ሙከራ የተጀመረው ከእነዚህ ሻለቃዎች አንዱ በነበሩት ሻለቃ ሱልጣን ይመስለኛል፤ የቃጥባሬ ሼክ ልጅ።

እሳቸው በንጉሡ ጊዜ የፈረስ አሠልጣኝ ነበሩ። ከበርካታ ወዳጆቻቸው ጋር ሆነው ‘ሰላማዊ ማኅበር’ የሚባል ኢስላማዊ ማኅበር አባኮራን ሰፈር አካባቢ አቋቋሙ።

የመንግሥት ደኅንነቶች ደርሰውበት ፈረሰ። ሻለቃ ሱልጣንን ደግሞ ንጉሡ ግዞተኛ አደረጓቸው” ይላሉ።

አሁን ኑሯቸውን በሳዑዲ አረቢያ ያደረጉት አቶ ጀማል አሊ ደግሞ የዚህን ማኅበር አመሠራረት በዘመኑ ከነበሩ አባቶች የሰሙትን እንዲህ ይተርካሉ።

“ስሙ “ሰላማዊ ማኅበር” ይባል ነበር።

የተመሠረተው ለአንዋር መስጊድ ቅርብ በሆነውና ከሐጂ መሐመድ ሳኒ ሐቢብ መኖርያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኝ አንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ነበር።

(ሐጂ መሐመድ ሳኒ ሐቢብ በዚያ ዘመን መጀመሪያ የአንዋር መስጊድ ምክትል ኢማም፣ በኋላም ዋና ኢማም ነበሩ።)

ከእርሳቸው ቤት ፊት ለፊት ትልቅ ግቢ ነበር። የቤቱ አከራይ ክርስቲያን ነው። ሆኖም ለሙስሊሞች ቀና አመለካከት እንደነበረው ሰምቻለሁ። ያ ግዙፍ ግቢ ኪራዩ በዓመት 350 ብር ነበር።

ድሮ መውሊድ በዓል ይከበር የነበረውም በዚህ ግቢ ውስጥ ነበር። በኋላ ነው አንዋር መስጊድ ዳስ እየተጣለ መከበር የጀመረው” ይላሉ አቶ ጀማል።

ይህን ሰላማዊ ማኅበር ማን መሠረተው በሚለው ዙርያ አቶ ጀማል ሲናገሩ፣ ‘አንድ ሰው መሠረተው የሚባል አይደለም’ ይላሉ።

“መሥራቾች በዋናነት፡ በዘመኑ በንግድ ሥራ የተሰማሩ፣ ዘመናዊ ትምህርት ተምረው በለስ ቀንቷቸው በመንግሥት ሥራ የተቀጠሩ፣ ከዝነኛው የካይሮው አል አዝሃር ዩኒቨርስቲ የተመረቁ፣ እንደሚገኙበት ሰምቻለሁ።

ከእነዚህ መካከል አብዱረህማን ሸሪፍ (የአንዋር መስጊድ አስተዳዳሪ የነበሩ)፣ ሐጂ በሽር ዳውድ (አል አዝሃር ዩኒቨርስቲ ተመራቂ የነበሩ እና በኋላም የአል-ዓለም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩ)፣ ኡስታዝ አብዱልከሪም (አል ዓለም ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ የነበሩ)፣ ኡመር ኢማም (የመዲና ሕንጻ ባለቤት እና የኦሜጋ ሰዓት አስመጪ የነበሩ)፣ ፊታውራሪ አመዴ ለማ (በኋላ የፓርላማ አባል የነበሩ)፣ አቶ ዩሱፍ አሊ (ነጋዴ)፣ ኮሎኔል አሕመድ አሚኖ፣ መሐመድ ሰብሪ፣ ሰኢድ ካሳዬ (ነጋዴ)፣ ከድር ኢባ (ነጋዴ)፣ ሻሚል ኑርሰቦ (የዕጸገነት ብስኩት ባለቤት) ይገኙበታል።

ከወጣቶች ክንፍ ደግሞ ወጣት መሐመድ ዩሱፍ እና ወጣት ሚሊዮን (በጠቅላይ ኦዲት መሥሪያ ቤት ይሠራ የነበረ) ተሳትፎ እንደነበራቸው ሰምቻለሁ” በማለት እሳቸው ከአባቶች የሰሙትን ለቢቢሲ አብራርተዋል።

ታዲያ የዚህ “ሰላማዊ ማኅበር” ፍጻሜን ያፋጠነው ምን ነበር? ለምንስ በአጭር ተቀጨ?

አቶ ጀማል ከአባቶች ጠይቄ ሰማሁት የሚሉትን ሲናገሩ፣ በጊዜው በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በዘውዱ አገልጋዮች ዘንድ ማኅበሩን በስጋት የማየት ሁኔታ ነበር።

የኤርትራ እንቅስቃሴ መሪዎች በስፋት ሙስሊም መሆናቸውን ልብ ይሏል።

“እንደሰማሁት የማኅበሩ መሥራቾች ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸው ንጉሡ ዘንድ ሄደው ነበር። ንጉሡ ደግሞ ሂዱና አገር አስተዳር አነጋግሩ አሏቸው። አገር አስተዳደር ሄደው ሲጠይቁ ደግሞ “እኔን አቋርጣችሁ ንጉሡ ጋ ሄዳችሁ'ኮ በቃ” ብለው ፊት ነሷቸው።

“የሙስሊሞች በማኅበር መሰባሰብ የፈጠረው ስጋት፣ በተለይ ደግሞ የማኅበሩ የመጨረሻ ሰብሳቢ የነበሩት አሊ ቡርሃን የተባሉ አባት ወደ ኤርትራ ከመሄድ ጋ ተገጣጠመና በዘውዱ የደኅንነት ሰዎች ዘንድ ጥርጣሬን ፈጠረ።

“በመጨረሻ ቢላል መስጊድ አካባቢ የነበሩ ሰኢድ ካሴ የሚባሉ ነጋዴ ዘንድ፣ የማኅበሩ ንብረት በአደራ መልክ ተቀመጠና ማኅበሩ ፈረሰ” ይላሉ አቶ ጀማል።

ይህ ምናልባትም በዘመናዊ የሙስሊሞች ታሪክ የመጀመሪያ የነበረ ማኅበር ከፈረሰ ከጊዜ በኋላ ነው ‘የሙስሊም ወጣቶች ክበብ’ የተመሠረተው።

በአጭር የተቀጨው ‘ሰላማዊ ማኅበር’ን አባቶች ነበር የመሠረቱት።

ቀጥሎ የተመሠረተው የወጣቶች ክበብ ግን በ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ነው የተመሠረተው።

አባቶች ያልሰመረላቸውን ኢስላማዊ ተቋም በሁለት እግር የማቆም ሙከራ ልጆቻቸው ይሰምራላቸው ይሆን?

የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የመሠረቱት ኢስላማዊ ክበብ

ከሰላማዊ ማኅበር በኋላ ሌላ መደበኛም ሆነ ኢመደበኛ ኢስላማዊ ማኅበር ወይም ተቋም ወይም አደረጃጀት በአገሪቱ አልነበረም።

ከአብዮቱ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ በ1964 ግን አንድ ክበብ ተመሠረተ። ለዚያውም በ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች።

ይህ እንደ ዋዛ የተመሠረተ ክበብ በኋላ እንዴት በአብዮቱ ዋዜማ ታላቁን ሰልፍ ለማስተባበር መድረክ እንደሆነ የክበቡ መሥራች እና አሁን ኑሯቸውን በጀርመን ያደረጉት አቶ መሐመድ ሐሰን ለቢቢሲ እንዲህ ይተርካሉ።

“በዚያ ዘመን ሙስሊሙን የሚወክል ተቋም ጭራሽ አልነበረም። ማለቴ መስጊድ አለ፤ የመስጊድ ኢማሞች (አሰጋጆች) አሉ። የመስጊዱ አስተዳዳሪ አለ። ሌላ ተቋም ግን የለም።

ይሄን ታምናለህ? አሁን ላይ ስታስበው የማይታመን ነው። ኮሚኒቲ ሆነን ነበር የምንታየው የምልህ ለዚያ ነው።

አንድ የሐጂ ኮሚቴ የሚባል ነበር። ሥራው የሐጂ መንፈሳዊ ጉዞን ማስተናበር ነው። በቃ ይኸው ነው። በዓመት አንዴ ማለት ነው።

መጅሊስ ግን የለም። ኢስላሙን የሚመራ ተቋም የለም።

በ1964 መድኃኒዓለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ አንድ አብዱ መስኡድ የሚባል አብሮኝ የሚማር ልጅ ነበር።

ኢስላማዊ ክበብ ለምን አንጀምርም ብዬ አማከርኩት። ደስ አለው። ሌሎች ጓደኞቻችን ተቀላቀሉን። አብዶ በሽር ከኮልፌ፣ አበጋዝ ከተግባረ እድ፣ መሐመድ ዩሱፍ ከልዑል መኰንን ትምህርት ቤት (አሁን አዲስ ከተማ የሚባለው) ተገናኘን።

ስብሰባ አደረግን። መሪ አድርገው መረጡኝ።

አምስት ነን መሥራቶቹ። ‘የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች መንፈሳዊ ክበብ’ በዚህ መንገድ ተመሠረተ።

ይሄ ክበብ ኋላ ላይ ለሰልፉ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ልብ አድርግ፤ ሚናው ትልቅ ነው እንጂ ሰልፉን በራሱ አልመራም።

የኛን ክበብ የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ግልባጭ ልትለው ትችላለህ።

ሙስሊም ወጣቶች በንቃት የሚሳተፉበት የስፖርት፣ የሴቶች፣ የሥነ ጽሑፍ፥ የዳእዋ ቡድን አደራጀን።

ነገር ግን ሁነኛ መገናኛ ቦታ አጣን። የት እንሰብሰብ? ጨነቀን።

አንድ ቀን ሐጂ አብዱረህማን ሸሪፍ ጋ ሄድን። እሳቸው ጣሊያን ሠርቶት የሄደው አንዋር መስጊድ አስተዳዳሪ ነበሩ። መሰብሰቢያ ቦታ አጣን አልናቸው። እዚያው አንዋር መስጊድ ግቢ ውስጥ ከፍ ካለው ቦታ-ጉብታው ላይ የሚገኝ አንድ ጠባብ አዳራሽ ነበር።

ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ ለሌላ ነገር እንዳንጠቀምበት አስጠንቅቀው ሰጡን።

ቤተ መጻሕፍት ከፈትንበት። ብዙ ወጣቶች መምጣት ጀመሩ። በዘመኑ የውይይት ክበቦች ፋሽን ነበሩ። ገና እነ ኢህአፓ አልተወለዱም። የጥናት ክበቦች ነው የነበሩት።

መጻሕፍት ማሳደድ ጀመርን። መጻሕፍት ፍለጋ “አሜሪካን ላይብረሪ” እንሄድ ነበር።

ትዝ እንደሚለኝ ቤተ መጻሕፍቱ በቅርቡ በፈረሰው ፒያሳ ኢየሩሳሌም ሕንጻ ላይ ነበር የሚገኘው። ካልተሳሳትኩ በአገሪቱ ብቸኛው ሊፍት የነበረው እዚያ ነበር።

አድዋ ሲኒማ አካባቢ ደግሞ የራሺያ ላይብረሪ ነበር። አቤቱታ አቅርበን መጻሕፍት ሰጡን። ወስደን ክበባችን ቢሮ ደረደርነው።

በዚህ መንገድ የሙስሊሙን ንቃተ ሕሊና ለማዳበር ክበቡ ትልቅ ሚና ተጫወተ።

ከክፍለ አገር የሚመጡ ደረሳዎችን ማስተማር ጀመርን። (ደረሳ ማለት የሃይማኖት ተማሪ ሲሆን፣ ምናልባት አቻው የቆሎ ተማሪ ሊባልይችላል።)

እነሱን ስለ መብት ማንቃት ጀመርን።”

“በተለይ ዘወትር እሑድ ከጠዋት እስከ ቀትር 'ዙሑር ሰላት' ድረስ ትልልቅ እንግዶችን እንጋብዝ ነበር።

ለምሳሌ ሰኢድ ሼክን ጋብዘናል። ሰኢድ ሼክ ማለት ሰኢድ መሐመድ ሳዲቅ ናቸው። ቁርአንን ወደ አማርኛ የተረጎሙ ዐ'ሊም (ምሑር) ናቸው።

በትርጉሙ ሂደት ሐጂ ሳኒ መሐመድ ሐቢብ ረዳት ሆነው የመጡላቸው ሰው ናቸው። ቆራጥ የመብት ታጋይ ነበሩ። የዘውዱ ደኅንነቶች የሚከታተሏቸው ሰው ናቸው። ስለ መብት ያስተምሩናል።

አብዱልከሪም ኑርሁሴንን ጋብዘናል። በጊዜው የማስተርስ ዲግሪ ከአሌክሳንድሪያ ይዘው የመጡ ምሑር ነበሩ።

ሕግን በተመለከተ ደግሞ ከዩኒቨርስቲ አባቢያ አባጆቢርን እንጋብዝ ነበር። (በኢህአዴግ ጊዜ አምባሳደር ሆነዋል፤ የአባ ጂፋር የልጅ ልጅ ናቸው) አሁንም በሕይወት አሉ።

ከሚዲያ ሰዎች ደግሞ ጋዜጠኛ ሐጂ በሽር ዳውድ እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዝነኛ ጋዜጠኛ የነበረውን መሐመድ ኢድሪስን እንጋብዝ ነበር።

ሼክ ሐሚድ ዩሱፍ ባለ አራት ዲግሪ ባለቤት ከግብፅ የመጡ ምሁር አባት ነበሩ። በዚያ ጊዜ ይሄ የማይታመን ነው። እሳቸውም እንደዚሁ ጋብዘናቸዋል።

ብቻ የሙስሊሙን ንቃተ ሕሊና ለማዳበር ብዙ ጥረት ተደረገ።

ይህ ብቻ አይደለም። ከ64-66 በነበሩት ሁለት ዓመታት ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ግንኙነት ፈጠርን። ቴአትር አዘጋጀን። ሙስሊም ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር።

በዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ የኢድ ፓርቲ ይዘጋጅ ነበር። የዩኒቨርሰቲ እና የሃይስኩል ተማሪዎች በጋራ መገናኘት ጀመሩ።

እንደምታውቀው ያኔ የፖለቲካ ትኩሳቱ ከፍ ያለ ነበር። የጥላሁን ግዛውን መገደል ተከትሎ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተቀጣጥሏል። የንባብ ክበቦች በየቦታው ነበሩ።

እኛም በሙስሊሞች የመብት ጉዳይ ላይ እንወያያለን። ንጉሡን የሚተቹ ሰዎችም ነበሩ። የክበቡ አባል የሆኑ በኋላ የታሰሩም፣ የተገደሉም አሉ።

ክበቡ ከአዲስ አበባ አልፎ ናዝሬት፣ ድሬዳዋ፣ ደሴ እያለ ተስፋፋ። ልብ አድርግ፤ በዚያ ጊዜ ሶሸል ሚዲያ የለም። ሬዲዮ የለንም። ለዚያ ነው ለ66ቱ አብዮት ሰልፍ የዚህ ክበብ ሚና ትልቅ ነው የምልህ።”

ከጃንሆይ ደኅንነቶች ሽሽት

አሁን በጀርመን የሚኖሩት መሐመድ ሐሰን ከ52 ዓመታት በፊት የመሠረቱት የወጣቶች ክበብ እንዴት ከታላቁ ሰልፍ ጋር ሊተሳሰር እንደቻለ ለቢቢሲ እንዲህ አጋርተዋል።

“እንደነገርኩህ ጭቆናው አገራዊ ነበር። ሙስሊሙ ደግሞ ድርብ ተጨቋኝ ነው። የመብት ጥያቄዎቹን ሲያነሳ ወዲያው በተገንጣይነት ያስፈርጁታል።

ብሶቱ አደባባይ ገንፍሎ እንዲወጣ የቻለውም ለዚሁ ይመስለኛል።

ሊገነፍል የነበረ ብሶት መልክ ማስያዝ አስፈለገ። አሕመድ ቀሎን የመሰሉ አዋቂዎች የመጡት ይሄን ጊዜ ነው።

በቶሎ ጉዳዩን የሚያስተባብር አንድ ኮሚቴ ተቋቋመ።

ማታ ማታ በኅቡዕ መሰብሰብ ቀጠልን። መንግሥት እንዳይደርስብን ዛሬ መርካቶ፣ ነገ ኮልፌ፣ ከነገ ወዲያ አባ ኮራን እያልን በሰዎች ቤት እያፈራረቅን እንሰበሰብ ነበር።

በዚህ መልኩ በግምት ከ10 ጊዜ በላይ ቁልፍ ስብሰባዎችን አድርገናል።

እኔና ኸሊል የሚባል ወዳጄ (አሁን ካናዳ ይኖራል) በኮሚቴው ወጣቶችን ወክለን እንገኝ ነበር። ነገር ግን ዋና አስተባባሪዎቹ የኛ ታላላቆች ናቸው። ከአባቶችም ከምሁራንም የተውጣጡ ናቸው።

መጀመሪያ ዶክመንት ይዘጋጅ ተባለ። የሙስሊሙን ጥያቄ በጽሑፍ ቀምሮ ለመንግሥት ለማቅረብ ማለት ነው። 7 አባላት ነበሩት ይህ ኮሚቴ፦

  • መሐመድ አወል (ከቴሌኮሚኒኬሽን)
  • አሕመድ ቀሎ (ከአውራ ጎዳና)
  • አብዱ አደም (ስሙ ለጊዜው ያልታወቀ የኩባንያ ባለቤት)
  • ዩሱፍ አሕደም አሊ (የኢንዶ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ)
  • አባ ቢያ አባ ጆቢር አባ ጂፋር (የሕግ ምሁርና ጠበቃ የነበሩ)
  • ኸሊል አብዶና እኔ (ከወጣቶች ክበብ) ነበርን።

ለጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው የሚቀርበው ረቂቅ ከተጠናቀቀ በኋላ በኮሚቴ ጸደቀና ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቀጠሮ ተወሰደ።

13ቱን የሙስሊም ጥያቄዎች የተመረጡ አባቶች ለልጅ እንዳልካቸው አቀረቡ።

ልጅ እንዳልካቸው ምን አሉ?

“የሕጻናት መዋያ” ስብሰባ

መርካቶ፣ ሐደሬ ሰፈር አባድር ኢንስቲትዩት የሚባል አንድ ትንሽዬ ትምህርት ቤት ነበር።

በዚያ የአብዮት ዋዜማ አንድ ስብሰባ በዚህ የመዋዕለ ሕጻናት ግቢ በድብቅ ይደረጋል።

የሳዑዲ አረቢያው ነዋሪ አቶ ጀማል አሊ “ይህ ወሳኝ ስብሰባ የተደረገው ሐደሬ ሰፈር በሚገኘው የአባድር ቅርንጫፍ ሳይሆን ጎላ ሰፈር ወረድ ብሎ ተክለሃይማኖት በሚገኘው ሌላ የአባድር ኢንስቲትዩት ነው” ብለው ይከራከራሉ።

ለማንኛውም ስብሰባው በመዋዕለ ሕጻናቱ ግቢ በአንድ የመማሪያ ክፍል የተደረገ ነው። ጉባኤውን የሚመሩት ደግሞ የሙስሊሙን ጥያቄ ለልጅ እንዳልካቸው አቅርበው ምላሽ ይዘው የመጡ አባቶች ናቸው።

መሐመድ አወል፣ መሐመድ አሊና ጣሃ የሚባሉ የልዑክ አባላት መድረክ ላይ ከፊት ተቀምጠዋል። የኮሚቴው አባላት በጊዜው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ልጅ እንዳልካቸውን አነጋግረው መመለሳቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን መልስ ሰጡ ብሎ ተሰብሳቢው በጉጉት ጠየቀ።

“ጉዳያችሁ ይታያል ብለውናል” አሉ የልዑካን ቡድኑ አባላት።

ይሄን ጊዜ ተሰብሳቢው ተቆጣ። ወጣቶች ሞራላቸው ተነካ። “እስከመቼ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያታልሉን?” የሚል ድምጽ ተሰማ።

ያ የሕጻናት መዋያ በአንድ እግሩ ቆመ “አላሁ አክበር!” ተባለ።

በዚህን ጊዜ ትንታግ ነው የሚባለው አሕመድ ቀሎ እጁን አወጣ፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መልስ የወቅቱን የአብዮት ትኩሳት ያላገናዘበ ነው” ብሎ ማራኪ ንግግር አደረገ።

“በአንድ ደብዳቤ ለውጥ የሚመጣ ከመሰለን ግን ተሳስተናል” ሲል አዲስ የትግል ጥሪ አደረገ። ተሰብሳቢው ወዲያውኑ ድጋፉን ገለጸለት።

ሁለተኛ ስብሰባ ላይ እነ አመዴ ለማ ተገኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጊዜ እንስጣቸው ወይስ አገር አቀፍ ሰልፍ እንጥራ የሚል ክርክር ጦፈ። ክርክሩ የአባድር መዋዕለ ሕጻናት ግቢ ከምትቋቋመው በላይ ነበር።

አሁንም አሕመድ ቀሎ እጁን አወጣ።

“እስከመቼ ነው በዚህ ሕጻናት መዋያ ውስጥ የምነሰበሰው። እስከመቼ ነው የምንፈራው? በግልጽ በመስጊድ ውስጥ መሰብሰብ የለብንም?” ሲል ሌላ የትግል እሳት ለኮሰ።

ተሰብሳቢው “አላሁ አክበር!” በሚል ድጋፍ ሰጠ።

በነገታው እሑድ ስብሰባው መስጊድ ውስጥ ተደረገ። ይህ በዚያ ወቅት የሚታሰብ አልነበረም።

ሙስሊሙን የሚያስተባብር 30 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተመረጠ።

አሕመድ ቀሎ (በኋላ ዶክተር) በድር ለተባለ አንድ መጽሔት ከ8 ዓመት በፊት በሰጠው ቆየት ያለ ቃለ ምልልስ እንደገለጸው ያኔ በአብዮቱ ዋዜማ በስብሰባው የተገኘውን ሺህ ሙስሊም አሰናብተው 30ዎቹ ዝግ ስብሰባ ጀመሩ።

ሕዝቡን በየት በኩል እንድረሰው የሚል ቁልፍ ጥያቄ ሲነሳ አንድ ስማቸው የማይታወቅ አባት “ለምን አሁኑኑ ተበታትነን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ እድሮችን ስም ዝርዝር ይዘን አንመጣም” የሚል ማንም ያላሰበው ሐሳብ አቀረቡ።

ከዚህ በኋላ ነበር የትዕይተ ሕዝቡ ሐሳብ መስመር የያዘው።

የአባድር መዋዕለ ሕጻናት ስብሰባ ከተደረገ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አጋጣሚ የመውሊድ በዓል ደረሰ።

በዓሉ በአንዋር መስጊድ ድንኳን ተቀልሶ ሲከበር የሰልፉ ሐሳብ ተበሰረ።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በድፍረት አደባባይ ሰልፍ ሊወጡ እንደሆነ በይፋ የተነገረውም በዚህ የመውሊድ በዓል ነበር።

“ኃይለኛ የመገፋት ስሜት ስለነበር የሕዝቡ ስሜት ከምነግርህ በላይ አስደንጋጭ ነበር” ይላሉ በዚህ የመውሊድ በዓል ተገኝተው የነበሩት አቶ መሐመድ ሐሰን።

ከዚህ በኋላ ነው ለታሪካዊው ሰልፍ ዝግጅት የተጀመረው።

ሳይሳሱ ቼክ ላይ የሚፈርሙት ባለሃብት

እነ አሕመድ ቀሎ (በኋላ ዶክተር)፣ እነ መሐመድ ሐሰን ማታ ማታ በድብቅ መሰብሰብ ቀጠሉ። ከደኅንነት ሰዎች እየተሽሎኮሎኩ ጓደኞቻቸው ቤት እያደሩ በኅቡዕ ዝግጅቱ ጦፈ።

አሕመድ ቀሎ ያኔ የአውራ ጎዳና ሠራተኛ ነበር።

ከቴሌ ደግሞ መሐመድ አወል የሚባል ሰው ነበር። አሁን በሕይወት የለም። በሂደቱ ትልቅ ሚና ነበረው ይላሉ ወዳጆቹ።

ሐጂ አብዱ አደም የሚባሉ ሰው ከሰልፉ ጋ የተገናኘ ወጪ በካሽ እሸፍናለሁ ብለው ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ሁሉ ያስታውሳሉ።

እኚህን ባለሃብት በተመለከተ አሕመድ ቀሎ “በድር” ከተባለ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ይህን ምስክርነት ሰጥቷል።

አብዱ አደም በጊዘዜ ትልቅ ሃብታም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው ጋ ገብተው አቤቱታ ካቀረቡት አባቶች አንዱ ነበር። አቤቱታው ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ሲረዳ ጠራኝና፣ ‘ማንኛውንም እርዳታ ስትፈልግ የትም እንዳትሄድ’ አለኝ። ገንዘቡን የፈለኩት ለዚህ ነው ለዚያ ነው እንዳትለኝ [ሲል አሳሰበኝ]። ‘ገንዘብ ስትፈልግ [መጠኑ] የፈለገውን ያህል ይሁን ቼክ ቁረጥልኝ በለኝ’ አለኝ። ...እንዲያውም ቼኩን ፈርሞ የፈለኩትን ገንዘብ መጠን እንድጽፍበት ክፍት አድርጎ ለመስጠት ዝግጁ ነበር።”

“እባካችሁ ጊዜ ስጡኝ” ጠቅላይ ሚኒስትር እንደልካቸው

የጀርመኑ መሐመድ ሐሰን የሰልፉን ዋዜማ እንዲህ ይተርካሉ።

“ጥያቄዎቹ ምላሽ ስላላገኙ ሰልፉን ማድረግ የግድ ሆነ። በወቅቱ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጥያቄዎች ነበሩ።

ልጅ እንዳልካቸው በቴሌቪዥን እየቀረቡ “እባካችሁ ጊዜ ስጡኝ -ፋታ ስጡኝ” እያሉ ይማጸኑ ነበር።

የሕዝብ ብሶት አይሎ ስለነበር ተማጽኗቸው ሰሚ አላገኘም።

ለሰላማዊ ሰልፉ ዝግጅቱ ጦፈ።

ለክርስቲያኑ ወገኖች በራሪ ወረቀት ተበተነ። በአባ ቢያ የሚመራ ልዑክ ደግሞ ወደ ቤተ ክህነት ተላከ። ይሄ የሆነው ለምንድነው መሰለህ? ቤተ ክህነት ሰልፉን እንድትረዳው ለማድረግ ነው።

በመጨረሻ የሰልፉን አካሄድ በተመለከተ መግለጫ እንድንሰጥ ወደተለያየ ቦታ ተሰማራን። ዕለቱ ጁምአ ነበር።

እኔ ፒያሳ በኒ መስጊድ ተመደብኩ። ከጁምአ ሰላት በኋላ መግለጫውን አነበብኩ።

ሰብሳቢያችን አቶ መሐመድ አወል ደግሞ የኮሚቴውን መግለጫ እና ለልጅ እንዳልካቸው የተጻፈውን አቤቱታ አንዋር መስጊድ ለተሰበሰበው ሕዝብ አነበበ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው አባካችሁ ፋታ ስጡኝ እያሉ መለመናቸውን ቀጥለዋል። እኛ ደግሞ እስከዚህ ቀን ድረስ መልስ ካልሰጣችሁን ሰልፉን እናደርጋለን እያልን እንዝታለን።"

አሁን የሳዑድ አረቢያ ነዋሪ የሆኑትና በወቅቱቁ ተሳትፎ ከነበራቸው ወጣቶች አንዱ የነበሩት ጀማል አሊ “ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው ለሐጂ አብዱረህማን ሸሪፍ ስልክ እንደደወሉ” አስታውሳለሁ ይላሉ።

“ሰልፉ ይካሄድ ወይስ እንታገስ በሚለው ክርክር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንዋር መስጊድ አስተዳዳሪ ደውለው ‘ሰልፉን ማድረግ አይኖርባችሁም፤ ጥያቄያችሁ በሂደት ይመለሳል’ አሏቸው። ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማጽኖ ሰሚ አላገኘም።”

ለሰልፉ አጥቢያ ሌሊቱን

አሁን አሜሪካ የሚኖሩት አቶ አሕመድ ሑሴን (ሪንጎ) ያቺን የሰልፍ ምሽት እንዲህ ያስታዉሱታል።

“የአንዋር መስጂድ ኢማም የነበሩት ታላቁ ሐጂ መሐመድ ሳኒ ሐቢብ ሰልፉን በሙሉ ልብ አልደገፉትም። ፍርሃት ነበራቸው። ለኛው በመሳሳት ‘እባካችሁ ልጆቼ ተዉ’ ይሉ ነበር።

ሐጂ ሳኒ ወደ ቤት ከሄዱ በኋላ መስጊድ ውስጥ ገብተን መፈክር ስንጽፍ አደርን። እሳቸው ሱብሂ (ለማለዳ ስግደት) ተመልሰው ሲመጡ ደነገጡ።

እኛ ሌሊቱን መፈክር ስንጽፍ ነው ያደርነው፤ ነገሩ ግልብጥብጡ ወጥቷል። ያው ምንም ማድረግ አልቻሉም።

ነገሩን ሐጂ መሐመድ ሳኒ ባይደግፉትም ልጃቸው ሻለቃ በሽር ግን ኃይለኛ የሰልፉ አስተባባሪ ነበር።

በኋላ ያው እሳቸውም ምንም ማድረግ አልቻሉም። ‘አላህ የሰላም ያድርግላችሁ’ ብለው ዱአ አድርገው ሸኙን።”

አቶ ጀማል አሊ በበኩላቸው የሐደሬ ሰፈር ልጆች ቀለም በማምጣት፣ መርካቶ ጣቃ ተራ አቡጀዲ በማዘጋጀት ትልቅ ሥራ ይሠሩ ነበር ይላሉ።

“መፈክር ስንጽፍ ነው ያደርነው፤ ከጻፍናቸው መፈክሮች ትዝ የሚሉኝ፦

“እስላም ምን ታየበት ከሰው በታች የሆነበት”

“ክርስቲያኑ ወገናችን፣ ተሰለፉ ከጎናችን”

“ሃይማኖት የግል፣ አገር የጋራ የሚለው መፈክር ተግባራዊ ይሁን” የሚሉት ናቸው”

'መለስ ዜናዊ ሌሊቱን መፈክር ሲጽፍ ነው ያደረገው'

የሙስሊሞች ሰልፍ በአገሪቱ ለሚፈለገው ሥር ነቀል ለውጥ ይረዳል የሚል መረዳት ስለነበረ ሙስሊም ካልሆኑት ጭምር ሰፊ ድጋፍ ነበረው።

በተለይ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍ ያለ ስለነበር ስልታዊ ድጋፍ ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይሰጥ ነበር።

የጀርመኑ አቶ መሐመድ ሐሰን ይህን በማስመልከት ሲያስታዉሱ እንዲህ ይላሉ፦

“አባ ጆቢር አባቢያ ከካናዳ ትምህርቱን ጨርሶ መምጣቱ ነበር። እሱ ቁልፍ ሚና ነበረው። ተክለሃይማኖት ጋ ከያዕቆብ ኃይለማሪያም ጋር ሆነው አንድ የጠበቃ ቢሮ ከፍተው ነበር።

በኋላ ስመ ጥር የሆኑ፣ ያኔ ግን እንደኛ ተራ ወጣቶች (ተማሪዎች) የነበሩ ስልታዊ ድጋፍ ለሰልፉ ሰጥተዋል።

ከዚህ ሌላ ድጋፍ የሚመጣው ሙስሊም ካልሆኑ ወገኖች ዘንድ እንደነበር አቶ መሐመድ ሐሰን ያስታውሳሉ።

“የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች መፈክር እንዲያዘጋጁ ተነግሯቸው ነበር። እነ ለገሰ ዜናዊ (በኋላ መለስ ዜናዊ) ሰልፉ ሊደረግ ማምሻውኑ መፈክር ይጽፍ እንደነበር አስታውሳለሁ። እሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ በኋላም የበድር ኮሚቴ ሆኜ ወደ ኢትዮጵያ በሄድኩ ጊዜ ለ30 ደቂቃ ያህል አውርቼዋለሁ።

መድኃኒዓለም ተማሪም እያለን እነሱ ዊንጌት ስለነበሩ ቅርባቸው ነበርን። እዚያ የነበሩት ልጆች ትንሽ ይፈሩ ስለነበር እኛ የመድኃኒዓለም ተማሪዎች ነበርን እየሄድን የምናነሳሳቸው።”

ለሰልፉ መለስ ብቻ ሳይሆን ያኔ የእሱ ታላላቅ የነበሩ እና ትልቅ ተሰሚነት የነበራቸው ሌሎች ብዙ የዩኒቨርስቲ ልጆች እገዛ ሰጥተዋል ይላሉ መሐመድ ሐሰን።

ይህን ምስክርነት አሜሪካ የሚኖሩት አቶ አሕመድ ሪንጎም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አቶ አሕመድ የመለስ ዜናዊን ተሳትፎ የሰሙት ከራሱ ከመለስ ዜናዊ የዘመን አቻዎች እና የክፍል ጓደኞቹ ጭምር ነው።

“አቡበከር እና ብርሃኔ ጌታሁን በሕይወት አሉ። እነሱ ነግረውኛል። ከሦስት ዓመት በፊት በአደጋ የሞቱት ታላቅ ወንድማችን የበድር መሥራች መሐመድ አወል የመለስ አቻ ነበሩ። እሳቸውም በሙስሊሞች ሰልፍ የመለስ ዜናዊን ንቁ ተሳትፎ ነግረኛል” ይላሉ።

አባቢያ አባጆቢር (በኋላ አምባሳደር) በዚህ ጉዳይ ላይ ቆየት ካለው የበድር መጽሔት ቃለ ምልልሳቸው ሲናገሩ፦

“…የተማሪውን እንቅስቃሴ እነ ጌታቸው በጋሻው ነበር የሚመሩት። እነ መለሰ ተክሌና ለገሰ (በኋላ መለስ ዜናዊ) [የሙስሊም] ስብሰባ ላይ አብረውን ይመጡ ነበር። እነ ዮሐንስ በንቲ (በኋላ ገላሳ ዲልቦ)፣ እነ ሮቤርቶ ጀዛኖ፣ …እነ እሸቱ ጮሌ (ያኔ በእርግጥ አስተማሪ ነበር)፣ እነ ፍቅሬ መርዕድ (በኋላ ፕሮፌሰር-የ81ዱን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ጄኔራል ልጅ) እነ ዮናስ አድማሱ በሚያስደስት ሁኔታ [ከሙስሊሞች እንቅስቃሴ] ጎን ነበር የቆሙት። የማይረሳኝ ግን መለስ ዜናዊ መፈክር ላይ የሚጻፉ ሐሳቦችን ሲያፈልቅ እና ሲጽፍ ነው ሌሊቱን ያደረው።”

‘ከእናንተ ጋ ለመሞት ነው የመጣሁት’

ሰልፉ ማለዳ ላይ ከአንዋር መስጊድ መነሻውን ያድርግ እንጂ ከመላው የከተማዋ አካባቢ ሕዝብ እየጎረፈ ነበር።

ከዚያ ቀደም ብሎ እንዲህ ዓይነት ሰልፍ ስላልነበረ የሕዝቡ ስሜት ከፍተኛ ነበር።

ዶክተር መሐመድ ቀሎ ከመጽሔት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ይህን ስሜት ሲያስረዱ፦

“ትዝ የሚለኝ ሰልፉ ላይ አንድ የባሕር ኃይል ኦፊሰር ነበር። የሰልፉ ቀን የደንብ ልብሱን ለብሶ፣ ሰይፉን ይዞ፣ መትረየሱን አንግቦ መጣና ‘በቃ ዛሬ መሞታችን ነው፤ እኔም ከናንተ ጋ ለመሞት ነው የመጣሁት’ አለኝ። ‘አይ የምን መሞት አመጣህ፣ ማንም የሚሞት የለም፣ መትረየስህን ዘወር አድርግ ብለን ወስደን አስቀመጥንለት። ሰይፉን ግን እንደታጠቀ ከኛ ጋ ሰልፍ ዋለ። የሕዝቡ ስሜት ይሄን ያህል ነበር።”

የጀርመኑ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው ዕለቱን እንዲህ ያስታውሱታል።

“ዑመር ሰመተር ፊትለፊት ከፎቶ ሉቃስ ከፍ ብሎመዲናየሚባል ፎቶ ቤት ነበር። ባለቤቱ ትልቅ ካሜራ ሰጠኝ፤ የድሮ ካሜራ።

ሰልፉ ላይ 600 የሚሆን ፎቶግራፍ ቀረጽኩ። ልዩ ስሜት የሚፈጥር ሰልፍ ነበር። በኋላ በቀይ ሽብር ጊዜ ደርግ የአባቴ ቤት ፍተሻ ሲያደርግ (አባቴ የምክር ቤት አባል ስለነበረ) ፎቶዎቹን እንዳያገኛቸው በሚል ወንዝ ውስጥ ተጣሉ።

ያን ሰልፍ ከ14ቱም ክፍለ አገር ብቻ ሳይሆን ከኬንያ እና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጭምር ተወካዮች ተሳትፈውበታል።

ሰልፉን እየመራን ከአንዋር መስጊድ ወደ ፒያሳ በራስ መኰንን ድልድይ አድርገን እስከ 4 ኪሎ ሄድን።

ልክ ትምህርት ሚኒስቴር ስንደርስ ትንሽ ረብሻ ተነሳ። ይህም የሆነው ተማሪዎች “የዘውዱ ሥርዓት ይገርሰስ” የሚል መፈክር ይዘው ሰልፉን ሊቀላቀሉ ሲሞክሩ ፖሊስ ጣልቃ በመግባቱ ነበር።

ምናልባት ችግር ከመጣ በሚል የታጠቁ ሙስሊም ሰልፈኞችም እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ነገሩ ግን ረብሻው ቶሎ በረደና ቁልቁል ወደ ቤተ መንግሥት አቅጣጫ ወረድን።

ምናልባትም ዛሬ ሸራተን ያለበት ቦታ ይመስለኛል፣ በዚያ አድርገን በኢዮቤልዩ አልፈን፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትርን በግራ ትተን በሰንጋ ተራ ሜክሲኮ አድርገን ከዚያ ደግሞ በተክለሃይመኖት ወደ አንዋር መስጊድ ተመለስን።

ሰልፉ ከምነግርህ በላይ ስኬታማ ነበር። ምባልባት በኋላ ደርግ እያስገደደ ሕዝቡን ሰልፍ ያስወጣ ስለነበር የኛን ሰልፍ የሚበልጥ ሰው አደባባይ ወጥቶ ይሆናል። ያ ካልሆነ በስተቀር በንጉሡ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊት በታሪክ እንደዚያ ዓይነት ትዕይንተ ሕዝብ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በመቶ ሺዎች የገመቱት ሰልፍ ነበር።”

የሳዑዲው ጀማል አሊ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ሰልፉን በ150 ሺህ ገምቶ ጽፎት እንደነበር ያስታውሳሉ። በዕለቱ ትዝ የሚላቸውን ሲናገሩ፦

“በዕለቱ ከሐደሬ ሰፈር እስከ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ሱቆች ተዘግተው ነበር። ፖሊሶች ረብሻ እንዳይነሳ ብቻ ሳይሆን የኛን ደኅንነት ይጠብቁም ነበር፤ አጅበውን ሲሄዱ ትዝ ይለኛል፤ ክርስቲያን ወንድሞች መንገድ ዳር ሆነው ድጋፋቸውን ይገልጹልን ነበር።”

አቶ ጀማልን ሌላው ከሰልፉ ዕለት ዛሬም ከ50 ዓመት በኋላ የሚደንቃቸው የአዛውንቶች ወኔ ነው።

“አብዮት ሲባል ሁልጊዜ ከወጣቶች ጋር ይያያዛል። በዚህ የሙስሊሞች ሰልፍ ግን ብታምንም ባታምንም አብዛኛዎቹ ሰልፈኞች አዛውንቶች ነበሩ። በቃ ወደ ጦር ሜዳ የሚሄዱ ይመስል በኮዳ ዉሃ ይዘው በከፍተኛ ወኔ ነበር የወጡት።”

የአሜሪካው አቶ አሕመድ ሑሴን (ሪንጎ) ደግሞ ይህን ያስታውሳሉ፦

“ትዝ ይለኛል “የሙስሊሞች በዓል ብሔራዊ ዓመት በዓል ይሁን” የሚለው እኔና ሻለቃ በሽር ነበር ያነገብነው። ሻለቃ በሽር የታላቁ ኢማም የሐጂ መሐመድ ሳኒ ሐቢብ ልጅ ነው።”

ተማሪው ተገልብጦ ተቀበለን። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ተቀላቀሉን። ያው አብዮት አይደለ?

እስከዛሬም የሚገርመኝ ግን በማግስቱ መቶ የማይሞሉ የቤተ ክህነት ሰዎች የኛን ሰልፍ ተቃውመው ሰልፍ አደረጉ። ግን ማንም አልሰማቸውም። ዞር ብሎ ያያቸውም አልነበረም። ሰልፍ ማድረጋቸውንም የሚያውቅ ስለመኖሩ እንጃ።”

የ66ቱ የሙስሊሞች ሰልፍ ትሩፋቶች

13 ጥያቄዎች ነበሩ ለልጅ እንዳልካቸው መንግሥት የቀረበው።

ጥያቄዎቹ የእኩልነት እና የዜግነት ጥያቄዎች ነበሩ።

ወቅቱ የአብዮት ስለነበር ቀጥተኛ ምላሽ አልተገኘ ይሆናል። ነገር ግን በሂደት ደርግ ሲመጣ አንዳንድ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል።

ዶክተር አሕመድ ቀሎ የዚያን ጊዜው ሰልፍ ዋናው ትሩፋት ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ከፍርሃት ቆፈን ማውጣቱ ነው ብለው ያምናሉ።

“በእኛ እና ከእኛ በፊት ሙስሊሞች ላይ ይደርስ የነበረው ዓይነት በደል በአሁኑ ትውልድ ላይ አልደረሰም። ያ እንቅስቃሴ ሙስሊሞችን ብቻ ሳይሆን የክርስቲያኖችን [ለኛ ያላቸውን አመለካከት] ጭምር ነው የቀየረው። …ከኛ በኋላ የመጣው ትውልድ እንደኛ ተሸማቆ አላደገም። [የሚያሳዝነው] አዲሱ ትውልድ ያኔ የነበረውን ሁኔታ አያውቀውም። ለዚህ ያበቃውን ትግል አያውቅም። ያ ለውጥ ባይደረግ ምን ይከተል እንደነበር አያውቅም።”

‘ኢማሙ በእግር ነበር የሚሄዱት’

አባቢያ አባጆቢር በበኩላቸው፣ ደርግ ሲመጣ የሙስሊሙን ጥያቄ ጥንቅቅ አድርጎ ተረድቶ ነው የመጣው። በእሳቸው አረዳድ ይህ ሊሆን የቻለው በዚያ ሰልፍ ምክንያት ነው።

“ከዓላማው ውስጥ አንዱ የሃይማኖት እኩልነት የሚል ነበር። ኢስላማዊ በዓላት እውቅና አገኙ። ለምሳሌ በፊት ከርዕሰ ብሔሮች ጎን የሚቀመጡት ጳጳሳት ብቻ ነበሩ። ከሰልፉ በኋላ ግን የሙስሊም ተጠሪዎችም እንዲታከሉ ተደረገ። ጳጳሳት በመርሰዲስ ሲሄዱ ሐጂ መሐመድ ሳኒ በእግር ነበር የሚሄዱት። በኋላ ለእርሳቸውም መኪና ተመደበ። የሙስሊም ኅልውና በመንግሥትም ደረጃ በማኅበራዊ ኑሮም አንጻር ከፍ አለ” ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው አባጆቢር በዚያ ቃለ ምልልስ የሰልፉን ትሩፋት በአንድ አረፍተ ነገር ሲያስቀምጡት፣ “ሙስሊሙ መብቱን ለመጠየቅ መብት እንዳለው ተረዳ” ይላሉ።

የጀርመኑ መሐመድ ሐሰን የሰልፉን ትሩፋት እና ሙስሊሞች ያቀረቧቸው 13 ጥያቄዎችን በተመለከተ እንዲህ ያሳርጋሉ።

“13ቱን ጥያቄዎች ብትጨምቃቸው አንድ ጥያቄ ይወጣቸዋል፤ እሱም ‘መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኑር’ የሚል ነው። በሌላ ቋንቋ የ‘ሴኩላሪዝም’ ጥያቄ ነው ያነሳነው። ያሳካነውም ይህንኑ ነው።”