በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም ማኅበረሰብ እንዲደርሱላቸው ተማጸኑ

በሱዳን መጠለያ ጣቢያ ያሉ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሱዳን መጠለያ ጣቢያ ያሉ ስደተኞች

በሱዳን ውስጥ እየተባባሰ በመጣው ጦርነት ምክንያት ከባድ አደጋ ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስላቸው ተማጸኑ።

በሱዳን ተነድባ እና ኡምራቁባ ተብለው በሚጠሩ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአገሪቱ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ሚኖሩበት አካባቢ እየተዛመተ በመሆኑ ስጋት ላይ መውደቃቸውን ተናገሩ።

በጄኔራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) የሚመራው እና ከመንግሥት ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ያለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወደ ስደተኞች መጠለያ ካምፖች እየተጠጋ በመሆኑ ደኅንነታቸው አደጋ ላይ መሆኑን ስደተኞቹ ተናግረዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ አብዛኛዎቹ ከምዕራብ ትግራይ የሆኑ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በሱዳን ከ60 ሺህ የማያንሱ ኢትዮጵወያውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይገመታል።

የአምስት ልጆች አባት የሆኑት የ48 ዓመቱ አቶ ወልዱ ሐድሽ ላለፉት አራት ዓመታት በተነድባ ካምፕ ተጠልለው ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ተጠልለው ወደሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች የእርስ በእርስ ጦርነቱ እየተቃረበ በመሆኑ ለከፍተኛ ስጋት ተጋልጠናል ያላሉ።

“ወዴት ልሂድ? ትናንት ልጆቼ እና ቤተሰቦቼ ተደናግጠው ስናለቅስ ነው የዋልነው። በተነድባ ከተማ የነበሩት ሱዳናውያን ሳይቀሩ በፍርሃት እየሸሹ ነው። ሱቆች የነበራቸው፤ አስቤዛ የሚሸጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረታቸውን ጭነው ሸሽተዋል። አካባቢው የጦርነት ቀጠና በመሆኑ ነው የሚሸሹት” ሲል ሁኔታውን ገልጿል።

“ታጣቂዎች ሰዎችን በቢላ ያስፈራራሉ፤ እርጉዝ ሴቶችን ያንገላታሉ፤ ሴቶችን ይደፍራሉ እንዲሁም ወጣቶችን ይገድላሉ። በተለይም የትግራይ ተወላጆችን ‘የሱዳን መንግሥትን ይደግፋሉ’ በሚል ያስራሉ፤ ያሰቃያሉ” በማለት አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ከመጠለያዎቹ ያነጋገራቸው ስደተኞች በተለይም ባለፉት አምስት ቀናት ስጋቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተነድባ ካምፕ ውስጥ ብቻ ወደ 30,000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ። በአሁኑ ጊዜ የሕክምና እና ሌሎች እገዛዎች ሲያደርጉላቸው የነበሩ የእርዳታ ድርጅቶች በጦርነቱን ስጋት ምክንያት ለቀው ወጥተዋል።

የሦስት ልጆች እናት የሆነቸው ወይዘሮ አስቴር ገብረሥላሴ ስደተኞቹ በሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አር.ኤስ.ኤፍ) ታጣቂዎች ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገልጽ መልዕክት እየደረሳቸው መሆኑን ተናግራለች።

“ከመጡ አይተዉንም። በተለይም የትግራይ ተወላጆች ‘በጦርነቱ ተሳትፈዋል’ እየተባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። የተኩስ ድምጽ እየሰማን ነው። [ረቡዕ ሰኔ 26] ተጨንቄ ነው ያደርኩት። ቤቴ ውስጥ ለመተኛት ፈርቼ ነበር” ትላለች።

በጄኔራል ሔሜቲ የሚመራ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ የትግራይን ኃይሎችን ከጄኔራል አል ቡርሐን ጎን ተሰልፈዋል በሚል መክሰሱ የሚታወስ ነው።

“የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር ጎን ተሰልፈው እየወጉን ነው” የሚል ክስ ማቅረባቸው ተከትሎም ስደተኞቹ ስጋት ላይ እንዲወድቁ ምክንያት ሆኗል።

የሔሜቲ ኃይሎች “የህወሓት ኃይሎች በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን ከሚመራው የሱዳን ጦር ጋር ተሰልፈው እየተዋጉን መሆኑን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ይዘናል” ሲሉ በመግለጫ አሳውቀው ነበር።

በወቅቱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ክሱን ቢያስተባብልም በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ግን ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ የጦርነቱ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

“እኛ መጥፎ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ዛሬ ወይም ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም። ምን እንደሚያደርጉን ቁጭ ብለን እየጠበቅን ነው። ተከበናል። ለዜጎቻቸው ካልራሩ እኛን እንዴት ሊምሩን” በማለት አቶ ወልዱ ሐዱሽ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አሁን ባለው አስጊ ሁኔታ ምክንያት የቆየ ከባድ በሽታ ያለባቸው ስደተኞች በድንጋጤ እየወደቁ ህክምና ማግኘት አልቻሉም።

በሔምቲ እና በአል ቡርሃን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት አንድ ዓመት አልፎታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሔምቲ እና በአል ቡርሃን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት አንድ ዓመት አልፎታል

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በዓለም ላይ ትልቁን የዜጎች መፈናቀል ቀውስ እንዳስከተለ የሚገለጽ ሲሆን በአገሪቱ ከ 8.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለዚህ ችግር ተጋልጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተለይ በምሥራቃዊ እና ምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍሎችን የሚገኙ አካባቢዎች እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ።

በመሆኑም ስደተኞቹ የአገራቸው መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲሰጣቸውም ይማጸናሉ።

“የተኩስ ድምጽ በቅርብ እየሰማን ነው። ሰዉ ምን ማድረግ እንዳለበት እና የት መሄድ እንዳለበት ጨንቆታል። የዓለም መንግሥታት እና ሕዝቦች ይመልከቱን። የኢትዮጵያ እና የትግራይ ክልል መንግሥታት በአስቸኳይ ከዚህ ችግር ሊያወጡን ካልቻሉ ሕዝቡ በከፍተኛ ስጋት ላይ ነው ያለው” ይላሉ አቶ ወልዱ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱ እና ጦርነቱ በምሥራቅ ሱዳን ወደሚገኙ ተነድባ እና ኡምራቁባ ወደ ሚባሉት የስደተኞች መጠለያዎች እየተቃረበ መምጣቱ እንዳሳሰባቸውም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱም ተቀናቃኝ ኃይሎች ግጭቱን እንዲያቆሙ እና የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት እንዲጠብቁ ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የፌደራል መንግሥቱም የኢትዮጵያውያኑ ስደተኞችን ስቃይ ለማስቆም የተቻለውን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።