አሜሪካ የዝንጀሮ ፈንጣጣ የኅብረተሰብ የጤና ስጋት ነው ስትል አወጀች

ክትባት እየወሰደ ያለ ሰው

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአሜሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የአገሪቱ መንግሥት በሽታው የኅብረተሰብ የጤና ስጋት ነው ሲል አወጀ።

መንግሥት በሽታው የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ነው ብሎ ማወጁ፤ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የክትባት ስርጭት እንዲስፋፋ፣ ሕክምና እና የፌደራል መንግሥት ሃብት እንዲጨምር ያደርጋል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ የተሰማው የዓለም ጤና ድርጅት ከሁለት ሳምንት በፊት በሽታው የዓለም ሕዝብ የጤና ስጋት ነው ብሎ ካወጀ በኋላ ነው።

እስካሁን በአሜሪካ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ6ሺህ 600 መሻገሩን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል አንድ አራተኛው በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ የተመዘገበ ሲሆን ካሊፎርኒያ እና ኢሊኖይስ ከኒው ዮርክ በመቀጠል በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኛ ግዛቶች ሆነዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ከ26ሺህ በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል (ሲዲሲ) አሐዝ ያሳያል።

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የትኛውም ሰው ሊይዝ የሚችል ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በበሽታው በብዛት እየተያዙ ያሉት በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች ነው።

አንዳንድ የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች በሽታው ‘የኅብረተሰብ ጤና ስጋት’ ተብሎ መታወጁ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ሊያገል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በቀጥታ በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ኢንፌክሽን ባይሆንም፤ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ማድረግ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በጣም ሊያሳክክ እና ሊያሳምም የሚችል ሽፍታን በቆዳ ላይ ይፈጥራል። ይህ ሽፍታ በመላው የሰውነት ክፍል ተሰራጭቶ ሌላ የጤና ስጋት ሊፈጥር ይችላል።

ይህ በሽታ ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ሕመም አያስከትልም። በሆስፒታል ተኝቶ መታከምን ሳይጠይቅ በራሱ ግዜ ሊጠፋም ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን ሕጻናት በዚህ በሽታ የመሞት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው ይላሉ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው ያሏቸው የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች ቀድመው መከላከያ ክትባት መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት አቅርቦት እጥረት መኖሩን የሚያመላክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።