አዲሱ ክልል አራት ዋና ከተሞች እንዲኖሩት ማድረጉ የሚኖረው አንደምታ

በይፋ ተመሰረተ የወራት ዕድሜ ያለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ የከተሞች ማዕከላትን ለመስተዳደሩ ተቋማት ለማደራጀት ወስኗል።
ሌሎቹ ክልሎች ማዕከላቸውን በአንድ ዋና ከተማ አድርገው ቢሮዎቻቸው በአንድ ስፍራ ላይ እንዲዋቀሩ በማድረግ ይታወቃሉ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግን ከሌሎቹ በተለየ ለየት ያለ አደረጃጀትን ለመከተል መርጧል።
በዚህም ከትናንት በስተያ ረቡዕ ሐምሌ 27/2014 ዓ.ም. የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አራት ዋና ከተሞች እንዲኖሩት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለክልሉ ምክር ቤት አቅርቧል።
ይህ ረቂቅ ሕግ የሚጸድቅ ከሆነ በክልሉ ካሉ ስድስት ዞኖች በአራቱ የዞን ከተሞች የክልሉ መስተዳደር ዋና ዋና አካላት መቀመጫ ይሆናሉ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል አካል የነበሩት ስድስት ዞኖች ተባብረው የመሠረቱት ክልል ነው።
በረቂቁ መሠረትም ቦንጋ የፖለቲካ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ጽህፈት ቤት መቀመጫ ትሆናለች።
ተርጫ የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫ፣ ሚዛን አማን የዳኝነት መዋቅሩ የሚገኝበት እንዲሁም ቴፒ የብሔረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫን ይይዛሉ።
ሥራ አስፈጻሚ ቢሮዎች ደግሞ በአራቱም ከተሞች ፍትሃዊ ሆነው ይመደባሉ ተብሏል።
ይህ አዲስ የክልል አደረጃጀት የተለያዩ ሃሳቦች እየተሰነዘሩበት ነው። አንዳንዶች የክልሎችን ሥራና ሃብት በአንድ ከተማ ላይ ብቻ በማከማቸትን በማፍሰስ ከሌሎች ከተሞች በበለጠ አንድ ከተማ ብቻ በላቀ ሁኔታ እንዲያድግና ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርገውን አሰራር ይለውጣል ሲሉ ይደመጣል።
ሌሎች ደግሞ ይህ የክልል መስተዳደር ተቋማትን በተለያዩ ከተሞች ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረግ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚፈልጉ ነዋሪዎችን ለወጪ እና እንግልት ከመዳረጉ ባሻገር፣ በክልሉ ተቋማት መካከል በቅርበት በትብብር የመስራት ዕድልን ከማጓደል ባሻገር አባካኝ ሊሆን ይችላል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
‘ተገልጋዮችን ያጉላላል’
አቶ ደያሞ ዳሌ ቀደም ሲል በደቡብ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው።
ይህ የክልሉ አስተዳደር እቅድ የክልሉን ነዋሪዎች ሊያጉላላ ይችላል ሲሉይናገራሉ።
የክልሉ መንግሥት ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው “በፖለቲካዊ ውሳኔ” ነው የሚሉት አቶ ደያሞ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አንድ ክልል ከአንድ በላይ ከተማ ሲኖረው ታይቶ እንደማይታቅ በማስታወስ ነው።
ጨምረውም እንዲህ አይነቱ ልምድ ያለው በሰለጠኑት አውሮፓ አገራት ውስጥ ነው ይላሉ።
“እንዴት ተግባራዊ ያደርጉታል የሚለውን ባለቤቶቹ ናቸው የሚያውቁት። ይህም ወደፊት የምናየው ይሆናል። ወጪው ከፍተኛ ይሆናል” ይላሉ አቶ ደያሞ።
ረቂቅ ሕጉ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትም ሆነ፤ አገልግሎት ለማግኘት ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ነው የሚሉት አቶ ደያሞ አራቱ ከተሞቹም የተመረጡበት መስፈርትም ግልጽ አይደለም ይላሉ።
“አራቱ ከተሞች በምን ተመረጡ? ትላልቅ ስለሆኑ ነው የተመረጡት ወይስ ከዞኖች ተወጣጥተው ነው? ያልደረሳቸው ከተሞች ቅሬታስ እንዴት ይፈታል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
ከአንድ በላይ የማዕከል
የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያሉ ነዋሪዎችን ፍላጎት ለማማከል ሲባል ከዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱን ይናገራሉ።
ይህ ክልል ሲመሰረት ማዕከላዊ ከተማው ማን ይሆናል የሚለው ብዙ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር ይላሉ አቶ ፀጋዬ።
“አንዳንድ ከተሞች ማዕከላዊ ከተማው እኛ ጋር ካልሆነ ክልሉን አንቀላቀልም የሚል አቋም ይዘው ስለነበር፤ በወቅቱ የነበረው አመራርም ሆነ ክልሉ ሲመሰረት የነበረው አመራር ከአንድ በላይ የማዕከል ከተማ ይኖራል በሚል ተነጋግረው ነበር” ይላሉ።
“ሰው ሳይጉላላ እና ሥራ ሳይጎዳ እንዴት አድርገን ነው ብዘሃ ከተሞችን የምንፈጥረው በሚለው ላይ ተነጋግረን አጠናቀናል” ይላሉ።
አንድ ነዋሪ ጉዳይ ለማስፈጸም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሳይጓዝ ጉዳዩን ባለበት መጨረስ የሚያስችሉ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮዎችም ታስበዋል ይላሉ።
“ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ የሚሸጋገሩ ተግባራት ካሉ፤ አገልግሎቱን የሚሰጡ ላይዘን ጽ/ቤቶች አብረን ለመፍጠር ነው ያሰብነው” ይላሉ።
በክልሉ የመንግሥት ተወካይ የሆኑት አቶ ፀጋዬ፤ ክልሉ አራት መዲናዎች እንዲኖሩት መደረጉ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል የሚል እምነት የለንም በማለት ይናገራሉ።
“ለምሳሌ አንድ ቢሮ በጀት ቢፈልግ ለፋይናንስ ቢሮ ወረቀት ይልካል እንጂ፣ በአካል ወደ አንድ ከተማ መጥቶ ገንዘብ አይወስድም፤ ስለዚህ የተለየ ወጪ አይኖርም” በማለት ያስረዳሉ።
በየትኛው ከተማ ምን አይነት ቢሮዎች ይኑሩ የሚለው ቀድሞ በስምምነት የተደረሰበት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፀጋዬ፤ “በዚህ ከተማ ይህ ቢሮ ይኑር የተባለው በስምምነት እንጂ በሳይንሳዊ ምክንያት አይደለም” ይላሉ።
የክልሉ ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ተወያይቶ ካጸደቀው በኋላ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል።
ይህ በአገሪቱ ካሉ ሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ የተደራጀው የአዲሱ ክልል አስተዳደር መዋቅር ድጋፍም ጥያቄም ከተለያዩ ወገኖች እየተነሱበት ነው።
ነገር ግን ከክልሉ ብዝሃነት አኳያ ማዕከሉን በአንድ ስፍራ አድርጎ የእድገትም ሆነ ሌሎች ዕድሎችን በአንድ ከተማ ላይ ከማከማቸት ይልቅ በተለያዩ ስፈራዎች መሆኑን በአዎንታ የሚመለከቱት አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ የመንግሥት ሥራዎችና አገልግሎቶችን በተለያዩ ስፍራዎች ላይ እንዲሆኑ መደረጋቸው ለሕዝቡ እንግልት፣ በክልሉም ላይ ከፍተኛ ወጪን ሊያስከትላል የሚችል ነው ይላሉ።
ቢሆንም ግን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ያስተዋወቀው አዲስ የከተሞችና የአስተዳደር ተቋማት አወቃቀር ሊኖረው የሚችለው ጥቅምም ሆነ የሚገጥመው ተግዳሮት ወደ ፊት የሚታይ ነው።












