በእስራኤል የሚገኙ ኤርትራውያን ተጎጂዎችን ለመርዳት አልባሳት እያሰባሰቡ ነው

በእስራኤል የሚኖሩ ኤርትራውያን በአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ ተጎጂዎችን ለመርዳት አልባሳት፣ ውሃ እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እያሰባሰቡ ነው።

በቴል አቪቭ ነዋሪ የሆነው የ43 ዓመቱ ሃለፎም ሱልጣን ኤርትራውያን በሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ተሳታፊ ነው።

ሃለፎም፣ እንዲህ ዓይነት በጎ ተግባር እስራኤላውያን በእስራኤል ለሚገኙ ኤርትራውያን የተለየ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳለው ለቢቢሲ ተናግሯል።

መስከረም ወር ላይ በቴል አቪቭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ጎራ ለይተው በፈጠሩት ግጭት 170 ሰዎች ከተጎዱ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ “ቀይ መስመር ተጥሷል” ብለው ነበር።

“በርካታ እስራኤላውያን እንደ አደገኛ ሕዝቦች ነው የሚያዩን።ለአፍሪካውያን ስደተኞችም አሉታዊ አመለካከት ነው ያላቸው።ሆኖም እስራኤላውያን በሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ላይ የኤርትራ ማኅበረሰብ ተሳትፎ አዎንታዊ ውጤት ሊያመጣ ይችላል።” ብሏል።

ሃለፎም እንደ አውሮፓውያኑ 2018 የእስራኤል መንግሥት አፍሪካውያን ስደተኞችን "ወደ ሦስተኛ አገር ለማሸገጋር በወጣው መርሃ ግብር" መሰረት ስደተኞችን ለመመለስ ባቀደበት ወቅት የተቋቋመው የኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ማኅበረሰብ ድርጅት ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል።

ሃለፎም ቅዳሜ ጠዋት ላይ በቴል አቪቭ በተሰሙ የማስጠንቀቂያ ድምጾች ከእንቅልፉ መንቃቱን ይናገራል።

“የሮኬት ድብደባውን ሰማሁት።በጣም ያስደነግጥ ነበር።ከዚያም ዜና ለማየት ስልኬን ከፈትኩ።” ብሏል።

በቴል አቪቭ የማስጠንቀቂያ ድምጽ ከጠፋ በኋላ በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል ሮሆቮት ከሚኖር የሌላ አገር ዜጋ ስልክ እንደተደወለለት ይናገራል።

“ልጆቹ ወደ መጠለያ ውስጥ እንዲገቡ እየነገራቸው ነበር ።በስልክ እያወራን የማስጠንቀቂያ ድምጾች እና ሁለት ሮኬቶች ሲያርፉ መስማት ችያለሁ።” ብሏል።

በሐማስ ስለታገቱ ሰዎች ሲሰማም በጋዛ አቅራቢያ በምትገኘው አሽኬሎን የሚኖሩ ሌሎች ኤርትራውያንን አነጋግሮ እንደነበር የገለጸው ሃለፎም፣እስካሁን የታገቱ አሊያም የተገደሉ ኤርትራውያን ስለመኖራቸው አለመስማቱን ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ መሰረት በእስራኤል ከ53 ሺህ በላይ ጥገኝነት ጠያቂዎች ይኖራሉ። አብዛኞቹም ከኤርትራ እና ከሱዳን የተሰደዱ ናቸው።