ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ግብዣ ቱርክ ገብተዋል
አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበ ውዝግብ ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ፕሬዝዳንት ጋባዥነት ውይይት ለማድረግ ዋና ከተማዋ አንካራ ገብተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከኢትዮጵያ ጋር ይደረጋል ለተባለው ሦስተኛ ዙር ንግግር ማክሰኞ ዕለት ወደ ቱርክ መሄዳቸውን የሶማሊያ መንግሥት ዜና ወኪል ሶና ገልጿል።
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ቱርክ መግባታቸውን ጽሕፈት ቤታቸው ቢያስታውቅም ከሶማሊያ መሪ ጋር ንግግር እንደሚኖር ያለው ነገር የለም።
የሶማሊያ መንግሥት የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ጉዞን አስመልክቶ እንዳሳወቀው ግን አንካራ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር በሚካሄደው ሦስተኛ ዙር ንግግር ላይ ለመሳተፍ መሆኑን አመልክቷል።
ነገር ግን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የሚያደርጉት ንግግር በቀጥታ በመሪዎቹ መካከል ይሁን ወይም የቱርክ መሪን በመጠቀም በተዘዋዋሪ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።
በየትኛውም መልኩ ሁለቱ መሪዎች በዚህ ውይይት ላይ የሚነጋገሩ ከሆነ በአፍሪካ ቀንድ አገራቱ መካከል ውዝግብ ከተፈጠረበት ካለፈው ዓመት በኋላ በመሪዎች ደረጃ የተደረገ የመጀመሪያው ንግግር ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ አንካራ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አመሻሽ ላይ አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን እንጂ ከሶማሊያው መሪ ጋር ይደረጋል ስለተባለው ንግግር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ የተባለ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለፈው ዓመት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተካረረ ሌሎች አገራትም በቀጥታ እና በዘዋዋሪ እየተሳተፉበት ነው።
ሶማሊያ የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተፈራረመችው ስምምነት የባሕር ጠረፍ ሰጥታ የአገርነት ዕውቅና የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ሲነገር ቆይቷል። በዚህም የተነሳ በስምምነቱ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቴን ጥሳለች ስትል ትከሳታለች።
ይህ በኢትየጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተካረረ አለመግባባትን የፈጠረው የሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ማብቂያ ላይ ከተፈረመ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ቢሆንም እስካሁን ከሁለቱም ወገኖች ስለተግባራዊነቱ የተባለ ነገር የለም።
ሶማሊያ ስምምነቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታ ከማቅረቧ በተጨማሪ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከምትኘው ግብፅ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ላይ በመድረስ ውጥረቱ ተባብሷል።
በተጨማሪም ሶማሊያ በአገሯ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር በማስወጣት አዲስ አበባ የነበሩትን አምባሳደሯን ጠርታለች። እንዲሁም ለዓመታት በተሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቷ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ቆይታለች።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ውዝግብ ለማርገብ ቱርክ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ሁለት ዙር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ንግግር መምራቷ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ፕሬዝዳንት አማካይነት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሶማሊያ መንግሥት ዜና ወኪል እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ግብዣ ወደ አንካራ ማምራታቸውን የሶማሊያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ቱርክ ባለፈው ዓመት ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በማነጋገር አገራቱን ለማቀራረብ ሁለት ዙር ንግግሮች ብታደርግም ውጤት ሳይገኝ መቅረቱ ይታወሳል።
አሁን በፕሬዝዳንት ኤርዶዋን አማካይነት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ንግግር ሦስተኛው ዙር ሲሆን፣ ቱርክ የሁለቱ አገራት ወዳጅ አገር ስትሆን ምጣኔ ሀብታዊ እና ወታደራዊ ስምምነት አላት።