ከክሪፕቶ ጋር በተያያዘ አድናቂዎቹን አሳስቷል የተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ

በማኅበራዊ ሚዲያ ዕውቅናን ያተረፈው ሎጋን ፖል አሳሳች ክሪፕቶ ኢንቨስትመንት በማስተዋወቅ ከአድናቂዎች ትርፍ አግኝቶ ሊሆን ይችላል በሚል ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው።

ቢቢሲ ያገኛቸው አዳዲስ ማስረጃዎች ፖል ጥቅም እንደሚያገኝበት ሳያሳውቅ ኢንቨስትመንቶቹን እንደሚያስተዋውቅ ያሳያሉ።

ዩቲዩብ ላይ 23 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ፖል የእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ዋጋ እንዲጨምር ያደረገ ይመስላል። በዚህም ባሉት ቶከኖች ሽያጭ ትርፍ ሊያገኝ ይችል እንደነበር ጥቆማዎችን ሰጥቷል።

ፖል ክሪፕቶዙ በተባለው እና ከከሰረው የክሪፕቶ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ክስ ተከፍቶበታል።

ተጽዕኖ ፈጣሪው ግን የተነሱበትን ክሶች በሙሉ ክዷል።

እአአ በ2021 ፖል ስለ አንድ ክሪፕቶ ትዊተር ላይ ከመጻፉ ጥቂት ቀደም ብሎ ማንነቱ ካልታወቀ ክሪፕቶ ጋር በይፋ በሚታወቀው የክሪፕቶ ዋሌቱ ይገበያይ ነበር።

ያልታወቀው ዋሌትም 120 ሺህ ዶላር ትርፍ አግኝቷል።

የቢቢሲ የምርመራ ውጤት ይፋ የሆነው ታይም መጽሔት ከሌላ ክሪፕቶከረንሲ እና ማንነቱ ካልታወቀ ዋሌት ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መኖሩን ከዘገበ በኋላ ነው።

ከምርመራው ጋር በተያያዘ ፖል ለበርካታ ወራት ከቢቢሲ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ አልሆነም ነበር። በኋላም ሃሳቡን በመቀየር በፖርቶ ሪኮ በሚገኘው ጂም ቃለ መጠይቅ እንዲደረግለት ፈቃዱን ሰጥቷል።

የቢቢሲ ባልደረቦች በቦታው ሲደርሱ ግን ዩትዩበሩ ሳይሆን ሎጋን ፖልን የሚመስል ግለሰብ ብቅ አለ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች መጥተው ቢቢሲን መስደብ ጀመሩ።

ቃለ መጠይቁን አለመሳካቱ ከታወቀ ከደቂቃዎች በኋላ ምርመራው ከታተመ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ከፖል ጠበቃ ለቢቢሲ ደረሰው።

ሜም ኮይንስ

ሎጋን ፖል አጫጭር የቪዲዮ ክሊፖችን አሁን በተዘጋው ቫይን ቀጥሎም ዩቲዩብ ላይ በመጫን ዝነኛ ከመሆን ባለፈ ዓለም አቀፍ ተከታታዮችን አፍርቷል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ደግሞ የፖል ቪዲዮዎች ክሪፕቶን መነካካት ጀመሩ።

ክሪፕቶ የባንክ ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልገው ደኅንነቱ የተጠበቀ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ዲጂታል የገንዘብ ዓይነት ነው።

ፖል እአአ በ2021 ከፍተኛ ጥርጣሬ የሚነሳባቸውን “ሜም ኮይንስ” የሚባሉ የክሪፕቶ ቶከኖችን አስተዋውቋል።

ብዙውን ጊዜም በበይነ መረብ ቀልዶች ወይም ሜሞች ላይ ተመሠረቱ ሲሆኑ፣ በበይነ መረብ ተከታታዮችም የተደገፉ ናቸው። የሜም ኮይኖች ከመገበያየት ውጭ ሌላ ትክክለኛ ዓላማ የላቸውም። ምንም አይነት ዋጋ ስለሌላቸው ብዙውን ጊዜ ዋጋቸው ቀንሶ ዜሮ ሊሆን ይችላል።

ፖል ኢላንጌት በመባል የሚታወቀውን እና የኢላን መስክ ምሥል ያለበትን የሜም ኮይን አወድሷ። “ኢላንጌት ሃብታም አደረገኝ። ኢላን የኔ ውድ!” ሲል በምዝገባ ብቻ ለሚከተሉት አድናቂዎቹ ቪዲዮዎችን በሚለቅበት ማቭሪክ ክለብ በኩል አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎም የኢላንጌት ዋጋ ከ6 ሺህ በመቶ በላይ ተመነደገ። ይህም የምንጊዜውም ከፍተኛ ዋጋው ሆኗል። በዚህ ዋጋ ለጥቂት ሰዓታት ሲገበያይ ከቆየ በኋላ ዋጋው አሽቆለቆለ።

ሎጋን ፖል ቪዲዮውን ሲለቅ በምን ዓላማ እንደነበር እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ስለኢላንጌት መናገሩ በዋጋው ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ግን ይመስላል።

ክሪፕቶ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚመራ ገበያ ነው ሲል የቴክኖሎጂ ጋዜጠኛው ዊል ጎተሴገን ተናግሯል። “ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው... እንደ ሎጋን ፖል ያለ ሰው ብዙ ክሪፕቶ ገዝቶ ለተከታዮቹ ይነግራል። እነሱም ይገዛሉ” ብሏል።

እንደቢቢሲ ምርመራ ከሆነ ማንነቱ ያልታወቀ የክሪፕቶ ዋሌት ከፖል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ይመስላል።

የክሪፕቶ ዋሌት (መሳሪያዎች ወይም የበይነ መረብ አገልግሎት ሊሆን ይችላል) የተጠቃሚዎችን የመለያ ቁልፎች ይይዛሉ። ሰዎች ክሪፕቶ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉ እና እንዲገበያዩም ያድርጋል።

ማንኛውም ሰው በዋሌት የተደረጉ ግብይቶችን ማየት ይችላል። ባለቤቱ ግን እንዳይታዩ ሊያደርግ ይችላል። ስማቸውን ወይም የግል መረጃቸውን ካያያዙት “ፐብሊክ ዋሌት” ይሆናል።

ዋሌቱ እአአ የካቲት 2021 የሎጋን ፖል ከነበረ ፐብሊክ ዋሌት ገንዘብ እንደተቀበለ ማየት ተችሏል። በኋላም ክሪፕቶ መግዛትና መገበያየት ጀመረ።

ሎጋን ፖል፡ መጥፎው ተጽዕኖ?

በዓለም ላይ ካሉት ታላላቅ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ የሆነው ሎጋን ፖል የክሪፕቶፕ ፕሮጄክቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ለተጫወተው ሚና ትችት ተሰንዝሮበታል። ማት ሺአ ጉዳዩን ይመረምራል።

ለሕግ አስከባሪ አካላት እና ለተጎጂዎች በመናገር እና ግለሰቡን ለመቅረብ በመሞከር ሎጋን ፖል ስህተት ሠርቷልን? ለሚለው ጥያቄ የመጨረሻ መልስ ለመስጠት ሺአ ፍላጎት አለው።

ዋሌቱ ከማቭሪክ ክለብ ተከፍሎታል። ፖል ግንቦት 10 ቀን 2021 ሲያስተዋውቅም ኢላንጌትን ይዞ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ፖል በትዊተር ገጹ “ወደ ጨረቃ” እያመራ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ከመስክ ጋር በተዛመደ ሚም ኮይን ተገበያየ። ይህም በክሪፕቶ ማኅበረሰብ ዘንድ የኮይኑ ዋጋ ሊጨምር ነው ብሎ እንዲያምን ያደርጋል ማለት ነው።

ከፖል ትዊተር አንድ ሰዓት ገደማ ቀድም ብሎ ካልታወቀው ዋሌት 160 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው ቶከን ተገዝቷል። ትዊቱ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ገዢዎች እንዲጎርፉለት አድርጓል።

ከ12 ሰዓታት በኋላ ዋሌቱ አብዛኛውን ድርሻውን ሸጠ። ከዚህ ግብይት የተገኘው አጠቃላይ ትርፍ ከ120 ሺህ ዶላር በላይ እንደሆነ ይታመናል።

ሎጋን ፖል ከክሪፕቶ ዋሌት፣ በውስጡ ካለውን የንግድ ልውውጥ ወይም ከእሱ ጋር ስላለው ግንኙነት ለቢቢሲ ምላሽ ላለመስጠት ቢመርጥም በጠበቆቹ በኩል ለአንዳንድ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

ዲንክ ዶይንክ

ፖል እአአ ሰኔ 2021 “ዲንክ ዶይንክ” የተባለ የሜም ኮይን አስተዋውቋል።

ድርሻ የገዛ ማንኛውም ሰው ጥቅልል ብረት የሚመስል የካርቱን ገጸ ባህሪያትን ያገኛል። በቴሌቭዥን ወይም ፊልም ላይ ከታየ ከገቢው የተወሰነውን ያገኛሉ።

ፖል በትዊተር ላይ ቶከኑን ሲያስተዋውቅ እና የዲንክ ዶይንክ ቴሌግራም “አምኜበታለሁ” ሲል ተናግሯል። “ይተኮሳል ብዬ አስባለሁ” ሲልም አስታውቋል።

ይህም ከፍተኛ የገዢዎች ፍሰት አስከትሎ የዲንክ ዶይንክ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል። ከዚያ የተለመደው ዑደት ቀጠለ። የትላልቅ የቶከን ባለቤቶች መሸጥ ጀመሩ። በሁለት ሳምንታት ውስጥም ዋጋው በ96 በመቶ እንዲቀንስ ሆነ።

ሎጋን ፖል ኮይኑን ማስተዋወቁ በፊት ዲንክ ዶይንክ የገዛ እና ብዙም ሳይቆይ የሸጠን ሌላ ማንነቱ ያልታወቀ ዋሌትን ታይም መጽሔት መርምሯል። በኋላ ላይ ዋሌቱ 100 ሺህ ዶላር ወደ ፖል ፐብሊክ ዋሌት ልኳል።

ቢቢሲ ተፅዕኖ ፈጣሪውን ስለዚህ ዋሌት ሲጠይቅ ጠበቆቹ የእሱ መሆኑን አልካዱም። ለእሱ ጥቅም ታስቦ የተያዘ መሆኑንም በተመሳሳይ ባይክዱም የተላለፈው 100 ሺህ ዶላር ከዲንክ ዶይንክ ጋር ግንኙነት የለውም ብለዋል።

ፖል ዲንክ ዶይንክን እንደተገበያየ ቢቀበሉም ያገኘው ግን 17 ሺህ ዶላር ብቻ ነው ይላሉ።

ፖርቶ ሪኮ

ፖል ለበርካታ ወራት ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም።

ሳይታሰብ ግን ከወንድሙ ጋር በባለቤትነት በሚያስተዳድረው እና በፖርቶ ሪኮ በሚገኘው የቦክስ ጂም ውስጥ ቢቢሲን ሊያናግር ተስማማ።

ፖል ምላሽ እንዲሰጥበት የሚፈለጉ ዝርዝር ጉዳዮች ተላኩለት። የሕዝብ ግንኙነት ቡድኑ ግን ቢቢሲ ወደ ካሪቢያን ደሴት ተጉዞ በአካል ሲገኝ ብቻ መልስ እንደሚሰጠው አስታወቀ።

በተጨማሪም ደሴቲቱ በትሮፒካል አውሎ ንፋስ ኤርኔስቶ እየተመታች ባለችበት ወቅት ቢቢሲ ወደ ደሴቲቱ እንዲበር አጥብቀው ጠየቁ።

በጂሙ ውስጥ ግን እንግዳ የሆነ ድባብ ተፈጠረ። አጠራጣሪ ቁጥር ያላቸው ካሜራዎቹ ወደ ቢቢሲ ሰዎች አማተሩ። ረዳቱም ባለው የጊዜ ሰሌዳ ምክንያት ፖል ወደ ክፍሉ ከሚገባበት ጊዜ ጀምሮ የቢቢሲ ካሜራዎች መቅረጽ እንዳለባቸው አጥብቆ ተናገረ።

ከዚያም ነገሮች የበለጠ እንግዳ ሆኑ። ሎጋን ፖል ሳይሆን እሱን የሚመሰል ግለሰብ መጥቶ ከቢቢሲ ሪፖርተር ማት ሺአ ፊት ተቀምጦ ለመምሰል ሙከራ ጀመረ።

ቢቢሲ ጉዳዩን በመረዳት ለፖል ረዳት አሳወቀ። እውነተኛው ሎጋን ፖል ይመጣ እንደሆነም ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ሰዎች ድንገት ብቅ ብለው ቢቢሲን በመሳደብ መጮኽ ጀመሩ።

ቢቢሲ ያን ሁሉ መንገድ የተጓዘው ሊቀለድበት ነበር።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ታዋቂ ሰዎች የግል የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ሳይገልጹ ለተከታዮቻቸው ክሪፕቶ በማስተዋወቅ ችግር ውስጥ ገብተዋል።

ኪም ካርዳሺያን እአአ በ2022 ኤተሪየምማክስ የተባለ ቶከን በኢንስታግራም ገጿ ላይ በማስተዋወቅ 1.26 ሚሊዮን ዶላር ተቀጥታለች።

የአሜሪካን የኢንቨስትመንት ኢንዱስትሪ የሚቆጣጠረው የሴኪውሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን (ሴክ) ኃላፊ የሆኑት ጋሪ ግንስለር እንደሚሉት ከሆነ አንድ ታዋቂ ሰው ክሪፕቶን እያስተዋወቀ ከሆነ “ከተከፈለው ሊያሳውቅ ይገባል፣ ምን ያህል ተከፈለው? ቶክን ካላቸው፣ በቶከኖቹ ገንዘብ ሠርተው እንደሆነ እና ስለ ፕሮጀክቱ የሚያውቁት ነገር እንዳለ” ማሳወቅ አለባቸው።

ክሪፕቶዙ

ሎጋን ፖል አሁን ክሪፕቶዙ በተባለው ቀጣዩ ሥራውን በሚመለከት ክስ ቀርቦበታል።

ይህ እንደ በይነ መረብ የንግድ ካርድ ጨዋታ ለገበያ ቀርቦ ነበር። በካርዶች ምትክ ግን ክሪፕቶዙ ኤንኤፍቲዎችን በመጠቀም ዋጋ ሊኖራቸው የሚችል የዲጂታል ጥበብ ስብስቦች አሉት።

ክሪፕቶዙን ለማጫወት ዙ ቶከን የተባለ ክሪፕቶ ከረንሲ መግዛት አስፈላጊ ነው። ይህም የኤንኤፍቲ “እንቁላል” ለመግዛት ሊያገለግል ይችላል።

እነዚህ እንቁላሎች ውሎ አድሮ ወደ የኤንኤፍቲ “እንስሳት” ይፈለፍላሉ ተብሎ ነበር። እንደ ፔንግዊን-ሻርክ እና ፓንዳ-ፊን ያሉ ስሞች ያሏቸው “ድብልቅ እንስሳትን” ያስገኛሉ።

እነዚህ ድቅል እንስሳት ተጨማሪ መካነ አራዊትን በማመንጨት ተሳታፊዎች ገንዘብ እንደሚያገኙ ያግዛሉ ሲሉ የፖል ተወካዮች ተናግረዋል።

መስከረም 2021 ላይ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎም “ገንዘብ የሚያስገኝ በጣም አስደሳች ጨዋታ ነው” ሲል ፖል ተከታዮቹ ተናግሯል።

ክሪፕቶዙ ወደ 18.5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ስቧል።

የሰሜን ምሥራቅ እንግሊዝ ነዋሪው የ21 ዓመቱ ሩበን ታውክ ክሪፕቶዙን ከገዙ የሎጋን ደጋፊዎች መካከል አንዱ ነበር።

“እሱ (ሎጋን ፖል) እያደረገ ያለው ነገር አካል በመሆኔ በጣም ተደስቼ ነበር።”

ጨዋታው ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ግን በችግር ተተብትቦ ነበር።

“የሚለቀቁትን ባህሪያት በተመለከተ የተወሰኑ ተስፋዎች ተሰጥተውናል። ብዙ ጊዜ ግን እነዚህ ነገሮች አይሠሩም” ሲል ሩበን ተናግሯል።

“ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሆነ ስህተት እንዳለ መገንዘብ ትጀምራለህ” ብሏል።

የዙ ቶከን እና እንቁላሎቹ ዋጋ ማሽቆልቆል ጀመረ። ሩበን 33 ሺህ ፓውን እንደከሰረ ተናግሯል።

በትንሹ 130 የሚደርሱ ሰዎች በፖል ክስ ላይ ተሳትፈዋል (ሩበን ከእነሱ አንዱ አይደለም)። ወደ 4.2 ሚሊዮን ዶላር ማጣታቸውን ይናገራሉ።

ከክሱ በስተጀርባ ያለው ጠበቃው ቶም ኬርከር (በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ ታዋቂ ዩቲዩበር ነው) ጨዋታውን አለማድረስ የጉዳዩ አካል ብቻ ነው ይላል።

ሾልከው የወጡ መልዕክቶች ፖል እና ቡድኑ በዝቅተኛ ዋጋ እንዲገዙ ለመፍቀድ በዙ ቶከን “በድብቅ በተደረገ ማስጀመሪያ” ላይ እንደተሳተፉ ያሳያል ብሏል።

“ቡድኑ በሥርጭት ላይ ያለው የዙ ቶከን አጠቃላይ ዋጋ 200 ሚሊዮን ዶላር ሲደርስ መሸጥ እንደሚጀምር ተስማምቶ ነበር” ብሏል።

“ይህ ለሕዝብ በሚሸጥ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ ትክክለኛው ሰነድ ካለ በሁለት ሰከንድ ውስጥ በማጭበርበር ይከሰሳሉ። ይህ የውስጥ ለውስጥ ንግድ ነው” ሲል አክሏል።

ፖል ከክሪፕቶዙ ጋር የተያያዘ ጥፋት አለመፈጸሙን ደጋግሞ አስተባብሏል። ይልቁንም ቃላቸውን አላካበሩም ባላቸው ሌሎች ቡድኑ አባላት ላይ ጥፋቱን አላኳል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቅር ለተሰኙ ባለሃብቶች አነስተኛ የማካካሻ ዘዴን አስታውቋል። ኤንኤፍቲ እንቁላል የገዙ ሰዎችን ገንዘብ ለመመለስ ቃል ገብቷል። ይህ ግን የሚሆነው ከክሪፕቶዙ ጋር በተገናኘ እሱን ላለመክሰስ ከተስማሙ ብቻ ነው።

ፖል ከዓላማው ጋር በተያያዘ በቀረበበት ጉዳይ አሜሪካ ውስጥ ካሉት የበይነ መረብ ተቃዋሚዎቹ ከሆኑት በአንዱ ላይ የስም ማጥፋት ክስ እያቀረበ ነው።

የሎጋን ፖል ተደማችነት በአድናቂዎቹ ላይ የተመሠረተ ነው። የመቀነስ ምልክት እያሳየ አይደለም።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፖል ፊቱን ወደ ቦክስ እና ትግል አዙሯል። ከብሪታንያው ተጽእኖ ፈጣሪ ኬኤስአይ ጋር በመሆን ፕራይም የተሰኘ የመጠጥ ኩባንያ አቋቁሟል።

በተሠራው ማስታወቂያ ምክንያት ምርቱ በጣም ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። በድጋሚ የቀረቡ ፕራይም ምርቶችም በመቶ ፓውንዶች እንደሚሸጡ ማስታወቂያ ተነግሮላቸዋል። ይህም በዋነኝነት የሎጋን ፖል እና የኬኤስአይ በወጣት ታዳሚዎቻቸው ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ የሚያሳይ ነበር።

ለአንድ ተከታዩ ግን ይህ ምሥሉ እስከወዲያኛው ተበላሽቷል።

“አንድን ሰው ሰምተህ የሚናገረውን አምነህ ያንን እምነት ከበላ በኋላ ቃላቶቹ ለአንተ ምንም ትርጉም የላቸውም” ብሏል ሩበን።