የጋዛ ጋዜጠኞች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን የዜና ወኪሎች አስጠነቀቁ

በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን መመገብ የማይችሉበት የከፋ ሁኔታ ላይ መድረሳቸውን ቢቢሲ እና ሶስት የዜና ኤጀንሲዎች አስጠነቀቁ።

እስራኤል በጋዛ እያደረሰችውን ያለውን የማያባራ ጥቃት እየዘገቡ ያሉ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ለረሃብ "ከቀረው ፍልስጤማውያን ጋር በከፋ ሁኔታ መጋለጣቸውን" ቢቢሲ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ሮይተርስ በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

ሚዲያዎቹ "ለበርካታ ወራት እነዚህ ነጻ ጋዜጠኞች በጋዛ ምድር ላይ እየሆነ ላለው ነገር የዓለም አይን እና ጆሮ ሆነው ቆይተዋል" ብለዋል።

ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች የጋዛን ጦርነት እንዳይዘግቡ እንዲሁም ወደ ግዛቶቹ እንዳይገቡ እስራኤል በመከልከሏ በርካታ ሚዲያዎችም ሆነ የዓለማችን ህዝብ በጋዛ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር የሚረዳው ከነዚሁ ጋዜጠኞች ነው።

ከ100 በላይ አለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋዛ የፍልስጤም ህዝብ በከፋ ረሃብ እንደሚመታ እያስጠነቀቁ ባለበት ወቅት ነው ሚዲያዎቹ ይህንን መግለጫ ያወጡት።

"በጋዛ ያሉ ጋዜጠኞቻችን ራሳቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን መመገብ ተስኗቸዋል ይህም ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቦናል" ይላል መግለጫው

መግለጫው "ጋዜጠኞች በጦርነት ቀጣና ውስጥ በርካታ ፈተናዎች እና መከራዎችን ይቋቋማሉ። የረሃብ ስጋት ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ነው" ብሏል

አክሎም "የእስራኤል ባለስልጣናት ጋዛ ውስጥ ጋዜጠኞች እንዲገቡ እንዲፈቅዱ በድጋሚ እናሳስባለን።

እንዲሁም በቂ የምግብ አቅርቦት በጋዛ መግባቱ መሰረታዊ ነው" ሲል ያትታል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ)፣ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ እና ኦክስፋም በጋራ ባወጡት መግለጫ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ፍልስጤማውያኑ "እየረገፉ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ወደ ጋዛ የሚገቡ እርዳታዎችን እና የሸቀጥ ፍጆታዎችን የምትቆጣጠረው እስራኤል የረድዔት ድርጅቶቹ "የሃማስን ፕሮፓጋንዳ እያስተጋቡ ነው" ስትል ከሳለች።

ከእሁድ ጀምሮ 45 ፍልስጤማውያን በረሃብ ሳቢያ መሞታቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።

የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ተቋም አቋቁመዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

እስካሁን ድረስ የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ 798 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አርብ ዕለት አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም 615 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት አንድ አራተኛው የጋዛ ህዝብ በረሃብ እየተፈተነ መሆኑን ባደረገው ግምገማ ገልጿል።

"የጅምላ ረሃብ ከማለት ውጭ ሌላ ምን እንደምትሉት አላውቅም፤ ይህም በሰው ሰራሽ ምክንያት የተፈጠረ ነው" ሲሉ የተቋሙ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረ እየሱስ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

"ይህም መንስዔው በጣም ግልጽ ነው፤ በእገዳው ምክንያት ነው" ብለዋል።