የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት በጋዛ የምግብ ማሟያ ሲጠባበቁ የነበሩ ህጻናት ተገደሉ

የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት በጋዛ የህክምና ማዕከል አቅራቢያ የምግብ ማሟያ ሲጠባበቁ የነበሩ ስምንት ህጻናት እና ሁለት ሴቶችን ጨምሮ 15 ሰዎች ሰዎች መገደላቸውን አል አቅሳ የሰማዕታት ሆስፒታል አስታወቀ።

ዴይር አል ባላህ በተሰኘችው ከተማ ህጻናቱን ጨምሮ የምግብ ማሟያ (ኒውትሪሽናል ሰፕልመንት) ለመቀበል ሲጠባበቁ የነበሩ እነዚህ ግለሰቦች እሰራኤል በጥቃት እንደገደለቻቸው ሆስፒታሉ አክሏል።

ከሆስፒታሉ የተገኘ ቪዲዮ የበርካታ ህጻናት አስክሬኖች ወለል ላይ ተዘርግተው፤ እንዲሁም ሌሎች የቆሰሉ በርካቶችንም የህክምና ባለሙያዎች ህክምና ሲያደርጉላቸው አሳይተዋል።

የእስራኤል ጦር በአካባቢው "የሃማስ አሸባሪ" ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል። "ተሳትፎ በሌላቸው ግለሰቦች ላይ ለሚደርሱ ማንኛውም ጉዳቶች ማዘኑን" ገልጾ፤ ጥቃቱ እየተገመገመ ነው ብሏል።

ከነዚህም በተጨማሪ የእስራኤል ጦር ሐሙስ ዕለት በጋዛ በፈጸመው ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል።

እነዚህ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያሉት የእስራኤል እና የሐማስ ልዑካን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በዶሃ ቀጥተኛ ባልሆኑ ውይይቶች እየተሳተፉ ባሉበት ወቅት ነው።

ከኳታር እና ከግብጽ ጋር በጥምረት የማሸማገሉን ስራ እየሰራች ያለችው አሜሪካ ተስፋ ብታሳይም እስካሁን ወደ ስኬት የተቃረበ አይመስልም።

የተገደሉ ሰዎች ጸሎት ተደርጎ የቀብር ስነ ስርዓት ከመከናወኑ በፊት፤ በአልአቅሳ ሆስፒታል የአስክሬን ማቆያ የሚወዷቸውን ያጡ ቤተሰቦች ሲያለቅሱ እና ሲያነቡ፤ የተገደሉትን ህጻናት በነጭ መሸፈኛ ሲጠቀልሉ ታይተዋል።

ከተገደሉትም መካከል ነፍሰ ጡር የሆነችው የእህቷ ልጅ ማናል፣ የሷ ልጅ ፋጢማ እንደሚገኙበት አንዲት ሴት ለቢቢሲ ተናግራለች። የማናል ልጅ በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኝ አክላለች።

"ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ለልጆቹ የምግብ ሟሟያ ለማግኘት ተሰልፋ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም" ስትል ኢንቲሳር ተናግራለች።

ከአንቲሳር አጠገብ ቆማ የነበረች ሌላ ሴት "በምን ኃጢያት ነው የተገደሉት?" ስትል ጥያቄዋን ወርውራለች። "አለም ሁሉ እያየ እና እየሰማ እየሞትን ነው። መላው ዓለም የጋዛ ሰርጥን እየተመለከተ ነው። ሰዎች ከእስራኤል ጦር ጥቃት ግድያ ካመለጡ እርዳታ ለማግኘት ሲሞክሩ ይገደላሉ" ብላለች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል መስከረም መጨረሻ በደረሰው ጥቃት የተሳተፈ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የኑክባ ጦር አባል መምታቱን አሰታውቋል።

የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት እቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል።

በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ "ሰብዓዊ ከተማ" ለማቋቋም እንደሚፈልጉ የተናገሩት ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ ይህም በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን የሚቆዩበት ካምፕ ይሆናል ብለዋል።

በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ህዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሚሆን አክለዋል።

ዕቅዱ የሐማስ አባላት አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የጸጥታ እና የደህንነት ምርመራ አድርጎ ወደ ካምፑ ለማስገባት እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከጦርነቱ በኋላ ጋዛን ተቆጣጥራ ፍልስጤማውያንን አፈናቅላ በቋሚነት ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ያቀረቡትን ሃሳብ አስመልክቶ በዋይት ሐውስ ተወያይተዋል።

ከዚህ ቀደም የአረብ መንግሥታት ትራምፕ ላቀረቡት የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ አማራጭ የሆነውን ፍልስጤማውያን ባሉበት እንዲቆዩ ለሚያስችለው የግብጽን የ53 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ ድጋፍ አድርገዋል።

ማንኛውንም የፍልስጤም ህዘብ የመፈናቀል ዕቅድ የዓለም አቀፍ ህግን የሚጥስ፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ሲሉ ሙሉ በሙሉ የአረብ መንግሥታቱ ውድቅ አድርገውታል።