የአሜሪካ ባለሥልጣናት በኬንታኪ ከደረሰ አደጋ በኋላ ተመሳሳይ ስሪት ያላቸው የጭነት አውሮፕላኖችን ከበረራ አገዱ

በኬንታኪ የደረሰውን የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ተከትሎ የታየ ጥቁር ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ አቪዬሽን ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት በኬንታኪ ለበረራ ሲነሳ የተከሰከሰውን የጭነት አውሮፕላን ተከትሎ ተመሳሳይ ስሪት ያላቸው ሁሉም አውሮፕላኖች እንዳይበሩ አዘዙ።

በዩፒኤስ ባለቤትነት የሚንቀሳቀሰው ቦይንግ ኤምዲ-11 አውሮፕላን በሉዊቪል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ በእሳት ጋይቶ በአቅራቢያው ካሉ ሕንጻዎች ጋር በመጋጨቱ 14 ሰዎች ሞተዋል።

የአሜሪካው የማጓጓዣ ድርጅት ቀደም ሲል ፌዴክስ የመሰረተውን ክስ ተከትሎ እየተደረገ ያለውን ምርመራ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ያሉትን አውሮፕላኖች እንደማያበር ተናግሮ ነበር።

አሁን የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ሁሉንም ኤምዲ-11 እና ኤምዲ11ኤፍ አውሮፕላኖች የደኅንነት ፍተሻዎች እስኪደረግላቸው ድረስ እንዳይበሩ የሚከለክል መመሪያ አውጥቷል።

እነዚህን አውሮፕላኖች የሚጠቀሙት ዩፑኤስ፣ ፌዴኤክስ እና ዌስተርን ግሎባል አየር መንገዶች ሲሆኑ በአጠቃላይ 70 ስሪቶች በሥራ ላይ አሉ።

የኤፍኤኤ ባለስልጣናት እንደተናገሩት የኬንታኪው አደጋ የተከሰተው የአውሮፕላኑ የግራ ሞተር በእሳት በመያያዙ እና ከክንፉ ላይ ተገንጥሎ በመውደቁ ነው።

አውሮፕላኑ ወደ ሃዋይ ለመብረር ሲነሳ 144,000 ሊትር ነዳጅ ጭኖ የነበረ ሲሆን ይህም ከአደጋው በኋላ ለቃጠሎው መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል።

የሉዊስቪል ከንቲባ ክሬግ ግሪንበርግ እንዳሉት በአደጋው ​​እና በተነሳው የእሳት ቃጠሎ 14 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ አንድ ሰው ደግሞ ሆስፒታል ገብቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ወቅት የሟቾች ቁጥር ከጠፉት ሰዎች ቁጥር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም የተነሳ ባለሥልጣናቱ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ይጨምራል ብለው እንደማይጠብቁ ተገልጿል።

ቦይንግ መመሪያውን እንደሚቀበል ተናግሮ ሞዴሉን የሚጠቀሙ ሦስቱ ኩባንያዎች "ለከፍተኛ ጥንቃቄ" በሚል ሥራቸውን እንዲያቆሙ ምክር መስጠቱን ተናግሯል።

ይህ ክልከላ በአሜሪካ ውስጥ ዕቃዎችን የማድረስ አገልግሎቶች ላይ ተጽዕኖው ምን ያህል እንደሚሆን እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ከሦስቱ ኩባንያዎች መካከል አንዳቸውም እስካሁን ድረስ አገልግሎት ስለማቋረጣቸውን ያሉት ነገር የለም።

የቀጥታ በረራዎችን የሚከታተለው የአየር ትራፊክ ድረ ገጽ፣ ፍላይት ራዳር24 የሰበሰበው መረጃ ባለፈው ሳምንት ብቻ 55 ኤምዲ-11 የጭነት አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ እንደዋሉ ያሳያል።

ፌዴክስ ባወጣው መግለጫው እንዳስታወቀው "አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እንደ ሕይወት አድን መድሃኒቶች፣ የሕክምና መሳሪያዎች እና ሌሎች ወሳኝ ምርቶች ሳይዘገዩ መጓጓዝ እንዲችሉ በአየር እና በምድር የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ዝግጁ የሆኑ የመጠባበቂያ ዕቅዶች አሉን" ብሏል።

ዩፒኤስም እንዲሁ አገልግሎቱን ለመቀጠል የመጠባበቂያ ዕቅድ አስቀምጦ እንደነበር ተናግሯል። መግለጫው በመቀጠል "ከሠራተኞቻችን እና ከምናገለግላቸው ማኅበረሰቦች ደኅንነት በላይ ለእኛ ምንም ቀዳሚ ነገር የለም" ብሏል።

የመንገደኞች አውሮፕላን ለመጨረሻ ጊዜ ኤምዲ-11ን የተጠቀመው እአአ በ2014 ነበር። ከዚያ በኋላ ሞዴሉ ለጭነት ማጓጓዣነት ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል።

አደጋው ​​ያጋጠመው አውሮፕላን ባለ ሦስት ሞተር የሆነው ሞዴል ኤምዲ-11ኤፍ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት የጀመረው ከ34 ዓመት በፊት በታይ ኤርዌይስ የመንገደኞች አውሮፕላን በመሆን ነበር።

ከዚያ በኋላ ግን እአአ በ2006 ወደ ዩፒኤስ ተዛውሯል።

ኤምዲ-11 አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረተው ኩባንያው ከቦይንግ ጋር እአአ በ1997 ከመቀላቀሉ በፊት በማክዶናልድ ዳግላስ ነበር።

የኤምዲ-11 አውሮፕላኖችን ማምረት እአአ በ2000 አብቅቷል።