አሜሪካ ከኳታር የተሰጣትን የ400 ሚሊዮን ዶላር አውሮፕላን ለትራምፕ መጓጓዣነት እያዘጋጀች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ከኳታር የተሰጣትን አውሮፐላን 'ኤይር ፎርስ ዋን' በሚል መጠሪያ ለፕሬዚዳንቶች መጓጓዣነት እንዲውል በሚሆን መልኩ ለትራምፕ እያዘጋጀች መሆኑን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘገበ።
ኳታር 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው የቦይንግ አውሮፕላን ለአሜሪካ የሰጠችው በስጦታ ከቅድመ ሁኔታ ጋር ሳይያዝ መሆኑ ተገልጿል።
ሆኖም ለአውሮፕላኑ ማሻሻያ የሚያስፈልጉ ወጭዎች በአሜሪካ መንግሥት የሚሸፈኑ ይሆናል።
በኳታር የተደረገው ስጦታ ከትራምፕ ተቃዋሚዎች እንዲሁም አንዳንድ ደጋፊዎች ዘንድ ትችትን የቀሰቀሰ ሲሆን የተወሰኑትም በውጭ ኃይል የተደረገ "ሙስና" ሲሉ ጠርተውታል።
ዋይት ሐውስ አውሮፕላኑን መቀበል ህጋዊ ነው ሲል የተከራከረ ሲሆን፤ ትራምፕ ከስልጣን መንበራቸው ከለቀቁ በኋላም ለፕሬዚዳንታዊ ቤተ መጻህፍታቸው እንደሚበረከት ቃል ገብቷል።
አሁን ያሉት ህጎች የአሜሪካ ባለስልጣናት መቀበል የሚችሉት ስጦታዎች ከ480 ዶላር በታች መሆኑን ይጠቁማሉ።
በኳታር እና በአሜሪካ የመከላከያ ዲፓርትመንት መካከል የተደረሰው እና ሲቢኤስ የተመለከተው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት አውሮፕላኑ እንዳለ ከተሰጠ በኋላ በኤይር ፎርስ ዋን ስም ለፕሬዚዳንቱ መገልገያ ከመዋሉ በፊት የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ፔንታጎን በበላይነት የሚቆጣጠር ይሆናል።
አውሮፕላኑ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊትም የደህንነት ፍተሻዎች ይደረግበታል።
"በዚህ የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ የትኛውንም አይነት ጉቦ፣ ያልተፈለገ ተጽዕኖ፣ ሙስናዊ አሰራር ወይም እንደ ስጦታ ወይም ቃል ኪዳን ተብሎ ሊታይ ወይም ሊተረጎም አይገባውም" ሲል ሰነዱ ያትታል።
አክሎም "ሁለቱም አካላት ስጦታው በቅን ልቦና የተደረገ መሆኑን ያረጋግጣሉ" ይላል።
አሜሪካ የኳታርን የአውሮፕላን ስጦታ ተቀብላለች የሚለው ዜና የትራምፕ ወግ አጥባቂ ደጋፊዎችን ጨምሮ በጎራ የተለያዪ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ ትችቶችን አስተናግዷል።
"ነውር እና አሳፋሪ ነው" ሲል የወግ አጥባቂው እና ደይሊ ዋየር ተንታኝ የሆነው ቤን ሻፒሮ በፖድካስቱ ላይ ተችቷቸዋል።
"ኳታር ለፕሬዚዳንት ትራምፕ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጄት በቸርነት ከልባቸው ሰጥታለች ማለት አይቻልም"
አክሎም "በተለየ መንገድ በገንዘብ ለመደለል እየሞከረች ነው" ብሏል።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቀኝ አክራሪዋ ላውላ ሊመር በበኩሏ ይህንን አውሮፕላን በስጦታ መቀበል አስተዳደሩ ላይ "ጥላሸት ቀብቶት" ያለፈ ነው ስትል ትችቷን አቅርባለች።
በአሁኑ ወቅት ፕሬዚዳንቱ የሚገለገሉባቸው ሁለቱ 747-200 የተሰኙት ጄቶች ከአውሮፓውያኑ 1990 ጀምሮ በአገልግሎት ላይ ያሉና አነስተኛ ናቸው።
ትራምፕ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ኩባንያ በቀጥታ ይሰጧቸው ተበለው ሲጠብቋቸው የነበሩ ሁለት ኤይር ፎርስ ዋን አውሮፕላኖች ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
አስተዳደሩ "አውሮፕላን መግዛት ወይም ማግኘት ይችል እንደሆነም" በወቅቱ አስተያየታቸውን ሰንዝረው ነበር።















