ያረጀው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላን - ኤር ፎርስ ዋን እና ባለ 400 ሚሊዮን ዶላሩ የኳታር ስጦታ

ኤር ፎርስ ዋን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርካታ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጋር የሚጓዙ ጋዜጠኞች የፕሬዝዳንቱን አውሮፕላን ውስጣዊ ገጽታዎች የማየት ዕድል የላቸውም።

ጋዜጠኞች የሚቀመጡት ከአውሮፕላኑ የጀርባ ክፍል ነው። ወደ ፕሬዝዳንቱ ክፍል ለማለፍ በሚቀጥለው በር ከሚገኙ ከታጠቁ የደኅንነት ሠራተኞች ጋር መደራደር ይጠይቃል።

ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉትን ጉዞ ተከትሎ የወደፊቱ የፕሬዝዳንቱ ግዙፍ አውሮፕላን የሁሉም መነጋገርያ ሆኖ ነበር።

የፎክስ ኒውስ አቅራቢው ሺን ሀኒቲ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተቀምጦ ቃለ ምልልስ የማድረግ ዕድል አጋጥሞት ነበር።

ነገር ግን ከርዕሰ ብሔሩ ጋር ለሚጓዙ ለተቀሩት የመገናኛ ብዙኃን አባላት መቀመጥ የተፈቀደው በጠባቧ የአውሮፕላን ክፍል ብቻ ነው።

በሦስት ቀናት ሦስት አገራትን ያዳረሰ ጉዞ ነበር። ይህንን የጽህፈት ቤቶቻቸው ሠራተኞች እና የፕሬስ አባላት የተሳተፉበት አድካሚ ጉዞ ፕሬዝደንቱ "ጽናት የሚፈተንበት" ሲሉ ገልፀውታል።

በእርግጥ የፕሬዝደንቱ አውሮፕላን ለጉዞ የሚያስቸግር አልነበረም። ያሉት 14 መቀመጫዎች ልክ በመደበኛ በረራ ላይ እንዳሉ የመጀመሪያ ደረጃ ክፍሎች ምቹ ናቸው።

መታጠቢያ ቤት፣ የተለያዩ ምግቦች፣ የትም የማይገኙ እና የፕሬዝደንቱ ፊርማ ባረፈባቸው መሸፈኛዎች የታሸጉ ጣፋጮች ይገኙበታል።

የአውሮፕላኑ የበረራ አስተናጋጆች ዓለምን የሚከታተሉበት ሁለት ቴሌቪዥኖች አሏቸው።

እነዚህ ቴሌቪዥኖች ፕሬዝዳንቱ የሚመርጧቸው ጣቢያዎች ሥርጭትን ያስተላልፋሉ። በጆ ባይደን ዘመን ሲኤንኤን ይከፈት የነበረ ሲሆን፣ አሁን በትራምፕ ዘመን ደግሞ ፎክስ ኒውስ ተመራጭ ጣቢያ ነው።

አንዳንድ ጊዜ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ወይንም የስፖርት ዝግጅቶች ይከፈታሉ።

በረዣዥም በረራዎች ላይ ምግብ አብሳዩ የተለያዩ ምግቦችን አዘጋጅቶ ያቀርባል። ፕሬዝደንቱ የተለያዩ ጣዕም ያላቸው ምግቦችን መርጠው ይዘጋጅላቸዋል።

ለአጭር በረራ ግን በስሎ የተዘጋጀ ምግብ ታሽጎ ይቀርባል።

ጃኪ ኬኔዲ ባለቤቷ ጆን ኦፍ ኬኔዲ በ1963 መገደሉን ተከትሎ ሊንደን ጆንሰን በኤር ፎርስ ዋን ውስጥ ፕሬዚደንት ሆኖ ቃለ መሃላ ሲፈጽም እየተመለከተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጃኪ ኬኔዲ ባለቤቷ ጆን ኦፍ ኬኔዲ በ1963 መገደሉን ተከትሎ ሊንደን ጆንሰን በኤር ፎርስ ዋን ውስጥ ፕሬዚደንት ሆኖ ቃለ መሃላ ሲፈጽም እየተመለከተች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኳታር ንጉሥ ለፕሬዝደንት ትራምፕ አዲስ "የሠማይ ላይ ቤተ መንግሥት" የተባለለትን አውሮፕላን የሚሰጡ ከሆነ፣ የዚህ የፕሬዝደንቱ አውሮፕላን ውስጣዊ ገጽታ ሙሉ እድሳት ተደርጎለት በቅርቡ መቀየሩ አይቀርም።

በእርግጥ የኳታር ንጉሥ ለአሜሪካው ፕሬዝደንት የሚሰጡት ይህ ስጦታ እስካሁን የአሜሪካ ርዕሰ ብሔር ከተቀበሏቸው ሁሉ ትልቁ ስጦታ ሆኖ ይመዘገባል።

የፕሬዝደንቱ መጓጓዣ አውሮፕላን የሆነው ኤር ፎርስ ዋን የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶችን መጠቀሚያ የሆነ የአየር ኃይሉ ንብረት ነው።

የአሜሪካ 36ኛው ፕሬዝደንት ሊንደን ጆንሰን ከኦስቲን ወደ ቴክሳስ መኖሪያቸው በ1960ዎቹ ይዘውት የሄዱት ትንሽዬ አውሮፕላንም ኤርፎርስ ዋን ነበር።

ነገር ግን ኤር ፎርስ ዋን ብዙ ሰው የሚያስበው ሃሪሰን ፎርድ በተወነበት በድርጊት የተሞላ ፊልም ላይ የሚታየው 747-200ቢ በቀዳማዊት እመቤት ጃኪ ኬኔዲ በ1962 ተመርጦ የተቀባው ውሃ ሰማያዊ ቅብ ያለው፣ ዙሪያው ሰማያዊ እና ነጭ ቀለም የተቀባ አውሮፕላንን ነው።

በአሁኑ ጊዜ ከ1990 ጀምሮ በአገልግሎት ላይ ያሉ ሁለት 747 የኤር ፎርስ ዋን የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖች ናቸው።

በአውሮፕላኖቹ ውስጥ የተገጠሙ ቴክኖሎጂዎች፣ ዲዛይኑ እና ሁሉም ነገር የመጪውን ዘመን ታሳቢ ተደርገው የተሠሩ ናቸው። አውሮፕላኖቹ ተሻሽለዋ፤ነገር ግን አውሮፕላኑን እና ሞተሮቹን ለመጠገን የሚወጣው ወጪ እየጨመረ ነው የመጣው።

አውሮፕላኖቹ እድሜያቸውን መደበቅ አልቻሉም።

ከኳታር የሚበረከተው ባለ 400 ሚሊዮን ዶላሩ አውሮፕላን የወቅቱን የዋይት ሐውስ መሪ የራሳቸው አውሮፕላን ያላቸው ብቸኛ ፕሬዝደንት የሚያደርግ ሲሆን፣ ነገር ግን ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንትነት ሥልጣንን ከመያዛቸው በፊትም የራሳቸው አየር መንገድ የነበራቸው ግለሰብ ናቸው።

ሐሙስ ዕለት አቡዳቢ የነበራቸውን ስብሰባ ሲያጠናቅቁ "አሁን ይህንን ትቼ የ42 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ወደ ሆነው ቦይንግ እገባለሁ" በማለት የአውሮፕላኑን ዕድሜ መግፋት አጋንነው ተናግረዋል።

ቀጠል አድርገው "ነገር ግን አዳዲሶች እየመጡ ነው" ብለዋል።

በእርግጥ አውሮፕላኑ እየመጣ ነው፤ ነገር ግን ለትራምፕ በቂ አይደለም። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው፣ በቦይንግ የተሠራውን የተሻሻለ የፕሬዝዳንት አውሮፕላን በሥራ ላይ ለማዋል ቃል ገብተው ነበር።

ትራምፕ የፕሬዝደንት ኬኔዲ ዲዛይን ምርጫ የነበረውን ቀይ-ነጭ-ሰማያዊ ቀለምን በመተው የራሳቸውን ቀለም መርጠዋል። የዚያን አውሮፕላን ሞዴል በጽህፈት ቤታቸው [በኦቫል ኦፊስ] ውስጥ በኩራት አሳይተው ነበር።

ኤር ፎርስ ዋን

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 ይደርሳል ተብሎ የነበረው አዲስ አውሮፕላን መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን ለግንባታ የተተመነው 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሁለቱ አውሮፕላኖች በታቀደላቸው ጊዜ ውስጥ ይደርሳሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ሆኗል።

የትራምፕ የሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ደግሞ በ2029 ጥር ወር ያበቃል።

በዚህ ባረጀ አውሮፕላን መጓዝ ምቾት እንደሚነሳው በግል ሲናገር ተደምጧል የተባለው ቢሊየነሩ ኤለን መስክ የአውሮፕላኖቹን ጉዳይ በቅርበት እንዲከታተል እና እንዲያፋጥን በፕሬዝደንቱ ኃላፊነት ቢሰጠውም ቦይንግ በተባለው ጊዜ ለማድረስ እንደማይችል ታውቋል።

ለዚያም ይመስላል ፕሬዝደንቱ ከአገር አገር፣ ከግዛት ግዛት ለሚጓዙበት አውሮፕላን ፈጣን ምላሽ ሲያፈላልጉ የኳታሩ ንጉሥ ስጦታ በራቸውን አንኳኩቶ ከተፍ ያለው።

400 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቅንጡ 747-8 አውሮፕላን ለመስጠት የኳታር መንግሥት እንደሚፈልግ ዜናው ሲሰማ መነጋገርያ ብቻ ሳይሆን ተገቢውን ማጣራት እና የሕግ ሂደት እስኪያልፍ ወራት እንደሚፈጅ ተገልጿል።

ትራምፕ ኳታር ልትሰጣቸው ቃል የገባችውን አውሮፕላን ሥልጣን ላይ በወጡ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የካቲት ወር አጋማሽ ላይ በምስጢር መጎብኘታቸው ተሰምቷል።

ስጦታው ከፕሬዝደንቱ አጋሮች እና ተቺዎች ከቀረቡበት የሥነ ምግባር እና የሕግ ጥያቄዎች ባሻገር የውጪ አገር 747 አውሮፕላንን ወደ አሜሪካ ፕሬዝደንት መጓጓዣነት መቀየር በርካታ ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች አሉት።

አውሮፕላኑ በአየር ላይ እያለ ነዳጅ መሙላት እንዲችል መደረግ እንዲሁም የደኅንነት እና የኮምዩኒኬሽን መሳሪያዎች ድጋሚ ሊገጠምለት ይገባል።

አሁን ያሉት የፕሬዝደንቱ አውሮፕላን ሞዴሎች የኒውክሌር ፍንዳታ እና ኤሌክትሮማግኔቲክ ጥቃትን ለመቋቋም የተገነቡ ሥርዓቶች አሏቸው።

የኤሮዳይናሚክ አድቫይዘሪ ዳይሬክተር እና የአቪየሽን ጉዳዮች ተንታኝ የሆነው ሪቻርድ አቦላፊያ እንዲህ ዓይነት የማሻሻያ ጥገናዎች ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ገልጾ ቢያንስ እስከ 2030 ድረስ ይቆያል ብሏል።

"አውሮፕላኑ ለ13 ዓመታት በአደገኛ ቦታ ክትትል ሳይደረግለት መቆየቱን ከግምት ማስገባት አለባቸው" ብሏል። "ይህ ማለት አውሮፕላኑን ለብቻ መውሰድ በቂ አይደለም። እያንዳንዱን አካል ለየብቻ መውሰድ አስፈላጊ ነው"

አውሮፕላኑ አዲሶቹን ሥርዓቶቹን ለማንቀሳቀስ ተጨማሪ ኃይል ያስፈልገዋል፤ እና ውስጡ መስተካከል አለበት። በዚህ በአየር ላይ በሚበረው ቤተ መንግሥት የመጀመሪያው ዲዛይን ውስጥ ጋዜጠኞች የሚቀመጡበት ስፍራ አልታሰበም።

የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መከላከያ እና ደኅንነት ክፍል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማርክ ካንቺያን እንደዚህ ዓይነት መልሶ የማደራጀት፣ የማሟላት ወጪዎች በቀላሉ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ሊደርሱ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ሆኖም ትራምፕ ከመረጡ የተወሰኑትን ወይም ሁሉንም የደኅንነት ማሻሻያዎችን ሊያስቀሩ እንደሚችሉ ገልጿል።

"ፕሬዝደንት እኮ ናቸው" ብሏል።

ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሁን ያለው ኤር ፎርስ ዋን 747 በመጨረሻ ጡረታ ሲያወጣ፣ ለአሥርት ዓመታት የአሜሪካ ታሪክ አካል ሆኖ ታሪኩ ይሰነዳል።

በ1995 ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተንን ከቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ጂሚ ካርተር እና ጆርጅ ኤችደብሊው ቡሽ ጋር ወደ ለይትዛክ ራቢን የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደ እስራኤል ማጓጓዙን ጨምሮ ታሪክ ይጻፍለታል።

የዓለም ንግድ ማዕከል እና ፔንታጎን የአሸባሪ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በኤር ፎርስ ዋን ውስጥ አየር ላይ በመሆን፣ አየር ላይ ነዳጅ እየሞላ ለሰዓታት የደኅንነት ቡድኑ ለማረፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እስኪያሳውቅ ድረስ ማገልገሉ ይነገርለታል።

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በበረራ ላይ ሳሉ ስልክ ደውለው ሲያዋሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስድስት የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች በዚህ አውሮፕላን ወደ ተለያዩ ዓለም ጫፎች ተጉዘዋል።

አንዱ ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጆ ባይደንን አጓጉዟል።

ዶናልድ ትራምፕ መካከለኛው ምሥራቅን በሚጎበኙበት ወቅት የሳዑዲ አረቢያ፣ የኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በአየር ክልላቸው ሲደርሱ ወታደራዊ ጄቶች ማረፊያው አጅበውታል።

ምንም እንኳ ኤር ፎርስ ዋን ዕድሜው ቢገፋም ለዓለም የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ሥልጣን እና አቅም ማሳያ ሆኖ አገልግሏል። ኤር ፎርስ ዋን ወታደራዊ አውሮፕላን ሆኖ ነገር ግን ከፍ ላለ እና ለተለየ ዓላማ ውሏል።

ኤር ፎርስ ዋን "የተሠራው ለቅንጦት አይደለም" ይላል አቦላፊያ። "አውሮፕላኑ የሚበር የማዘዣ ማዕከል ነው። እዚያ ውስጥ ቸበር ቻቻ ሊዘጋጅበት አይችልም።"