ኬንያ ውስጥ ቱሪስቶችን የያዘ አውሮፕላን ተከስክሶ አሳፍሯቸው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ሞቱ

የአውሮፕላኑ ስብርባሪ እና ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኬንያ መገናኛ ብዙኃን አውሮፕላኑ በእሳት የተቃጥሎ እና ስብርባሪው በወደቀበት ቦታ ላይ ተበታትኖ የሚያሳዩ ምሥሎችን እያሠራጩ ነው።

ኬንያ ውስጥ ቱሪስቶችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን የባሕር ዳርቻ ግዛት በሆነችው ክዋሌ ውስጥ ወድቆ መከስከሱን የአገሪቱ አቭዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።

በአደጋው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 10 አውሮፓውያን እና ኬንያዊ አብራሪ ሕይወታቸው ማለፉን የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆነው ኩባንያ አስታውቋል።

ሞምባሳ ኤር ሳፋሪ የተባለው ድርጅት እንዳለው በአውሮፕላኑ ውስጥ ስምንት ሃንጋሪያውያን፣ ሁለት ጀርመናውያን እና አንድ ኬንያዊ የነበሩ ሲሆን በአደጋው የሁሉም ሕይወት ጠፍቷል።

የአውሮፕላኑ ኩባንያ ባወጣው መግለጫ ላይ "በአሁኑ ጊዜ ቀዳሚው ትኩረታችን የሚሆነው በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች ቤተሰቦች የሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ነው" ሲል ገልጿል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት ሰዎች በዓለም ታዋቂ ወደ ሆነው የማሳይ ማራ ፓርክ የሚሄዱ ቱሪስቶች እንደሆኑ እና ከመካከላቸውም ማንም ሰው ይተርፋል ተብሎ እንደማይታመን የክዋሌ ግዛት አስተዳዳሪ ስቴፈን ኦሪንዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኬንያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን እንዳለው ቱሪስቶቹን ያሳፈረው አውሮፕላን አደጋው የደረሰበት በጎብኚዎች ከምትዘወተረው የባሕር ዳርቻ መዝናኛዋ ዲያኒ በማለዳ ተነስተው ወደ ፓርኩ ሲያመሩ ንጋት 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ ነው።

የኬንያ መገናኛ ብዙኃን አውሮፕላኑ በእሳት የተቃጥሎ እና ስብርባሪው በወደቀበት ቦታ ላይ ተበታትኖ የሚያሳዩ ምሥሎችን እያሠራጩ ነው።

የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሠራተኞች በአደጋው ስፍራ ደርሰው ያጋጠመውን ጉዳት እና የአደጋውን ምክንያት እየመረመሩ ነው።

ነገር ግን ባለሥልጣኑ አደጋው በደረሰበት አውሮፕላን ውስጥ ስለነበሩት ሰዎች ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ኦሪንዴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን የጉብኝት ጉዞን የሚያዘጋጅ ድርጅት ንብረት እንደሆነ እና ወድቆ የተከሰከሰውም ከዲያኒ ተነስቶ ከወጣ በኋላ ክዋሌ ከተማ ሊደርስ 10 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ነው።

አውሮፕላኑ ማሳይ ማራ ውስጥ ወደሚገኘው ኪችዋ ቴምቦ ወደ ተባለው የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ እያቀና ነበር።

አስተዳዳሪው ጨምረውም ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማወቅ ምርመራ ለማድረግ በአካባቢው ያለው መጥፎ የአየር ሁኔታ እንቅፋት ሆኗል።

"በአሁኑ ወቅት እዚህ ያለው የአየር ሁኔታ ጥሩ አይደለም፤ ከማለዳው ጀምሮ እየዘነበ እና ጭጋጋማ ነው። ስለአደጋው ምክንያት ምንም ማለት አንችልም" ብለዋል ኦሪንዴ።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የሕክምና በጎ አድራጎት ቡድን የሆነው አምሬፍ ንብረት የሆነ ቀላል አውሮፕላን ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ዳርቻ ላይ ወድቆ ተከስክሶ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።