በሆንግ ኮንግ አንድ አውሮፕላን ከመንደርደሪያው ተንሸራትቶ ባሕር ውስጥ በመግባቱ ሁለት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ የጭነት አውሮፕላን ሰኞ ዕለት በሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንደርደሪያ አስፓልቱ ተንሸራቶ በመውጣት ባሕር ውስጥ በመግባቱ ሁለት ሠራተኞች ሞቱ።
የኤሚሬትስ አውሮፕላን የሆነው እና ከዱባይ ተነስቶ ሆንግ ኮንግ የደረሰው የበረራ ቁጥር ኢኬ9788 ከመንደርደሪያው ላይ ተንሸራትቶ ከአውሮፕላን ማረፊያው መኪና ጋር መጋጨቱ ተገልጿል።
በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሲሞቱ፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት አራት የበረራ አባላት ከአደጋው ተርፈዋል።
ይህ ክስተት በሆንግ ኮንግ ከዓመታት በኋላ ከደረሱ የአቪዬሽን አደጋዎች መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
የከተማው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መልካም የደኅንነት ታሪክ አለው።
ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ወቅት የተፈጠረው ስህተት ላይ ምርመራ ጀምረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ኃላፊዎች ለአውሮፕላኑ ትክክለኛውን መመሪያ እንደሰጡ እና አውሮፕላኖቹን ለመምራት በማረፊያው ተገቢው ምልክቶች መቀመጣቸውን ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ስቲቨን ዩ እንደተናገሩት የቅኝት መኪናው በወቅቱ ከአውሮፕላን መንደርደሪያ ውጪ በሆነ መንገድ ላይ "ከመንደርደሪያው ደኅንነቱ በተጠበቀ ርቀት" ይጓዝ ነበር ብለዋል።
ከዚያ በኋላ አውሮፕላኑ ከማኮብከቢያው በመውጣት ከተሽከርካሪው ጋር በመጋጨቱ ወደ ባሕሩ ውስጥ እንደገፋው ዩ አብራርተዋል።
መኪናው "በእርግጠኝነት ወደ ማኮብኮቢያው መንገድ አልሄደም" ሲል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከሰዓታት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ "በተለምዶ አውሮፕላኑ ወደ ባሕር መዞር የለበትም" ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ጊዜ የአደጋ ምልክት አላስተላለፈም ብለዋል።
ባሕር ጠላቂዎች የቅኝት ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩትን ግለሰቦች አስከሬን ከባሕር ውስጥ አውጥተዋል።
ሁለቱ የሞቱት የአየር መንገዱ ሠራተኞች ዕድሜያቸው 30 እና 41 ሲሆን የሰባት እና የ12 ዓመት ልምድ እንደነበራቸው ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
የሆንግ ኮንግ የትራንስፖርት ቢሮ ሠራተኞቹ ሕይወታቸው በማለፉ "ማዘኑን" ገልጾ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
የኤሜሬትስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ አውሮፕላኑ በሆንግ ኮንግ ሲያርፍ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረው "ሠራተኞቹ ደህና መሆናቸውን ተረጋግጧል እና ምንም ጭነት አልጫነም ነበር" ብለዋል ።
በተጨማሪም ቦይንግ 747-481 የካርጎ አውሮፕላን ከቱርክ አክት አየር መንገድ በኪራይ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የኪራይ ውሉ አየር መንገዱ አውሮፕላኑን፣ ሠራተኞቹን እና ኢንሹራንሱን ለሌላ አየር መንገድ የሚሰጥበት መንገድን የተከተለ ነው ተብሏል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት አራት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ከአደጋው በኋላ የአውሮፕላኑን የአደጋ ጊዜ በሮች ከፍተው ነበር።
በሁለት ደቂቃ ውስጥ ወደ ቦታው በደረሱ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ከአደጋው አካባቢ እንዲወጡ መደረጉን ባለሥልጣናት ጨምረው ተናግረዋል።
ከአደጋው ስፍራ የተገኙ ምሥሎች እንደሚያሳዩት አውሮፕላኑ ለሁለት ተከፍሏል።
ከፊሉ የአውሮፕላን አካል በውሃው ውስጥ ሰምጦ ሲገባ ቀሪው ክፍል ደግሞ ከላይ ተንሳፍፎ ይታያል።
አንድ የፖሊስ ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃን የወንጀል ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የሆንግ ኮንግ የአየር አደጋ ምርመራ ባለሥልጣን የበረራ መረጃ መቅጃውን እና የአብራሪዎቹ ክፍል ድምጽ መቅጃን (ጥቁር ሳጥን) ከባሕር ውስጥ ለማውጣት እየሞከሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተጎዳው የአውሮፕላኖች ማኮብኮቢያ ዛሬ ተዘግቶ የሚቆይ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት መንደርደሪያዎች ግን አሁንም ሥራ ላይ ናቸው።
ሰኞ ዕለት በሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቢያንስ 11 የጭነት አውሮፕላኖች ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ሁሉም በረራዎች ተሰርዘዋል።
አየር ማረፊያው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ ወር 1998 ቀድሞ ከነበረበት አሁን ወዳለበት ከተዛወረ በኋላ ይህ አደጋ በአውሮፕላን ማረፊያው የደረሰ ሁለተኛው ትልቅ አደጋ ነው።
በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 1999 የቻይና አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን በሚያርፍበት ወቅት ባጋጠመው ከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት ወድቆ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።















