ባልታሰበ ምክንያት በረራ ቢሰረዝብዎት አሊያም ቢራዘም ምን ማድረግ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዓለማችን እጅግ ግዙፍ ከሚባሉ አየር ማረፊያዎች አንዱ የሆነው የለንደኑ ሂዝሮው አርብ ዕለት ባጋጠመው ክስተት ምክንያት አገልግሎት ሳይሰጥ ውሏል።
በአየር ማረፊያ አካባቢ ያለ የኤሌክትሪክ ጣቢያ ላይ በደረሰ አደጋ ምክንያት ነው ሂዝሮው ከአገልግሎት ውጭ የሆነው።
በዩናይትድ ኪንግደም እጅግ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ይህ አየር ማረፊያ በክስተቱ ምክንያት 1300 የሚሆኑ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገዷል።
ለመሆኑ በመሰል ምክንያቶች በረራዎ ቢሰርዝብዎ አሊያም ቢራዘም ምን ማድረግ ይችላሉ? መብትዎስ ምን ይላል?
በረራ ቢቋረጥ ምን ማድረግ እችላለሁ?
ከቤት ሳይወጡ በረራዎ ከተቋረጠ ወደ አየር ማረፊያ ማቅናት አይመከርም። ነገር ግን ከአየር መንገዱ የሚደርስዎን መረጃ መከታተል እና ተጨማሪ መረጃ ማሰባሰብ መልካም ነው።
ብዙውን ጊዜ አየር መንገዶች በረራ ሲራዘም ገንዘብ ይመልሳሉ አሊያም አማራጭ በረራ ያቀርባሉ።
ቲኬት የገዛሁበትን ገንዘብ ማግኘት እችላለሁ?
በዩናይትድ ኪንግደም ሕግ መሠረት እንዲህ የመሰሉ ክስተቶች ሲያጋጥሙ አየር መንገዱ ቲኬት የገዙበትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ መመለስ አሊያም አማራጭ በረራ ማቅረብ አለበት።
አብዛኛዎቹ አየር መንገዶች በራሳቸው ምክንያት በረራ ሲቋረጥ ገንዘብ ይመልሳሉ።
አንደኛው በረራ ተቋርጦ ነገር ግን ሙሉ ገንዘብ የሚመለስባቸው ክስተቶች አሉ። ለምሳሌ ደርሶ መልስ ቲኬት ቆርጠው አንደኛውን በረራ ቢቋረጥ የሙሉ ቲኬቱን ዋጋ ማስመለስ ይችላሉ ማለት ነው።
ገንዘብ እንዲመለስልዎ ከጠየቁ አየር መንገዱ ከዚህ ያለፈ ኃላፊነት የለበትም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች አየር መንገዶች ገንዘብ መመለስን የተመለከተ ፖሊሲ (ሪፈንድ ፖሊሲ) መረጃ በድረ-ገፃቸው ያስቀምጣሉ።
ሌላ በረራ ማግኘት እችላለሁ?
በረራ ቢቋረጥም ጠብቀው መጓዝ ከፈለጉ አየር መንገዱ በተቻለው መጠን በሚቀጥለው በረራ የማሳፈር ግዴታ አለበት። አስፈላጊ ከሆኑ በሌሎች አየር መንገዶችም ሊያሳፍርዎ ይችላል።
ነገር ግን ልክ እንደ ሂዝሮው አየር ማረፊያ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም ሌሎችም አየር መንገዶች እክል እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።
አየር መንገዶች ሌላ ምን ግዴታ አለባቸው?
አየር ላይ አሊያም አየር ማረፊያ ከሆኑ አየር መንገዶች እርስዎን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው።
ለምሳሌ በረራዎ በነጋታው ከሆነ የሚያድሩበትን ሆቴል ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።
ከአየር ማሪፈያ ሆቴል እንዲሁም ከሆቴል ወደ አየር ማረፊያ የሚያመላልስ ትራንስፖርት ማዘጋጀትም ግዴታቸው ነው።
የምግብ እና መጠጥ ዋጋን መሸፈን ይኖርባቸዋል። ብዙውን ጊዜ ይህን የሚያደርጉበት ወረቀት ያዘጋጃሉ። መንገደኞች ይህን ወረቀት እያሳዩ መመገብ ይችላሉ።
መንገደኞች ስልክ መደወል ካለባቸው እና የአየር ሰዓት ከገዙ የዚህንም ውጭ መሸፈን አለባቸው።
አየር መንገዱ ይህን ማድረግ ካልቻለና እርስዎ ይህን ካደረጉ ያወጡትን ወጪ አየር መንገዱ እንዲሸፍን የመጠየቅ መብት አለዎት።
የዩናይትድ ኪንግደም አቪየሽን ባለሥልጣን መንገደኞች ደረሰኝ እንዳይጥሉ እና ከተገቢው በላይ ወጭ እንዳያወጡ ይመክራል።
በረራዬ ቪዛ ወደሌለኝ ሀገር ከተዛወረስ?
ለምሳሌ የዩናይትድ ኪንግደም ቪዛ ኖሮዎት ነገር ግን በረራው ወደ ቪዛ ወዳልያዙበት የአውሮፓ ሀገር ቢዘዋወር አየር መንገዱ ተገቢውን ኃላፊነት መወጣት አለበት።
ቪዛ ከሌለዎ አየር መንገዶች ብዙውን ጊዜ አውሮፕላን ውስጥ እንዲቆዩ አሊያም አየር መንገዱ ውስጥ ባለ ሥፍራ እንዲቆዩ ያደርጋል።
ነገር ግን ቀጣዩ በረራው ረዥም ጊዜ የሚወስድ ከሆነ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ያለ ሆቴል ሊወስድዎ ይችላል።
ይህ ሲሆን መንገደኞች ፖርት ቪዛ የሚባል ማኅተም ሊመታላቸው አሊያም 'ቪዛ ኦን አራይቫል' ሊሰጣቸው ይችላል።
ዊች የተሰኘው ተቋም እንደሚመክረው በተለይ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና ባሉ ሀገራት ያለቪዛ ከገቡ ወደ ኢሚግሬሽን ሰዎች ሄደው የአደጋ ጊዜ መውጫ አሊያም ማራዘሚያ መጠየቅ ይገባል።
ከላይ ከተጠቀሱት መረጃዎች በተጨማሪ በረራዎ ከሁለት እስከ አራት ሰዓታት ከተራዘመ ከአየር መንገዱ እርዳታ ማግኘት ይችላሉ።
በረራው ከአምስት ሰዓታት በላይ ከተራዘመ ገንዘብ እንዲመልስልዎ መጠየቅ አሊያም አማራጭ በረራ እንዲዘጋጅልዎ የመጠየቅ መብት አለዎት።












