በኬንያ አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሶ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ

የተከሰከሰው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ንብረትነቱ የረድኤት ድርጅት የሆነ አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሶ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ።

አምሬፍ የተባለው ረድኤት ድርጅት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ከኬንያ ዊልሰን አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ሶማሊያ ሐርጌሳ መንገድ የጀመረው አውሮፕላን በናይሮቢ የመኖሪያ ህንፃ ላይ ወድቆ በእሳት መያያዙን አስታውቋል።

የኪያምቡ ግዛት ኮሚሽነር ሄነሪ ዋፉላ አብራሪውን ጨምሮ ሐኪሞች እና ነርሶች በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉን ያሳወቁ ሲሆን፤ በተጨማሪም በአካባቢው የነበሩ ሌሎች ሁለት ሰዎችም ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ሁለት ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ መርማሪዎች ወደ አካባቢው መላካቸውም ታውቋል።

አውሮፕላኑ በተነሳ በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ከአየር ተቆጣጣሪዎች ጋር የነበረው የራዲዮ እና የራዳር ግንኙነት መቋረጡን የኬንያ አቪየሽን ባለሥልጣን ገልጿል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የተሳፈሩ የአምሬፍ ረድኤት ድርጅት ባልደረቦች እና ሠራተኞች እንደነበሩ ድርጅቱ አስታውቋል።

የአምሬፍ ስራ አስፈፃሚ ስቴፈን ጊታው "በዚህ ሰዓት ከሚመለከታቸው የአቪየሽን ባለሥልጣናት እና በሁኔታው ዙሪያ ያሉ እውነታዎችን ለማጣራት ከተቋቋመው የአደጋ ጊዜ ቡድን ጋር እየተባበርን ነው" ብለዋል።

የፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራውን ለመፈፀም የኬንያ መከላከያ ኃይል እና ብሔራዊ ፖሊስ አካባቢው ላይ ተመድበዋል።

ፐትሪሺያ ኮምቦ የተባለች የዓይን እማኝ ወደ አካባቢው በታክሲ ከጓደኞቿ እያቀናች ሳለች ከባድ ፍንዳታ እና እሳት ከፊት ለፊታቸው መመልከቷን ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ስልኬን አውጥቼ ከመቅረፄ በፊት እሳቱ ጠፋ፤ ጭስ እየተግተለተለ ነበር። ከዚያም ሰዎች ሲጮሁ እና ሲሯሯጡ አየን፤ እኛም መንገዳችንን አቋረጥን።

"ከዚያም የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ መሆኑን አወቅን። እና መሬት ላይ በአደጋው የተከፈተውን የሰመጠ ጉድጓድ ተመለከትን" ስትል እማኝነቷን ሰጥታለች።

በሌላ አደጋ ከናይሮቢ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ናይቫሻ ከተማ ባቡር እና አውቶብስ ተጋጭተው የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉት ሮይተርስ የዜና ወኪል የቀይ መስቀል ሠራተኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።