"የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ" - በትምህርት ቤት ላይ ከተከሰከሰው አውሮፕላን 20 ሕጻናትን አድና ሕይወቷ ያለፈው መምህርት

የባንግላዴሽ አየር አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ተማሪዎቼ እኮ ለእኔም ልጆቼ ናቸው" ማህሪን ቻውዲሪ የተባለችው መምህርት በሕይወት እና በሞት እያጣጣረች ነበር ይህንን ለባለቤቷ የተናገረችው።

ከሞት አፋፍ ላይ ከመገኘቷ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በባንግላዴሽ መዲና ዳካ በሚገኘው ማይልስቶን ስኩል ኤንድ ኮሌጅ የተሰኘው ትምህርት ቤቷ በር ላይ ቆማ ነበር።

ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ለወላጆቻቸው ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ነበረች።

ነገር ግን በሰከንዶች ውስጥ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ።

በደስታ ተሞልቶ የነበረው የሰኞ የምሳ ሰዓት ፕሮግራም ወደ አስፈሪ ሁነት ተቀየረ።

የባንግላዴሽ አየር ኃይል ተዋጊ ጄት በትምህርት ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ ላይ ተከስክሶ በእሳት ጋየ።

ማህሪን አሁንም በሕንጻው መማሪያ ክፍሎች ውስጥ ተማሪዎች እንዳሉ ስለተረዳች በድፍረት ወደሚቃጠለው ሕንጻ ገባች።

"ከ20 እስከ 25 የሚደርሱ ተማሪዎችን ለማውጣት የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ" ስትል ማህሪን በጽኑ ሕሙማን ክፍል ከመግባቷ እና የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ከመገጠሙ በፊት ለባለቤቷ ማንሱር ሄላል እንደገነገረችው ይገልጻል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም" ማለቷንም ባለቤቷ ለቢቢሲ አስረድቷል።

በዳካ ናሽናል በርን ኢንስቲትዩት የሕክምና ማዕከል የተወሰደችው ማህሪን የሕጻናቱን ሕይወት ለመታደግ በምትሞክርበት ወቅት 100 በመቶ በሚባል ሁኔታ ሰውነቷ በእሳት ቃጠሎ ደርሶበታል።

ማህሪን አልተረፈችም፤ በዚያችው ዕለት ሕይወቷ አለፈ።

ሰኞ ሐምሌ 14/2014 ዓ.ም. በደረሰው በዚህ አደጋ ማህሪንን ጨምሮ የ31 ሰዎች ሕይወት የተቀጠፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 25ቱ ሕጻናት ናቸው።

የባንግላዴሽ አየር ኃይል ኤፍ7 የተሰኘው ተዋጊ ጄቱ ሰኞ ዕለት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ለሥልጠና ልምምድ ከተነሳ በኋላ የመካኒካል ችግር እንደገጠመው ገልጿል።

እናም ፓይለቱ ሉቴናንት እና ዶክተር ታውኪር ኢስላም ጄቱን ሰዎች ወደማይበዙበት ቦታ ለመውሰድ መሞከራቸው ተነግሯል። በዚህ አደጋ ከሞቱት ፓይለቱ አንዱ ናቸው።

አደጋው አገሪቱ ባለፉት አስርት ዓመታት በፊት ካጋጠማት አስከፊው የአቪዬሽን አደጋ መሆኑም ተገልጿል።

ከ160 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን በኡታራ አድሁኒክ ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ተረኛ ዶክተር ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ከ10 አስከ 15 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ በርካቶቹም የተጎዱት በጄት ነዳጅ በደረሰባቸው ቃጠሎ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕጻናት እና አዋቂዎችን ጨምሮ ከ50 የሚበልጡት በቃጠሎ ምክንያት ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ናሽናል ኢንስቲትትዩት ኦፍ በርን ኤንድ ፕላስቲክ ሰርጀሪ የተሰኘው የጤና ማዕከል አስታውቋል።

የአውሮፕላን መክስከሱ ዜና ከሰማ በኋላ ለባለቤቱ እንደደወለላት ማንሱር ለቢቢሲ ተናግሯል።

ባለቤቱ ሳትመልስለት ስትቀር ትልቁ ልጁ ወደ እናቱ ትምህርት ቤት ሄዶ የሆነውን ነገር እንዲያጣራ ላከው። ብዙም ሳይቆይ የአምቡላንስ አሽከርካሪ ደውሎ ባለቤቱ በኡታራ ሞደርን ሜዲካል ሆስፒታል ወደሚገኘው የቃጠሎ ክፍል እየተወሰደች እንደሆነ ነገረው።

በኋላም ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል ገባች።

የባንግላዴሽ አየር አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ከመገጠሙ ትንሽ ቀደም ብሎ ማህሪን በሆስፒታል አልጋዋ ላይ ሆና ይቅርታ እንደጠየቀችው ማንሱር ይናገራል።

ማንሱር ከባለቤቱ ጋር የነበረውን የመጨረሻ ጊዜ ሲያስታውስ በእንባ ነው።

"በሕይወት ነበረች። ስትናገርም በታላቅ አዕምሯዊ ጥንካሬ ነበር። መቶ በመቶ ማለትም ውስጣዊ እንዲሁም ውጫዊ አካሏ ቃጠሎ ደርሶባት ነበር" ይላል።

ማህሪን በማይልስቶን ስኩል እና ኮሌጅ ትምህርት ቤት ለ17 ዓመታት ያህል አገልግላለች።

በመጀመሪያ በመምህርነት የተቀጠረች ሲሆን፣ በኋላ ደግሞ ከ2ኛ እስከ አምስተኛ ከፍል ላሉ ተማሪዎች በአስተባባሪነት ተሾመች።

ማህሪን በሰሜን ባንግላዴሽ ኒልፋማሪ በተሰኘችው የትውልድ ስፍራዋ አደጋው በደረሰ በማግስቱ፣ ማክሰኞ ቀብሯ ተፈጽሟል።

በዚህ አደጋ ሕይወታቸው ለተቀጠፉ ሕጻናት እና አዋቂዎችም ባንግላዴሽ ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጃ ሰንደቅ ዓላማዎች ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ተደርጓል።

የባንግላዴሽ ጊዜያዊ መንግሥት መሪ ሙሐማድ ዩኑስ አደጋውን የሚያጣራ የምርመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል።

በመዲናዋ ማክሰኞ ዕለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ተማሪዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ትክክለኛ የሟቾች ቁጥር እንዲገለጽ እንዲሁም የትምህርት አማካሪው ሥራ እንዲለቁ ጥያቄ አቅርበዋል።

በርካቶች የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ዋና በር ሰብረው እንደገቡ ከአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተገኘው ቪዲዮ ያሳያል።

የባንግላዴሽ አየር አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዚህ አደጋ ቢያንስ 25 ህጻናት ተገድለዋል

ተቃዋሚ ተማሪዎችን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ እና ከፍተኛ የድምጽ መሳሪያ የተጠቀመ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በርካቶች መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

ተቃዋሚዎቹ በዚህ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ተጎጂዎች ስማቸው እንዲገለጽ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል ከመጠየቅ በተጨማሪ ያረጁ እና አደገኛ ናቸው ያሏቸው ጄቶች እንዲወገዱ እና የአየር ኃይል ሥልጠና አሰጣጥ እንዲቀየር ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

የባንግላዴሽ የአየር አደጋ የደረሰው ጎረቤቷ ሕንድ በዓለማችን ላይ በአስር ዓመት ውስጥ ከታዩ አሰቃቂ የአየር ትራንስፖርት አደጋ ከደረሰባት ከሳምንታት በኋላ ነው።

ከአንድ ወር በፊት፣ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም. በምዕራብ ሕንድ ከሚገኘው አህመዳባድ አየር ማረፊያ ወደ ለንደን እያቀና የነበረው ቦይንግ 787-87 ድሪምላይነር አውሮፕላን ከተነሳ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነበር የተከሰከሰው።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 242 ተሳፋሪዎች እንዲሁም አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ስፍራ ላይ የነበሩ 19 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

260 ሰዎች በተቀጠፉበት በዚህ አሰቃቂ አደጋ አንድ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ የሆነ መንገደኛ ብቻ በተአምር መትረፍ ችሏል።

የበርካቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው የሕንድ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተነሳ ከሰከንዶች በኋላ የነዳጅ ተቆጣጣሪዎቹ ጠፍተው፤ ወደ ሞተሩ የሚደርሰው ነዳጅ ተቋርጦ እንደነበር አደጋውን አስመልክቶ የወጣው ቅድመ ሪፖርት ማመልከቱ ይታወሳል።

የበረራ መረጃዎችን በያዘው ጥቁር ሳጥን መረጃ መሠረት የአውሮፕላኑ ሁለቱም የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ጠፍተው እንደነበር የሕንዱ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ቢሮ (AAIB) ያወጣው ሪፖርት አሳይቷል።