የህንድ አውሮፕላን ከመከስከሱ በፊት የነዳጅ መቆጣጠሪያዎቹ ጠፍተው ነበር- ሪፖርት

የህንድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለ260 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው የህንድ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተነሳ ከሰኮንዶች በኋላ የነዳጅ ተቆጣጣሪዎቹ ጠፍተው፤ ወደ ሞተሩ የሚደርሰው ነዳጅ ተቋርጦ እንደነበር አደጋውን አስመልክቶ የወጣው ቅድመ ሪፖርት አመላከተ።

አደጋውን ተከትሎ ከኮክፒት የተገኘ የድምጽ ቅጂ አንደኛው ፓይለት "ለምን አቋረጥከው?"ሲል የሚሰማ ሲሆን ሌላኛው አብራሪ ደግሞ "አኔ አላቋረጥኩትም" ሲል ይደመጣል።

ከአንድ ወር በፊት፣ ሰኔ 5/ 2017 ዓ.ም በምዕራብ ህንድ ከሚገኘው አህመዳባድ አየር ማረፊያ ወደ ለንደን እያቀና የነበረው ቦይንግ 787-87 ድሪምላይነር አውሮፕላን ከተነሳ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ነው የተከሰከሰው።

260 ሰዎች በተቀጠፉበት በዚህ አሰቃቂ አደጋ አንድ እንግሊዛዊ መንገደኛ ብቻ በተአምር መትረፍ ችሏል።

በህንዱ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ቢሮ (AAIB) የሚመራው ምርመራ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ፤ዘርዘር ያለ እና የተጠናቀረው የመጨረሻው ሪፖርት በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ እንደሚወጣ ይጠበቃል።

የበረራ መረጃዎችን በያዘው ጥቁር ሳንዱቅ መሰረት የአውሮፕላኑ ሁለቱም የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ጠፍተው እንደነበር አሳይቷል።

አውሮፕላኑ ከተነሳ ከሰኮንዶች በኋላ መቆጣጠሪያዎቹ ከመብራት ወደ መጥፋት በመቀየራቸው ወደ ሞተሩ የሚወስደው ነዳጅ መቋረጡን መረጃው አመላክቷል።

የነዳጅ መቆጣጠሪያዎቹ አብዛኛውን ጊዜ እንዲጠፉ የሚደረጉት አውሮፕላኖች ካረፉ በኋላ ወይም ሞተሩ እሳት መያያዝ ባሉ ድንገተኛ ሁኔታዎች ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አውሮፕላኖች በሚነሱበት ወቅት የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች በፍጹም እንደማይጠፉም ተገልጿል።

የነዳጅ መቆጣጠሪያዎቹ በመጥፋታቸው የአውሮፕላኑ ሁለቱም ሞተሮች ኃይላቸውን (ግፊታቸውን) እንዳሳጣቸው የምርመራው ሪፖርት አመልክቷል።

ከዚያም በኋላ በኮክፒቱ ውስጥ ግራ መጋባት የፈጠረ ሲሆን አንደኛው አብራሪ ሌላኛውን ለምን የነዳጅ መቆጣጠሪያዎቹን እንዳጠፋ ሲጠይቀው ተሰምቷል።

በለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ እያቀና የነበረው አውሮፕላን ዋነኛ አብራሪ ሰሚት ሳብሃርዋል ሲሆን ረዳት አብራሪው ክላይቭ ኩንዳር ነው።

በኮክፒቱ ሲሰማ የነበረው ድምጽ የትኛው የማን እንደሆነ ሪፖርቱ አልጠቀሰም።

ወዲያውኑ የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች (ማብሪያ/ ማጥፊያ) ወደ መደበኛ የበረራ ቦታ ተመልሶ ነዳጅ ወደ አውሮፕላኑ ሞተር እንዲሄድ ሆኖ ነበር።

አንደኛው ሞተር ኃይሉን መልሶ ማግኘት ቢችልም የአውሮፕላኑን ፍጥነት መቀነስ መመለስ አልቻለም ብሏል።

አውሮፕላኑ ተከስክሶ ለጤና ባለሙያዎች ማደሪያነት የሚያገለግል ህንጻ ላይ ወድቆ ፍንዳታ ከመከሰቱ በፊት አንደኛው አብራሪ የእርዳታ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ሁለቱም አብራሪዎች ከበረራው በፊት "በቂ የእረፍት ጊዜ" እንደነበራቸው ሪፖርቱ አክሏል።

ባለሙያዎች ቀደም ሲል ወፎች አደጋውን አስከትለውት ሊሆን እንደሚችል ገምተው ነበር፤ ነገር ግን ሪፖርቱ በአውሮፕላኑ የበረራ አቅጣጫ "የወፍ እንቅስቃሴ የለም" ሲል አስፍሯል።

ሪፖርቱ አክሎም "በዚህ የምርመራ ደረጃ ለቦይንግ 787-8 ወይም ጂኢጂኢኤንኤክስ-1 ቢ የሞተር አፐሬተሮች እና አምራቾች የምንሰጠው የምክር እርምጃዎች የሉም። በአውሮፕላኑ ወይም በሞተሮቹ ላይ ምንም ትልቅ ስህተት አልተገኘም" ብሏል።

የህንድ አየር መንገድ ቃል አቀባይ አየር መንገዳቸው ቅድመ ሪፖርቱን መቀበሉን አሳውቋል።

"ምርመራው እየገፋ ሲሄድ ከህንድ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ቢሮ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ሙሉ በሙሉ መተባበር እንቀጥላለን። ምርመራው አለመጠናቀቁን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተወሰኑ ዝርዝሮች ላይ አስተያየት አንሰጥም። የሚነሱ ጥያቄዎችም የምርመራ ቢሮው ይመልሳል" ሲሉ ቃል አቀባዩ አክለዋል።

ቦይንግ በበኩሉ በተባበሩት መንግሥታት አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ፕሮቶኮልን በማክበር ስለተከሰከሰው አውሮፕላን መረጃ ኃላፊነቱ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ቢሮ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አትቷል።

አክሎም ለምርመራው እንዲሁም ለደንበኛው የህንድ አየር መንገድ ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጿል።