ቀሲስ በላይ ይግባኝ አቅርበው የእስር ቅጣታቸው ወደ 3 ዓመት ከሰባት ወር ተቀነሰ

በሐሰተኛ ሰነድ ከአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ገንዘብ ለማውጣት በመሞከር በሙስና ወንጀል እስር እና የገንዘብ ቅጣት የተፈረደባቸው ቀሲስ በላይ መኮንን የእስር ቅጣታቸው መቀነሱ ተገለጸ።

በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው አምስት ዓመት እና 10 ሺህ ብር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ቀሲስ በላይ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለታቸውን ተከትሎ የእስር ቅጣታቸው እንዲቀነስ መወሰኑን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ረቡዕ፣ ሐምሌ 16/ 2017 ዓ.ም የዋለው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት የቀሲስ በላይን ቅጣት ወደ ሦስት ዓመት ከሰባት ወር እስር እንዲቀነስ መወሰኑን ጠበቃቸው አቶ ገብሩ ማህተም ገልጸዋል።

ከቀሲስ በላይ ጋር በተመሳሳይ ክስ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ተፈርዶባቸው የነበሩት ሁለት ተከሳሾች እስራቸው ወደ ሦስት ዓመት ዝቅ እንዲል ፍርድ ቤቱ ብይን ማስተላለፉን አቶ ገብሩ አክለዋል።

ቀሲስ በላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያስገቡት ይግባኝ ለስር ፍርድ ቤት በርካታ የቅጣት ማቅለያ መረጃዎች ቢያቀርቡም የተያዘላቸው አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ ነው።

ጠበቃ ገብሩ እንደሚሉት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቀሲስ በላይ ያቀረቡትን ምክንያት ተቀብሎ ተጨማሪ ሁለት የቅጣት ማቃለያዎችን በመያዝ የእስር ቅጣታቸውን ቀንሶታል።

ወደ 23 የሚሆኑ የቅጣት ማቅለያዎችን ደንበኛቸው እንዳቀረቡ የሚናገሩት ጠበቃው፤ ከእነዚህም መካከል በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ያላቸው ተሳትፎ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው፣ የጤና ጉዳይ፣ ከዚህ በፊት በወንጀል ተሳትፎ የሌላቸው መሆኑ፣ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ተሳትፎ የሚሉ ተካተውበታል።

የስር ፍርድ ቤቱ ግን እነዚህን በአምስት "እንደጨመቃቸው" የሚናገሩት ጠበቃው እነዚህ ማቅለያዎች ቢያንስ ወደ ሰባት የሚመነዘሩ ናቸው በሚል ሁለት ተጨማሪ ማቅለያዎችን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንደያዘላቸው ያስረዳሉ።

ፍርድ ቤቱ ሁለት ተጨማሪ ማቅለያዎችን በመያዝም ቅጣቱን መቀነሱን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የቅጣት ውሳኔ የተላለፈው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥር 22/2017 ዓ.ም. ነበር።

ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች ዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበባቸው የወንጀል ሕጉን እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ተላልፈዋል በሚል ነበር።

ግለሰቦቹ ላይ የተመሠረተው ክስ በአፍሪካ ኅብረት ስም የተዘጋጀ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ስድስት ሚሊዮን 50 ሺህ ዶላር ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ነው።

ጠበቃ ገብሩ እንደሚሉት ከጥፋተኝነት ጋር ተያይዞ፣ ቀሲስ በላይ ጥፋተኛ የተባሉበትን ድንጋጌ፣ የእሳቸውን ተሳትፎ፣ የተጠቀሰባቸውን አዋጅ በተመለከተ፤ እንዲሁም ሌሎች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን አንስተው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያቀረቧቸው ቅሬታዎች ውድቅ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከቅጣት ጋር ተያይዞ ሁለት ቅሬታዎችን ማቅረባቸውን የሚናገሩት ጠበቃ ገብሩ የመጀመሪያው ቅሬታ የቅጣት መጠኑ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቀሲስ በላይ የቅጣት ደረጃ ሲያዝ "የእሳቸው ተለይቶ መካከለኛ" በሚል እና የሌሎቹ በቀላል መያዙን በመጥቀስ፤ "መካከለኛ ተብሎ መያዙ አግባብ አይደለም" በሚል ተከራክረዋል።

ሌላኛው ደግሞ ካለባቸው የጤና እክል እና ከነበራቸው ማኅበራዊ አስተዋጽኦ አንጻር በማስጠንቀቂያ በሚል የገደብ ጥያቄን ቢያቀርቡም ሁለቱም ውድቅ መደረጉን ያስረዳሉ።

በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ክርክራቸውን እንዳልጨረሱ የሚናገሩት ጠበቃው "መሠረታዊ የሕግ ክፍተት አለባቸው ብለን የምናምናቸውን ነጥቦች አሉ፤ እሱን መሠረት አድርገን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት የምናቀርብበት አግባብ ይኖራል" ብለዋል።

ቀሲስ በላይ ወደ ሁለት ዓመት የሚጠጋ፣ አንድ ዓመት ከስምንት ወር በማረሚያ ቤት መቆየታቸውንም አውስተዋል።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ለመመሥረት በነበራቸው እንቅስቃሴ የሚታወቁት ቀሲስ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበሩ።